www.maledatimes.com ቅዱስ ጋብቻ ወይስ ጅምላ ጋብቻ? - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ቅዱስ ጋብቻ ወይስ ጅምላ ጋብቻ?

By   /   October 8, 2012  /   1 Comment

    Print       Email
0 0
Read Time:20 Minute, 59 Second

 

matrimonyጋብቻን በተመለከተ፣ ሦስት አሳሳቢ አዝማሚያዎች ይታያሉ። የመጀመሪያው፣ የክርስቲያንና የእስላም ጋብቻ ሲሆን። ቀጥሎ፣ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ። በመጨረሻም፣ የጅምላ ጋብቻ ነው። አንድ ሙስሊም፣ ክርስቲያን ሚስት ማግባት ይችላል ይላል ቁራን። አንዲት ሙስሊም ሴት ግን ክርስቲያን ባል ማግባት አትችልም። ሙስሊም ባል ያገባችዋ ሴትና የምትወልዳቸው ልጆች ደግሞ በክርስቶስ እምነት ውስጥ መሆናቸውን ይከለክላል። በአሁኑ ወቅት ክርስቲያን ነን በሚሉ በአንዳንዶች ዘንድ ከኑሮ ውድነትና እምነትን ካለመረዳት የተነሳ ከሙስሊሞች ጋር የሚጋቡ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል። እምነቱን እንደሚገባ የማያውቅ ምእመን እንግዲህ የተጋለጠ ለመሆኑ ይህ አንድ ማስረጃ ነው። “የሰላምና የመቻቻል” አራማጆች የሚሰብኩንን መስማት ትተን የክርስቶስን ወንጌል እንደሚገባ ማስተማር የሚኖርብን ለዚሁ ነው። “[ክርስቶስን] ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድአትጠመዱ፤ … ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?” [2ኛ ቆሮንቶስ 6፡14-15]። በሌላ አነጋገር፣ ክርስቶስን ላመኑ፣ እግዚአብሔርን መታዘዝ ሰውን ከመታዘዝ ሊቀድምባቸው ይገባል [የሐዋርያት ሥራ 4፡19]። እንደዚሁም፣ የክርስቶስን ትምህርት የማይገነዘቡ ያፈቀዳቸውን ያደርጋሉ ማለት፣ ክርስቶስን ለሚከተሉት መመሪያ ይደነግጉላቸዋል ማለት እንዳይደለ ሊታወቅ ይገባል።

ሌላኛው፣ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ጉዳይ ነው። ግብረሰዶማዊነት ሰብዓዊ መብት ነው በሚል ሳቢያ ሕጋዊ እውቅናና ድጋፍ ለማሠጠት ሕዳር ወር 2004 ዓ.ም. በአፍሪካ አዳራሽ የተደረገውን ሙከራ አንዘነጋም። መንግሥት ይህን ተግባራዊ ካላደረገ እርዳታ እንደሚያጣ አሜሪካና አውሮጳ አስታውቀዋል። የፖለቲካና የቤተክርስቲያን መሪዎችም የተባበረ፣ ግልጽና ጠንካራ አቋም እንደመውሰድ በተናጠል ሲቆሙ፣ ሲያመነቱና ሲያፈገፍጉ ታይተዋል። ዛሬ የመብት ጥያቄ ነው፤ ነገ ግን ጥያቄው የጋብቻ ጥያቄ እንደሚሆን ቤተክርስቲያን መርሣት የለባትም። ቤተሰብ የአገር ህልውና መሠረት እንደመሆኑ፣ በዚህ አፍራሽ በሆነ ጉዳይ ላይ ተቻችሎ መኖር የሚባል ነገር ሊኖር እንደማይችል ግልጽ ይመስለናል።

ሦስተኛው፣ ሰሞኑን እየተወራ ያለው የጅምላ ጋብቻ ወይም “የሺህ ጋብቻ” ጉዳይ ነው። በዚህ መሠረት፣ አንድ ሺህ ተጋቢዎች ከየክልሉ መስተዳደሮች ለየብሔሩ በወጣው መመሪያና ኮታ መሠረት እንደሚመለመሉና ጋብቻቸውን በሕዳር ወር በስፖርት ሜዳ ላይ እንደሚፈጽሙ፣ ይህም በዜና አውታሮች እንደሚሠራጭ አዘጋጆቹ ገልጸዋል። ዓላማው፣ ሀ/ ሠርግ እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ ነው ተብሏል። ሪፖርተር ጋዜጣ፣ በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ድህነት ስላለ፣ ማግባት እየፈለጉ የተሳናቸው እንዳሉ ጠቅሶ፣ የናጠጠ ሠርግ የሚሠርጉትን ወርፏቸዋል፤ ለ/ የመቻቻልን ባህል ለማዳበር መ/ የአዲስ አበባን መቆርቆር 125ኛ ዓመት ለመዘከር ሠ/ “ሺህ ጋብቻን” ዓመታዊ ክብረ በዓል ለማድረግ ረ/ የአገራችንን መልካም ገጽታ ለዓለም ለማስታወቅና በ“ጊነስ” የዓለም ሪኮርድ ለማስመዝገብ ነው ብለዋል። ተጋቢዎች ማመልከቻ ይሞሉና፣ለዚሁ የተቋቋመው ኮሚቴ መዝኖ የሚቀበለውን ተቀብሎ ሌላውን  ውድቅ ያደርጋል፤የተመረጡት ተጋቢዎች ወደየመጡበት ክልል ተመልሰው ይህንኑ አዲስ ባህል ያስተዋውቃሉ ማለት ነው።

ዝግጅቱ በንግድ ለተሠማሩ ገቢ ያስገኛል እንበል። በአገር ደረጃ ግን አደገኛ አዝማሚያ መፍጠር ብቻ ሳይሆን ያልታቀዱ ቆይተው የሚከሰቱ የቀውስ ጽንሶችን እንደቋጠረ ማሰብም ይበጃል። መነሻ አሳቡ፣ ማሕበረሰብን በፈለግነው ሁኔታ እንደ አውራ ጎዳና መቀየስ እንችላለን ከሚል ከ19ኝኛው መቶ ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የተቆነጠረ ይመስላል። ሰው፣ በአምላክ መልክ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ሳይሆን በፍጥረት ሂደት የተገኘ ጅምላ አካል ነው ይላል። ባለፈው ትውልድ፣ እግዚአብሔር የሌለበትን ሶሻሊስታዊ ማሕበረሰብ ለመመሥረት፣ የነበረውን እንዳለ መጣልና ማፍረስ እንደ ተጀመረ እናስታውሳለን። በዚያን ወቅት የአገሬውን ባሕልና የሰውን ተፈጥሮ ካለመረዳት የተነሳ የጠፋውን ሕይወትና የወደመውን ንብረት መጠን እንደማስታወስ፣ ያንኑ ስሕተት በሌላ መልኩ ስንደግም እንዳንገኝ ያሠጋል። ሁለተኛ፣ ልዩ ልዩ መሆን ወንጀል እንዳይደለ ሁሉ፣ አንድ ወጥነትም መቻቻል ነው ሊባል አይችልም። ተጋቢዎቹ ብሔራቸውን ይወክሉ ከተባለ፣ ድርጊቱ አንዱ ብሔር ከራሱ ውጭ ከሌላኛው ብሔር ጋር እንዳይጋባ እንደሚከለክልም አብሮ የታሰበ አይመስልም። ከሺህ ተጋቢዎች ውስጥ ገሚሱ ክርስቲያን [የስም ክርስቲያን ሊሆን ይችላል] ገሚሱም ሌላ ሊሆን ይችላል እየተባልን ነው። ሠርጉ የሚፈጸመው በቤተክርስቲያን ሳይሆን በስፖርት ሜዳ ነው። ዝግጅቱ [ለቱሪስቶች] መዝናኛ እንዲሆን ጭምር ነው። የክርስቲያን ጋብቻ አፈጻጸም፣ በክርስቲያን ሥርዓት በቤተክርስቲያን መሆን ሲገባው፣ በንግድ፣ በመንግሥታዊ ድርጅቶችና በባለሥልጣናት አቀናባሪነት መሆኑ የእግዚአብሔርን ቤት ሥልጣን መቀናቀን ብቻ ሳይሆን ጋብቻ የሰው፣ የፖለቲካና የንግድ ሥራ መደረጉን ማየት አያዳግትም። የቤተክርስቲያንን ሥልጣንና ተልእኮ በማሕበራዊ ድርጅቶች መተካት ወዴት ሊያመራ ይችላል? አውሮጳና ሰሜን አሜሪካ ከደረሰባቸው ማሕበራዊና ሞራላዊ ቀውስ አንጻር ምን ጥንቃቄ ልንወስድ ይጠበቅብናል?

ጋብቻ በመሠረቱ፣ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረግ ቃል ኪዳን ነው። ቅዱስ ነው፤ ከማሕበራዊ ግንኙነቶች ሁሉ የተለየና የከበረ ነው። ጋብቻን የመሠረተው፣ ሰው ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ ነው። የሁሉ ፈጣሪ የሆነ እግዚአብሔር የደነገገው ሥርዓት ስለሆነ ሰዎች እግዚአብሔርን ይመኑ አይመኑ ለውጥ አያመጣም ማለት ነው። “ከፍጥረት መጀመሪያ ግን እግዚአብሔር ወንድና ሴት አደረጋቸው፤ ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤ ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” [ዘፍጥረት 2፡18-25። ማርቆስ 10፡6-9]። “ሺህ ጋብቻ” ይህን አስተምህሮ ይቀናቀናል። የተቀደሰ ሲል፣ የግለሰቦች ክልልና በፍቅር ላይ የተመሠረተ መፈቃቀድ መሆኑን ያመለክታል። ሙሽሮች ይቀድማሉ፤ታዳሚ ይከተላል። ሁለቱ አይነጣጠሉም። ሙሽሮች ይደምቃሉ፤ ታዳሚ ያዳምቃል። የጅምላ ጋብቻ ግን ትኩረቱ “ማሕበራዊው” ላይ ስለሆነ፣ የግለሰብን ሕልውና ይውጠዋል።

በሦስቱ ሥላሴዎች [አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድ አምላክ] ለሚያምኑ በ“ሺህ ጋብቻ” መሳተፋቸውን ወንጌል አይደግፍም። ወንጌል፣ ጋብቻን ክቡርና የተቀደሰ እንደሆነና፣ የሰው ሥራ እንዳይደለ ለማስረዳት፣ በክርስቶስና በቤተክርስቲያን መካከል ባለው ግንኙነት ይመስለዋል። ክርስቶስን ባል፣ ቤተክርስቲያንን ሚስት፤ ወይም ሙሽራና ሙሽራዪቱ ይላቸዋል። ሙሽራዪቱን ፍለጋ ዳግመኛ ሲመለስ የሠርግ ግብዣ እንደሚኖርም ይጠቅሳል፣ “ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነው … ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ” [ኤፌሶን 5፡23-32፤ ራእይ 19፡7-9]።

ጋብቻን በጅምላ በማፈጻጸም በዓለም ዙሪያ የታወቀው ከወር በፊት በ92 ዓመት ዕድሜ የሞተውና መሲሕ ነኝ እያለ ሲያታልል የኖረው ኮርያዊው ሙን ነው። ሙን፣ በአዳምና ሔዋን ኃጢአት ምክንያት የፈረሰውን ቤተሰብ ለማደስና በዓለም ላይ ሰላምን ለማምጣት፣ እኔና ባለቤቴ ተልከናል ብሏል። በዚህ አሳብቦ የተለያዩ ሴቶችን አግብቶ ወልዶ ፈቷል፤ ወጣት ሴቶችን አማግጧል። ያጋባቸው ብዙዎችም እንዳሰቡት አልሆነላቸውም። በሌላ አነጋገር፣ ሙን እንኳንስ የሌሎችን ትዳር ሊመሠርት የራሱንም አልተወጣም! በቻይና ደግሞ፣ የምዕራባውያንን ባሕል ተጽእኖ ለመግታት፣ በጥንታዊ ሃን ስርወ-መንግሥት ባሕል መሠረት የጅምላ ጋብቻ መፈጸም ተጀምሯል። በኢንዶኒዥያም ገቢአቸው ትዳር እንዳይመሠርቱ ላገዳቸው ሺህዎች ዜጎች መንግሥት ነጻ ቲኬት እያደለ ማጋባት ጀምሯል። ናይጄሪያ በካኖ ክፍለ ግዛት ባል ወይም ሚስት የሞቱባቸውና የፈቶች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ መሆኑ ያሳሰበው መንግሥት በጅምላ እየዳረ ይገኛል።

የጅምላ ጋብቻ ከሚመልሰው ይልቅ የሚያስነሳው ጥያቄ ይበዛል። ድህነት ትዳር እንዳይመሠርቱ ካገዳቸው፣ ከተጋቡስ በኋላ እንዴት ይወጡታል? እያንዳንዱ እንደ አቅሙ እንጂ እንደ ጎረቤቱ [ወይም እንደ ቴዲ አፍሮና እንደ ቀነኒሳ] ማግባት አለበት ማን አለ? በአገር ደረጃ በተቀናበረ ሠርግ ጋብቻን መፈጸም ራስን መሸንገል አይሆንም ወይ? የአቅም ማነስን ችግር ለመፍታት ከአቅም በላይ የመኖርን ችግር መፍጠር አይሆንም ወይ? ሕጋዊ ጋብቻ ሳይፈጽሙ አብረው የሚኖሩትን እንዴት ማገድ ወይም እንዲጋቡ ማስገደድ ይቻላል? ቀዳሚው ማሕበራዊ እንቅፋት ትዳር አለመመሥረት ነው ወይንስ ድህነትና ሥራ አጥነት? በብሔር መጋባት፣ ሃይማኖት ቀይጦ ወይም ሃይማኖትን ጥሎ መጋባት እውን መቻቻልን ያስገኛል?

መቻቻል ጠፍቷል ከተባለ መንስዔው ምንድነው? ሕዝቡስ እስከ ዛሬ እንዴት አብሮ ሊኖር ቻለ? በበለጸጉ አገሮችስ አለማግባት፣ ዘግይቶ ማግባትና አግብቶ አለመውለድ መስፋፋቱ ለምን ይሆን? መንግሥትና፣ መንግሥት እውቅና የሠጣቸው ድርጅቶች ቤተሰብን በማቋቋም ተግባር መሠማራታቸው ተገቢ ነው ወይ? ሪፖርተር ጋዜጣ እንዳስታወቀው፣ ድህነት ባይባባስ ኖሮ ጅምላ ጋብቻ ይታሰብ ነበር? “የሺህ ጋብቻ” አቀናባሪዎች ካቀረቡት ምክንያት አንጻር መልሱ፣ አይታሰብም ነው። ድህነት እንደሆነ ከአርባና ከሃምሳ ዓመት በፊትም የነበረ ነው። አግባብ የሚሆነው፣ ያኔ ትዳር የመሠረቱ እንዴት ተወጡት? ብሎ መጠየቅ ነበር። የመንግሥትና የንግድ ድርጅቶች ጣልቃ መግባት ይልቅ የግል ጥረትን፣ የጓደኛና የጎረቤትን የመተሳሰብና የመተጋገዝን ባሕል አዳክሞ ተመጽዋችነትን እንዳያስፋፋ ያሠጋል።

ያልጸኑ ምእመናን በሙን ትምህርትና በ“ሺህ ጋብቻ” እንዳይወሰዱ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ምን እርምጃ እየወሰደች ነው? ወይስ፣ ከአሜሪካና ከናይጄሪያ የተቀዳ የጅምላ ክርስትናና የጅምላ ጋብቻ አይጣሉም እንበል?

ጌታን ማገልገል ይወዳሉ? በዚህ ድረ-ገጽ የተለጠፉትን ጽሑፎች ለወዳጆችዎ በኢሜይል በመላክ ያገልግሉ።ምንጩ www.Ethiopianchurch.org

About Post Author

Abby

Internet reporter, freelancer and webmaster.
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 8, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 9, 2012 @ 12:33 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

About the author

Internet reporter, freelancer and webmaster.

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%

One thought on “ቅዱስ ጋብቻ ወይስ ጅምላ ጋብቻ?

  1. Can you label and give credit to the two pictures at the top? Bad practice in Ethiopian media to just put photos without a label and credit!!!

Comments are closed.

<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar