www.maledatimes.com በ40 ሚሊየን ብር ያለአግባብ ግዥ ሊጠየቁ የሚገባቸው ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነን ለሚንስትርነት ማዕረግ? - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በ40 ሚሊየን ብር ያለአግባብ ግዥ ሊጠየቁ የሚገባቸው ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነን ለሚንስትርነት ማዕረግ?

By   /   November 5, 2016  /   Comments Off on በ40 ሚሊየን ብር ያለአግባብ ግዥ ሊጠየቁ የሚገባቸው ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነን ለሚንስትርነት ማዕረግ?

    Print       Email
0 0
Read Time:7 Minute, 40 Second
ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሠራተኞች አንዷ

ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም.፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በድጋሚ ያቋቋሙትን ካቢኔ ከአንድ ዓመት ጊዜ ቆይታ በኋላ በማፍረስ እንደ አዲስ ያደራጁትን አዲስ ካቢኔ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሕዝብ አሳውቀዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካዋቀሩት ካቢኔ ውስጥ አብዛኞቹ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጡ መሆናቸው እስከ አሁን ካለው አወቃቀር ልዩ ያደርገዋል።

ከዚህ በፊት የነበረው ካቢኔ ለምን እና በምን ምክንያት እንዳፈረሱት በቂ ምክንያት ያላቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲያቸው “ጥልቅ ተሃድሶ” ብሎ ከጀመረው መንገድ አንዱ መሆኑን አንዳንዶች ይስማማሉ፤ ነገር ግን አዲስ የተቋቋው ካቢኔ ለወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ እንደማይሆን ብዙዎች ይስማማሉ፤ የሕዝቡ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ወደ ጎን ያለ እና የመፍትሔ አቅጣጫ ከመሆን በዘለለ መንግሥት እየሄደ ያለው የማደናገር አካሄድ መሆኑን ያሳያል። ለምሳሌ የቀድሞ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ከሰተ ብርሃንን የተኩት በሙያቸው የማህፀንና የፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪም የሆኑት ፕ/ር ይፍሩ ብርሃነ ከወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊነት፤ የዲላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተርነት፤ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን፤ እና በቅርቡ ተሹመው ከነበሩበት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስተዳዳሪ ነበሩ።

ፕ/ር ይፍሩ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሲመጡ፤ የሆስፒታሉን እጅግ የተንዛዛ አሠራርም ሆነ የኮሌጁን ወቅታዊ ቁመና ላይ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ታስቦ ነበር። በነበራቸው የወራት የሆስፒታሉ ቆይታ ካስተካከሉት ይልቅ ያበላሹትና ያሰቃቀሉት፤ መልክ መልክ ያላስያዙት ሥራ እጅግ ገኖ ይታያል። ፕሮፌሰሩ ለሆስፒታሉም ሆነ ለኮሌጁ ላይ የለወጡት አሠራር ቢኖር ቀድሞ በሁለት ተቋም ተከፋፍለው ሥራቸውን ሲያካሂዱ የነበሩትን ሆስፒታሉንና ኮሌጁን በአንድ ዕዝ ሰንሰለት ማስገባታቸው እንደ በጎ ጅማሬ ታይቶ ነበር፤ በተጨማሪ ሆስፒታሉ ውስጥ የነበሩትን ቢሮዎች በማጥፋት “ሆስፒታሉን ለሆስፒታል አገልግሎት ብቻ” በሚል መርኅ ቢሮ ለቢሮ በመዞር በተለያዩ ፕሮጀክቶች እና ለቢሮ ሥራ ሲያገለግሉ የነበሩትን ክፍሎች ወደሕክምና መስጫነት ለመለወጥ ያደረጉት አካሄድ በበጎ የሚታይ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በ“Office Reshuffling” ጊዜ ከሃያ ዓመታት በላይ ውሳኔ ሳይሰጥባቸው መወገድ የሚገባቸውን ንብረቶች በአጭር ጊዜ በማስወገድ ሆስፒታሉ የተሻለ ዕይታ እንዲኖረው የቻላቸውን ያህል ማድረጋቸው የሚያስመሰግናቸው በጎ ሥራዎች ናቸው።

ከዚህ በተቃራኒ ግን በርካታ የውስጥ ሠራተኞችን ከሚሠሩበት ቦታ በማመሰቃቀል፤ ቋሚ ሠራተኞች ሆነው ቦታ ስለታጣላቸው ብቻ ካለምንም አገልግሎት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በማባረር፤ ብቃት የሌላቸውን ሰዎች በዳይሬክተርነት ቦታ ላይ በመሾም፤ ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የመንግሥት ገንዘብ በማውጣት የወንበርና የጠረጴዛ ግዢ በመፈጸም፤ ቀድሞ በኮሌጁ የዲን ቦታ ላይ የተቀመጡ እና በርካታ ዘርፈ ብዙ ሥራ ለኮሌጁ ሲሠሩ የነበሩትን በኮሌጁም ሆነ በሆስፒታሉ ማኅበረሰብ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው በወር 30 ቀናት በቀን ከ12 ሰዓት በላይ ሲያገለግሉ የነበሩትን ዲን ያለበቂ ምክንያት በማባረር፤ ለቦታው የማይመጥንን ሰው የእርሳቸውን ፍልስፍና ስለሚያቀነቅን ብቻ በመሾም፤ በመረጃ ሳይሆን በወሬ ላይ በመመስረት ውሳኔ በመስጠት እና በመሰል ነገሮች ሥማቸው ይነሳል።

1. ከ40 ሚሊየን ብር በላይ የተደረገ የወንበርና የጠረጴዛ ግዥ መፈጸም

ፕ/ር ይፍሩ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሲመጡ ያደረጉት የመጀመሪያ ሥራ ቢኖር አሠራርን ከማዘመን ይልቅ፤ የሆስፒታሉም ሆነ በኮሌጅ ውስጥ የሚገኙትን ወንበርና ጠረጴዛ መቀየር ነበር። በቀን በርካታ ሰዎች ተገቢ የሕክምና አገልግሎት አግኝተው መዳን የሚችሉ ሰዎች ሕይወታቸውን እንደዋዛ በሚያጡበት ሆስፒታል ውስጥ ይህን ያህል ብር ከመንግሥት ካዝና በማውጣት ይህን ግዥ መፈጸም ብዙዎችን አግባብነቱ ላይ ጥያቄ ያጭራል። በርካታ የሕክምና ክፍሎች በቂ አልጋ ሳይኖራቸው በሽተኞች መሬት ላይ ተኝተው በሚታከሙበት ሆስፒታል ውስጥ በቀረጥ ከሕዝብ የተሰበሰበን ገንዘብ ለእንደዚህ አይነት አገልግሎት ማዋል ተገቢ ካለመሆኑ በተጨማሪ፤ በማአለብኝነት የተሠራ አሠራር መሆኑን ያመላክታል። ይህ ብር በርካታ የሕክምና መሳሪያዎችን በመግዛት፤ የነበረውን የሆስፒታል አገልግሎት አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ መሆን ይችል ነበር።

ለተማሪዎች በቂ የሕክምና መጻሕፍት በሌለበት ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ በሚኒስትር ደረጃ የእንግዶች መቀበያ የሚሆን 80 ሺህ ብር የሚያወጣ ሶፋና ወንበር ለተማሪዎች ኢንተርኔት መጠቀሚያ ማስቀመጥ እብደት ከመሆኑ በተጨማሪ፤ በየዘርፉ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተጠያቂነት የሌለው አሠራር መስፈኑን የሚያሳይ ነው። ፕሮፌሰሩ በየቢሮዎች የሚገኙትን ከተገዙ ዓመት እንኳን ያልሞላቸውን ወንበር ጠረጴዛ እንዲቀየር ሲያደርጉ፤ ሠራተኞቹ ለምን? ብለው መጠየቅ ሌላ እርምጃ የሚያስወስድ ነበር። ፕሮፌሰሩ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ አውጥተው ለላይብረሪ ወንበርና ጠረጴዛ ሲገዙ የተማሪዎችን የመጽሐፍ ፍላጎት ለማሟላት በነበራቸው የወራት ቆይታ አንድም ያደረጉት ነገር አለመኖሩ፤ ተማሪዎቹን አሮጌ መጻሕፍቶችን በአዲስ ወንበር ተቀምጠው እንዲያነቡ አስገድዷቸዋል። ይህ አይነት አሠራር ከተዛባ ዕይታ የሚነሳ፤ ቀድሞ ምን መደረግ እንዳለበት አለመገንዘብ እና የታይታ ሥራ ከመውደድ የሚመነጭ ነው።

ይህን ያህል ብር ለገጠሪቱ ድሃ አርሶአደሮች ማኅበረሰብ ክፍል ምን ያህል ጤና ጣቢያ፤ ምን ያህል አምቡላንስ እና ምን ያህል የሕክምና መገልገያ እቃዎችን እንደሚገዛ ሲታሰብ ድርጊቱ እጅግ ከማሳዘንም ባለፈ ያሳፍራል። መንግሥት እንዲ አይነት ኃላፊነት የማይሰማቸው የማያገናዝቡ ሰዎችን በመመዘን የሕዝብ ሀብት ያለአግባብ እንዳይወጣ የማድረግ ኃላፊነት ይኖርበታል። መንግሥት ከሕዝብ የሚሰበስበውን ግብር በአግባቡ ለታሰበለት አላማ በማዋል በተለያዩ ኃላፊዎች የሚደረግን የሀብት ብክነት ሊቆጣጠር ይገባል።

አሁን ቢሆን የዚህ የወንበርና የጠረጴዛ ግዥ አግባብነትና ላይ አሁን ያሉት ኃላፊዎችም ሆነ ፕሮፌሰሩ ሊጠየቁ ይገባል።

2. ሠራተኞችን ያለበቂ ምክንያት ከሥራ ገበታቸው ላይ ማባረር/ማንሳት

ፕሮፌሰሩ ሆስፒታሉንና ኮሌጁን አንድ በሚያደርጉበት ወቅት ያለ ግልጽነት እና ተጠያቂነት በሌለበት አሠራር በርካቶችን ከሥራ ገበታቸው ላይ ዝቅ ብለው እንዲሠሩ አድርገዋል። ሲብስም በጋርዮሽ የአስተዳደር እሳቤያቸው አንድ ላይ አብዮታዊ እርምጃ የተወሰደባቸው ሰዎች ብዙዎች ናቸው። ቀድሞ የኮሌጁ ዲን የነበሩትን ሰው፤ መቶ በመቶ የኮሌጁም ሆነ የሆስፒታሉ ማኅበረሰብ እኩል ድምጽ የሚሰጣቸው፤ እጅግ ሥራ ወዳድ እና የተማሪም ሆነ የሠራተኛውን ችግር ለመፍታት ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉ ሰውን በአንድ ደብዳቤ ከ10 ዓመት በላይ ካገለገሉበት ዩኒቨርሲቲ ከአመራርነት የማባረር ሥራ ሠርተዋል። ይህም ተግባራቸው እስከ አሁን ድረስ ማንንም ያላስደሰተ ተግባር ነበር። ፕሮፌሰሩ ሠራተኛ ማባረር ከማብዛታቸው የተነሳ ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አድማሱ ከአሁን በኋላ ምንም አይነት ሠራተኛ እንዳያባርሩ ማሳሰቢያ ተሰቷቸው ነበር። ፕሮፌሰሩ ለጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት እስከተሸሙበት ጥቅምት 22 ቀን ድረስ ሠራተኞችን ከፍና ዝቅ የማድረግ ሥራ ተጠናውቷቸው ነበር። በአሁኑ ሰዓት ያለአግባብ የተነሱ በርካታ ሠራተኞች ጉዳያቸውን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ እየተሟገቱ ይገኛሉ።

ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነን

ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነን

በመሰረቱ አንድ ተቋም የተሰጠውን አላማ ከግብ ለማድረስ የባለሙያዎች አስቷጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ይታወቃል፤ ነገር ግን ሠራተኛን በጥናት ላይ የተመሰረተ ምደባ በማድረግ አንድም የሠራተኛን መብት አክብሮ ተቋማዊ ግብንም ማሳካት ይቻል ነበር። የፕሮፌሰሩ አካሄድ ግን ከዚህ በጣም የራቀ እና አስተዳደራዊ ፍልስፍና ያልነካው መሆኑ እጅጉን ያስወቅሳቸዋል።

3. የተማሪዎችን የኮምፒዩተር መጠቀሚያ ክፍል የመዝጋት ሥራ

ኮሌጁ እንደ ኮሌጅ እንዲቀጥል የተማሪዎች ኤሌክትሮኒክ መጠቀሚያ ላይብረሪ ወሳኝነቱ አያጠያይቅም። በአሁኑ ሰዓት ብዙ ተማሪዎች ላፕቶፕ ተጠቃሚ የሆኑትን ያህል፤ ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ የተገኙ የዝቅተኛ ቤተሰብ ልጆችም ቀላል ቁጥር አይዙም፤ ቀድሞ ተማሪዎች ሲጠቀሙበት የነበረው በርካታ ኮምፒዩተሮችን የያዘው ኮምፒዩተር ክፍል በአሁኑ ወቅት ከተዘጋ እና ከአገልግሎት ውጪ ከሆነ ሦስት ወራቶች አስቆጥረዋል። ይህም እሳቸው የሚመሩት ከፍተኛ ማኔጅመንት ለነገሮች ያለው ንዝህላልነትን የሚያመላክት ነው። ይባስ ብለው ፕሮፌሰሩ በአንድ ወቅት “ይህን ክፍል ከዚህ አንስተን ወደ ሌላ ቦታ እንወስደዋለን” በማለን በሚሊየን የሚቆጠር ሀብት የፈሰሰበትን ክፍል እንደ ተራ ነገር በመቁጠር ተናገረው ነበር።

4. የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ ሰዎች መከበብ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ በሹመት ቀን “የትምህርት ዘርፍና በአመራር ዘርፍ በመሰማራት በጤና ልማትና ምርምር ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ፤ በቅርቡ በተመደቡበት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና ጤና ሳይንስ ኃላፊነት ጉልህ ውጤት ማምጣት የጀመሩ” በማለት ስላልተመዘነው ሥራቸው መስክረውላቸዋል። መንግሥት እኚህን ሰው ወደ ሚኒስትርነት ማዕረግ ከማምጣቱ በፊት ያገለገሉበትን መስሪያ ቤት ሠራተኞች፤ የቀድሞ እና የአሁን አመራሮችና ተማሪዎች ጋር በመውረድ የዳሰሳ ጥናት በጥቂቱ ቢያካሄድ መልካም ነበር። በመሰረቱ ፕሮፌሰሩ የመሥራት ፍላጎት እና የመሥራት አቅም ቢኖራቸውም፤ የሚሄዱበት አካሄድ ግን ተቋምን ከማዘመን ይልቅ ቁልቁል እንደሚወስድ፤ ብዙ ነገሮችን እንደሚያመሰቃቅል የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተሞክሮን ባለማየት ለጤና ጥበቃ ሚኒስትር አድርጎ መሾም እጅግ ከመግረምም የተነሳ ያሳዝናል።

ፕሮፌሰሩ በዙሪያቸው የከበቧቸው ሰዎች መንግሥት ከተከለው ደመወዝ በላይ ከሦስትና ከአራት እጥፍ በላይ ለማካበት የተሰገሰጉ ናቸው፤ በወር እስከ 76ሺህ የኢትዮጵያ ብር ከተለያዩ ፕሮጀክቶች በመሰብሰብ የግል ጥቅማቸውን የሚያባርሩ ሰዎች ጥላ ከለላ አድርገው ሰውየውን ከበዋቸዋል። አሁንም ይህን አይነት አሠራር ጤና ጥበቃ ይዘው የሚሄዱ ከሆነ ተቋሙን ለከፋ ውድቀት የሚጋብዙት መሆኑን መንግሥት ሊረዳው ይገባል።

5. ያልተገባ ቦታ መገኝት

ፕሮፌሰሩ በሺህ የሚቀጠር ሠራተኛን በአግባቡ እንዲያስተዳድሩ ትልቅ ኃላፊነት ተሰቷቸው ከውጭ የመጡ እንግዶች እሳቸውን ለማነጋገር ቢሮ በሚጠብቋቸው ሰዓት እሳቸው በየሽንት ቤቱ እየዞሩ የተከፈተን ቧንቧ መዝጋት፤ ከውጭ የመጣን እቃ እንደ ግምዣ ቤት ኃላፊ ቆሞ ማስወረድ፤ በየቢሮ እየዞሩ ሠራተኞችን ክፍሉን እንዲለቁ ማድረግ፤ ቆሻሻ ማጸዳት፤ ቀለም ማስቀባት፤ ኮርኒስ ማሠራት፤ የሚወገዱ እቃዎች ማስቆጠር እና ለኤክሲኩቲቭ ዳይሬክተር የማይሠራውን ሥራ በመሥራት ዋና ጊዜያቸውን ያባክኑ ነበር።

በአንድ ወቅት ፕሮፌሰሩ የግል መኪናቸውን አቁመው ቢሮ ገብተው እስኪወጡ ድረስ የመኪናው ስፖኪዮ ከቦታው ላይ በማጣታቸው ደብዳቤ በመጻፍ የጥበቃ አባላቱን 1000 ብር ከማይደርሰው ደመወዛቸው ተቆርጦ የጠፋው ስፖኪዮ ከሰባት ሺህ ብር በላይ በማውጣት እንዲገዙ ማድረጋቸው ግርምት የፈጠረ ነገር ነበር። በቁጥር ለመቁጠር የሚያዳግት የሕክምና መሳሪያ ሲሰረቅ ቁጥጥር የማይደረግበት ሆስፒታል፤ የአንድን ኃላፊ የመኪና ስፖኪዮ ሲጠፋ አስተዳደራዊ እርምጃ ብሎ ይህን ማድረግ መቻል ብዙዎች እንዲገረሙ አድርጓል።

6. ሆስፒታሉ ግማሽ ክፍሉ እንዲፈርስ የማድረግ ውሳኔ

ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በርካታ የሕክምና አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ታስቦ በወቅቱ በነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቡ የአንድ ብር መዋጮ ከተሠራ 50 ዓመት አልፎታል፤ ይህ ሆስፒታል ያለውን ይዞታ ይዞ እንዲቆይ ማድረግ ይገባል፤ በፕሮፌሰሩ የወራት የሆስፒታሉ ቆይታ ግን የሆስፒታሉ የፊት ለፊት አካል እንዲፈርስ ውሳኔ ተሰጥቶበት ክፍሎች እንዲለቁ እያደረጉ ይገኛሉ። ይህም ትልቅ ሕንጻን በቦታው ላይ ለመሥራት በማሰብ ነበር፤ ነገር ግን ቅርስ ሊሆን የሚችልን ተቋም እያፈረሱ በመስታወት የተቀባ ሕንጻን መሥራት ዘመናዊነትን አያሳይም። አሁንም መንግሥትም ሆነ የኮሌጁ አስተዳደር የሆስፒታሉን አንድ ክንፍ ከማፍረስ እንዲታደጉት በፕሮፌሰሩ የተወሰነውን ውሳኔ ዳግም መጤን ይገባዋል።

ፕሮፌሰሩ የሚወስኑት ውሳኔ ቅጽታዊ ከመሆኑ በተጨማሪ የውሳኔው ትርፍና ኪሳራ በአግባቡ ሳያጤኑ ስለሚወስኑ ተቋሙን ያላስፈላጊ ዋጋ አስከፍሎታል፤ ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም የሚለው እሳቤ እሳቸው ጋር አይሠራም። ሮምን በአንድ ቀን ለመገንባት በቅጡ ያልተመከረበት ውሳኔን ሲወስኑ ይታያል። ይህን አይነት አካሄድ ደግሞ እያደር ከሚያመጣው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ እጅጉን ያመዝናል፤ ሠራተኞችን ለማንሳት ሲፈልጉ ቀጣይ ስለሚኖራቸው ቦታ ብዙም አያሳስባቸውም፤ ካነሷቸው በኋላ ቦታ ካለ ይሰጣሉ ያለበለዚያ ደግሞ ያባርራሉ። ሠራተኞች አስር ዓመት ተቀምጠው ከሚሠሩበት ቢሮ በአንዲት ቀን ተነስተው እንዲወጡ ይፈልጋሉ … ሌላም ሌላም …

በመጨረሻም

ፕሮፌሰር ይፍሩ በግላቸው በርካታ ጽሁፎችን ቢጽፉም፤ ግለሰባዊ ጥንካሬያቸውን ያሳያል እንጂ ጤና ጥበቃን የሚያክል መንግሥት ለአገሪቱ ከሚመድበው በጀት በላይ ከውጭ ተራድኦ ድርጅቶች የሚያገኝን እና ወደ ሥራ የሚቀይርን ተቋም የማስተዳደር አቅም አላቸው ማለት አይደልም። በአካዳሚክ እውቀት እና ተቋምንና ሕዝብን የማስተዳደር ክህሎት እጅግ የተራራቁ መሆናቸውን መንግሥት ሊረዳ ይገባል። አንድን ተቋም ለማስተዳደር በአካዳሚክ እውቀት መሰረታዊ ቢሆንም፤ የግለሰቡ አስተዳደራዊ ፍልስፍናው እና የሠራቸው ሥራዎች ሚዛን ላይ መቀመጥ ይኖርባቸዋል። አሁንም በዶ/ር ከሰተ ብርሃን ያዋቀሩትን የጤና ጥበቃን የበላይ አመራር እንዳልነበረ አድርገው አፈር እንደሚያበሉት፤ የሚሠራውን ከማይሠራው ጋር ደባልቀው እንደሚያባሩ ዝቅና ከፍ እንደሚያደርጉ እሙን ነው። ሲከተሏው የነበሩትን ሰዎች አስከትለው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደሚሰገስጉ እርግጥ ነው።

እኚህ ሰው ባልተመዘኑበት ሥራቸው ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሹመታቸው እንደተሳማ በሰዓታት ውስጥ በጥቂት የበላይ ወዳጆቻቸው እና በአጨብጫቢዎቻቸው አማካኝነት በኮሌጁ የስብሰባ አደራሽ “Congratulations!” በማለት ሽኝት ተደርጎላቸዋል። እሳቸው እጅጉን በብዙ ነገር ያመሰቃቀሉትን ተቋም “ከጎናችሁ ነኝ” በማለት ቃል ገብተዋል። አዲሱን ጤና ጥበቃን ለማመሰቃቀል ለውጥ የሚመስልን፤ ነገር ግን ለውጥ ያልሆነን ሥራ ለመሥራት የዶ/ር ከሰተን ወንበር ተረክበዋል። ውጤቱን ወደፊት የምናየው ይሆናል።

ቸር ሰንብቱ!
የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሠራተኛ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 7 years ago on November 5, 2016
  • By:
  • Last Modified: November 5, 2016 @ 7:25 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar