ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ የመገናኛና ኢንፎሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የታላቁ ህዳሴ ብሔራዊ ምክር ቤት ቦርድ አባል

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ እንዲጀመር የመሠረት ድንጋይ በይፋ የተጣለበት ስድስተኛ ዓመት ሊደፍን ጥቂት ቀናት ብቻ ይቀራሉ፡፡ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ አቅም በአፍሪካ ትልቁ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ 10 ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች መካከል አንዱ መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ከራሷ በሚፈልቀው የዓባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የቆየውን የግብፅ ብቸኛ ተጠቃሚነትንና ኃያልነትን የሰበረ መሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋል፡፡ ይህ አገራዊ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የውኃ ሀብታቸው ያለ ጥቅም ለዘመናት ሲፈስ እያዩ ምንም ማድረግ ላልቻሉ የናይል ወንዝ ተጋሪ አገሮች ጭምር መሆኑም እየተነገረለት ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን ስድስተኛ ዓመት መቃረብ አስመልክቶ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ምክር ቤት ቦርድ አባልና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የካቲት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ መግለጫውን የተከታተለው ዮሐንስ አንበርብር የህዳሴውን ግድብ ግንባታና ሌሎች የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በተመለከተ ከዶ/ር ደብረ ጽዮን ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡

ሪፖርተር፡– ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሲበሰርና የመሠረት ድንጋዩ በይፋ ሲቀመጥ ከፍተኛ ብሔራዊ አንድነት የታየበት መነሳሳት ተስተውሏል፡፡ የነበረውን ብሔራዊ አንድነትና መነሳሳት አሁን ላይ እንዴት ይገመግሙታል? የግድቡ ግንባታ ያለፉት ስድስት ዓመታት ጉዞ ምን ይመስላል? ያጋጠሙ ፈተናዎችስ ምን ነበሩ?

ዶ/ር ደብረ ጽዮን፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጅምሩ አንስቶ ኅብረተሰቡን ያስተሳሰረ ነው፡፡ አሁንም በአንድነት አስተሳስሮ እየቀጠለ ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡ በፋይናንስ ድጋፍም በመንፈስም ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው፡፡ የፀጥታ ችግሮችና ፈተናዎች በነበሩባቸው አካባቢዎች ጭምር የህዳሴው ግድብ በኅብረተሰቡ አስተሳሰብ ላይ ቀዳሚ ሥፍራ የተሰጠው፣ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ላይ ኃያል ሥፍራ የያዘ መሆኑን ዛሬም እያየን ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት ነው እንዳልነው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እጁን ያሳረፈበት ነው፡፡ ከአስተሳሰቡ ጀምሮ በላቡና በገንዘቡ ዜጋውን ያሳተፈ ነው፡፡ የሁሉም ክልሎች አባላት ሠራተኞች እየተሳተፉበት ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች የበጀት ድጎማ ቀመር እንደሚያዘጋጀው፣ እያንዳንዱ ክልል የሕዝብ ብዛቱን መሠረት በማድረግ ለግድቡ ግንባታ የሚያዋጣው የሰው ኃይል ድርሻ ተከፋፍሎ ነው የሰው ኃይል ቅጥር የሚፈጸመው፡፡ የሚከፈል መስዋዕትነትም ካለ እንደዚያው፡፡ ኢትዮጵያን በሚያንፀባርቅ ገጽታ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት ነው፡፡ የግድቡ ግንባታ በጥር ወር ላይ በተመዘገበ መረጃ መሠረት 56 በመቶ ደርሷል፡፡  ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ይኼ ነው የሚባል ችግር ገጠመን ማለት አንችልም፡፡ ሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን የሚታለፉ ናቸው፡፡ ሥራውን የሚፈታተንና ችግር ላይ የሚጥል ፈተና አልገጠመንም፡፡ እዚያው ላይ የሚፈቱና ተሠርተው የሚለወጡ ችግሮች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የሚገመት ነው፡፡ ምክንያቱም ግዙፍ ሥራ ነው፡፡ ለዚህም ነው በጥሩ ሁኔታ እየቀጠለ ነው የምንለው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት አገራዊ ችግር መሆኑን መንግሥት እየገለጸ ነው፡፡ የግድቡ ግንባታስ የውጭ ምንዛሪ ፈተናውን እንዴት እየተቋቋመ ነው?

ዶ/ር ደብረ ጽዮን፡- የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ተፅዕኖ በአገር አቀፍ ደረጃ አለ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ግድብ ቅድሚያ ነው የሚሰጠው፡፡ ያለ ምንም መወላወል መንግሥት ያለውን የውጭ ምንዛሪ ሲደለድል ቁጥር አንድ የሚያስቀምጠው ታላቁ ህዳሴ ግድብን ነው፡፡ ከሁሉም ሥራዎቻችን ቁጥር አንድ ተብሎ የተለየውና የውጭ ምንዛሪ ምደባ ቅድሚያ የሚያገኘው ይኼ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይኼ የመንግሥት ውሳኔ ነው፡፡ ይህንን ውሳኔ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ባንኮችም ሆኑ ሌሎችም የሚመለከታቸው በተጠየቁት መሠረት ሥርዓቶቹን አሟልተው ለህዳሴው ግድብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጊቤ ሦስትን በቅርቡ ስላጠናቀቅን ነው እንጂ በውጭ ምንዛሪ ምደባ ቁጥር ሁለት ቅድሚያ የተሰጠው ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ወደ ኤክስፖርት ዘርፍና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች እያለ የሚመደበው፡፡ ስለዚህ ያለንን የውጭ ምንዛሪ ለግድቡ ነው ቅድሚያ የምንጠቀመው፡፡ ለዚህም ነው የግድቡ ግንባታ የፋይናንስ ችግር የለበትም የምንለው፡፡

ሪፖርተር፡የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የግድቡ ግንባታ የኤሌክትሮ መካኒካል ኮንትራት ወስዶ እንዲሳተፍ መደረጉን አስመልክቶ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ይህንን ግዙፍ ኃላፊነት የመወጣት አቅም ኮርፖሬሽኑ የለውም በማለት የሚጠይቁ አሉ፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ደብረ ጽዮን፡- ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ላይ በዋና ኮንትራክተርነት እንዲሳተፍ መንግሥት የወሰነው በፖለቲካዊ ምክንያቶች ነው፡፡ ይህ ይሁን እንጂ ካሰብነው በላይ የውጭ አማካሪ ኩባንያዎችም ቀደም ሲል የነበራቸውን ፍርኃትና ጥርጣሬ አስወግዶ ያስደመመ ሥራና ውጤት እያስመዘገበ የሚገኝ አገራዊ አቅም ሆኖ ወጥቷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ሥራዎች ግማሽ የሚሆነውን የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች ኃላፊነት ነው እንዲወስድ የተደረገው፡፡ ውሳኔውን መንግሥት ያሳለፈው ቀደም ብዬ እንዳልኩት ፖለቲካዊ በሆኑ ምክንያቶች ነው፡፡ የውሳኔው መነሻ በኮርፖሬሽኑ ምትክ የውጭ ኩባንያዎች ኃላፊነቱን ቢወስዱ ብዙ ፈተናዎች ይገጥሙናል የሚል ነበር፡፡ አንዱ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎች ላይ ከተንጠለጠልን በጫና ጥለውን ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ቢቻል ሁሉንም በራሳችን እንሥራው የሚል መርህ ነበር፡፡ ሁሉንም ሥራዎች በራሳችን ብናከናውን ገንዘቡንና ጫናውን ብቻ ሳይሆን፣ ግንባታው የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሪ እንቀንሳለን የሚል መነሻ ነበር፡፡ የራሳችንን አቅም ብናስገባ የምናወጣውን የውጭ ምንዛሪ እንቀንሳለን በሚል ወደፊት ለሚገጥመው ችግር የመፍትሔ ውሳኔ ነው ከጅምሩ የወሰድነው፡፡ በዲፕሎማሲያዊ ጫና ኮንትራቱን የሚወስዱ ኩባንያዎችን የማስወጣት ዘመቻ እንደሚካሄድ አስቀድሞ ተገምቷል፡፡ ተመሳሳይ ጫና በጊቤ ሦስት ላይ ገጥሞናል፡፡ ገንዘብም እንዳናገኝ የውጭ የሲቪክ ተቋማት (NGOs) ተንቀሳቅሰው አስተጓጉለውብናል፡፡ ድጋፍም መስጠት የፈለጉም ትተውታል፡፡ እንደ አዲስ ነው መንግሥት ተንቀሳቅሶ ጊቤ ሦስትን መጨረስ የቻለው፡፡ በዚህ ምክንያት ጊቤ ሦስት መጠናቀቅ ከነበረበት ሁለት ዓመት ዘግይቷል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግን በውጭ ተፅዕኖ መጫወቻ መሆን አይችልም ብቻ ሳይሆን መጋለጥም የለበትም፡፡ ለዚህ መፍትሔው የራሳችንን አቅም ማስገባት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን ለመቀነስ የራሱ ትርጉም አለው፡፡ እንዲሁም ለውጭ ተፅዕኖ እንዳንጋለጥና ግንባታው እንዳይስተጓጎል (እንዳይቆም) በሚል የተወሰነ ነው፡፡ ይህ ጫና ግንባታው ከተጀመረ በኋላ ተሞክሯል፡፡ ሲቪል ኮንትራቱን የወሰደው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ለቆ እንዲወጣ ጫና ደርሶበታል፡፡ በተለያየ አግባብ ነበር ጫናው የተሰነዘረው፡፡ በአውሮፓ ኅብረት በኩል፣ እንዲሁም በጣሊያን መንግሥትም በኩል ጫና ለማሳደር ሞክረዋል፡፡ ኩባንያውም ሙከራውን ተገንዝቧል፡፡ ነገር ግን ይህ ኩባንያ በኢትዮጵያ ብዙ ዓመታት የቆየ በመሆኑና ኢትዮጵያን በደንብ ስለሚያውቅ ነው የተቋቋመው፡፡ ሌላ ኩባንያ ቢሆን ኖሮ ምን ይፈጠር ነበር? የሠጋነው ነገር ያለምንም ጥያቄ ይገጥመን ነበር፡፡ ሁለት ሦስት ኩባንያ ቢሆኑስ፣ አንዱ ወይም ሁለቱ ሊሄዱ ይችሉ ነበር፡፡ እዚያ የምታገኘው አንድ ቢሊዮን ከሆነ እኔ እሰጥሃለሁ በማለት ተደራድረው ሊያስወጧቸው ይችላሉ፡፡ ትርፉን ጨምረው ከፍለው፡፡ ስለዚህ የአደጋ ተጋላጭነቱን የቀነስንበት አንዱ መንገድ የራሳችንን አቅም በማስገባት ነው፡፡ አደጋው ታይቷል፡፡ ጫናውን ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን አንድ ኩባንያ ብቻ ስለሆነና ይህንንም ኩባንያ መንግሥት አምኖበትና የተሻለ ብሎ ስላስገባው ዘልቀናል፡፡ የፋይናንስ ጫናም ቀንሰናል፡፡ የቴክኖሎጂ አቅምም ፈጥረናል፡፡ በፊት ያልሠራነውን በዚህ ግድብ እንሥራ ብለን ነው እንደ መንግሥት የገባነው፡፡ አንድ አገር ቀጣይ ዕድገትን የሚያረጋግጠው አስተማማኝ የሆነ የቴክኖሎጂ አቅም ሲኖረው ነው፡፡ ነፃ ነን ማለት የሚችለው በራሱ መሥራት ሲችል ነው፡፡ ገንዘብ ኖሮ የውጭ ኩባንያ እያስመጡ መሥራት ራስን መቻል ማለት አይደለም፡፡

ስለዚህ በዚህ ፈታኝ ፕሮጀክት የአገር ውስጥ ኩባንያ አስገብተን ግድቡን እየገነባን፣ አቅማችንን መገንባት ችለናል፡፡ ብዙ ርቀት ሳንሄድም ውጤቱን በመጀመሪያው ዓመት ማየት ችለናል፡፡ እንደምታውቁት 5,200 ሜታ ዋት የነበረው የግድቡ የማመንጨት አቅም ወደ 6,000 ሜጋ ዋት የተሸጋገረው በአገር አቅም ነው፡፡ በኮርፖሬሽኑ ነው ማለቴ ነው፡፡ በአገር አቅም ስንል ግን ብቻውን ነው ማለት አይደለም፡፡ የራሱ አቅም አለው፣ ነገር ግን የሚጎላውን የውጭ ሙያተኞችንና ኩባንያዎችን ተጠቅሞ እያካካሰ ነው፡፡ ልምድ ሳይኖረው ይሞክር ተብሎ የገባ ተቋምም አይደለም፡፡ አሁን አጠቃላይ የግድቡ የማመንጨት አቅም ወደ 6,450 ሜጋ ዋት አድጓል፡፡ ስለዚህ አሁን ባለበት ደረጃ 1,150 ሜጋ ዋት ጨምረናል፡፡ መጀመሪያ ወስነን ከገባን በኋላ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ተከዜ፣ በለስ፣ ጊቤ ሁለት ተደምረው ከሚያመነጩት በላይ ማለት ነው፡፡ ይህ በአገራዊ አቅም የመጣ ነው፡፡ አሁንም የበለጠ ለማሳደግ ተጨማሪ ተስፋ አለ፡፡ ነገር ግን ብዙ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኮርፖሬሽኑ መማር ብቻ ሳይሆን እየተማረ እየሠራ ተጨማሪ የማመንጨት አቅም እንዲኖርም አስችሎናል፡፡ ስለዚህ ውጤቱን አይተነዋል፡፡ ለችግር መፍትሔ ብለን ያስገባነው የአገር ውስጥ ኩባንያ ተደራራቢ ጥቅሞችን እየሰጠን ነው፡፡ ይህንን ውጤት ሲያስመዘግብ ተጨማሪ ኃይል እንጂ ተጨማሪ ወጪ አልወጣም፡፡ ስለዚህ እርካታው ብዙ ነው፡፡ ወጪው መጀመሪያ ግድቡ ሲጀመር የነበረበት አካባቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡በመጀመሪው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የመጀመሪያ ዙር ኃይል እንደሚያመነጭ ተነግሮ ነበር፡፡ አሁን ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ላይ ነን፡፡ መቼ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል?

ዶ/ር ደብረ ጽዮን፡- አስቀድመን የተወሰነ ኃይል እናመንጭ የሚል እሳቤ ነበር፡፡ ገና የግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅም 5,200 ሜጋ ዋት በነበረበት ጊዜ፡፡ ማመንጨት ይጀምራል እንጂ ግድቡ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ይጠናቀቃል ማለት አይደለም፡፡ የመጀመሪያው ዓመት ሥራ የኮንትራትና ዲዛይን ሥራዎችን እንጨርስ በሚለው ላይ ትረኩት ሰጥተን ነው የሠራነው፡፡ ከ5,200 ሜጋ ዋት ወደ 6,000 ሜጋ ዋት ማሳደግ የተቻለው በመጀመሪያው ዓመት ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ዲዛይኑን በየጊዜው የምንቀይር ከሆነ የትኛዎቹም አገሮች ጥያቄ ያነሱብናል፡፡ ትንሽ አስበን ባንሠራ ኖሮ መሥራት እንችል ነበር የሚል ቅሬታ ውስጥ ነበር የምንገባው፡፡ ስለዚህ አንዱን ዓመት ሙሉ ለዲዛይን ብቻ ነው ትኩረት የሰጠነው፡፡ የማመንጨት አቅሙ ከ5,200 ሜጋ ዋት ወደ 6,000 ሜጋ ዋት እንዲያድግ ሲደረግ፣ በሲቪል ሥራው ዲዛይን ላይም ማሻሻያ አድርገናል፡፡ መጀመሪያ ላይ የነበሩትን 15 ተርባይኖች ወደ 16 ስላሳደግን የግድቡ ዲዛይን እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ አንድ ተጨማሪ ተርባይን እንዲይዝ ለማድረግ የግድቡ ጎን እንዲሰፋ ተደርጓል ማለት ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ተራራ መግፋት ግድ ብሎናል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሥራዎች ስናከናውን በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ለማመንጨት ያቀድነውን መፈጸም አንችልም ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ሥራው ተቀይሯል፡፡

ስለዚህ እንደማይሆን እናውቃለን ማለት ነው፡፡ ቀሪው የኃይል ማመንጨት አቅም የተፈጠረው በጄኔሬተሮች ላይ በተደረጉ የማሻሻያ ሥራዎች ነው፡፡ ሁለቱ ተርባይኖች ግን በቀድሞው ዲዛይን ነው እንዲቀጥሉ የተደረጉት፡፡ ሌሎቹ እያንዳንዳቸው 410 ሜጋ ዋት እንዲያመነጩ ማሻሻያ ሲደረግባቸው፣ ሁለቱ ጄነሬተሮች ግን በቀድሞው ዲዛይን እንዲቀሩ በመደረጉ እያንዳንዳቸው 375 ሜጋ ዋት ነው የሚያመነጩት፡፡ መቼ እንደምናመነጭ እናውቀዋለን፡፡ ነገር ግን ኃይል የማንጨት ሥራ ከታችኛው አገሮች ጋር በመመካከር የምናደርገው ነው፡፡ የብቻችን ሥራ ነው ብለን አንወስድም፡፡ ምክንያቱም ስምምነት አለን፡፡ ግድቡን በስንት ዓመት በውኃ እንሙላው በሚለው ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ የተጀመሩ ጥናቶች አሉ፡፡ ገና በሒደት ላይ ናቸው፡፡ እኛ ግን ውኃውን ሙሉ ለሙሉ መያዝ የምንችልበት የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ቀደም ብዬ ሁለቱ ተርባይኖች ላይ ማሻሻያ አልተደረገም ያልኩት ቀድመው ማመንጨት እንዲጀምሩ ነው፡፡ እነሱ ዝግጁ ናቸው፡፡ የመገጣጠም ሥራ ነው የሚቀራቸው፡፡ ውኃ ለመያዝ የሚያስችሉን ምክክር የማይጠይቁ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ እነሱን እያፈጠንን ነው አሁን እየሠራን ያለነው፡፡ የመጀመሪያውን ኃይል ለማንጨት የሚያስፈልግ ውኃ ለመያዝ የሚያስችለን ሥራ ነው እየሠራን ያለው፡፡ ሌላው ሥራ እንዳለ ሆኖ ዋናው ቁልፍ ሥራ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉን የመጨረሻ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ ዋናው የውኃ ሙሌት ግን ምክክር የሚያስፈልገው ነው፡፡

ዋነኛው ፈተና ከታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ጋር ስምምነት የሚጠይቀው አጠቃላይ ግድቡን በውኃ የመሙላት ሒደት ነው፡፡ በስንት ዓመታት ውስጥ ቢሞላ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት አያደርስም የሚለው በባለሙያዎች የተደገፈ ስምምነት ያስፈልገዋል፡፡ ጥናቱን እንዲያከናውኑ የተቀጠሩት ሁለት ገለልተኛ አማካሪ ኩባንያዎች ጥናታቸውን ለመጀመር በአሁኑ ወቅት ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት እኛ ሥራችንን እንቀጥላለን፡፡ አሁን ያለንበት ደረጃ ቅድሚያ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል የመጨረሻ ዝግጀት ላይ ነን፡፡ ቅድሚያ ኃይል ማንጨት የሚጀምሩት ሁለት ተርባይኖችን ወደ መሥራት ለማስገባት ውኃ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ የሚያስፈልገውን ውኃ ለመያዝም የመጨረሻውን ዝግጅት በማድረግ ላይ እንገኛን፡፡ ለሁለቱ የሚያስፈልገው ውኃ በጣም አነስተኛ ስለሆነ በቀላሉ ተግባብቶ መሥራት ይቻላል፡፡ አጠቃላይ  ተርባይኖቹን (16) ሥራ ለማስጀመር የሚያስፈልገው ውኃ ትልቅ ሐይቅ እንደ ማለት ነው፡፡ ከግብፅ የአስዋን ግድብ የሚበልጥ ነው፡፡ ጥንቃቄና ተነጋግሮ መግባባት የሚያስፈልገው ሥራ ነው፡፡ ሁለቱ ተርባይኖች ቅድሚያ ኃይል እንደሚያመነጩ የሚያስፈልገውን ውኃ በተመለከተ ግን ብዙ ችግርና ጫና የሚፈጥር አይደለም፡፡ መነጋገር ስላለብን ካልሆነ በስተቀር ጫና የሚፈጥር አይደለም፡፡ በቀላሉ ተግባብተን ልንሠራው የምንችለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወጪ ወዳሉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ልውሰድዎት፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን 17 ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ታቅዶ ፕሮጀክቶቹ ተቀርፀዋል፡፡ ዕቅዱ የተለጠጠ ይመስላል፡፡ የመሳካት ዕድሉን እርስዎ እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር ደብረ ጽዮን፡- የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት እንደሚታወቀው ከፍተኛ ነው፡፡ በየጊዜውም እየጨመረ ነው ያለው፡፡ እንደሚታወቀው በኤሌክትሪክ አቅርቦት ረገድ ብዙ ችግሮች አሉብን፡፡ ዋናው ወቅታዊ ችግር ከኃይል አቅርቦት ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ ከሥርጭትና ከሰብ ስቴሽኖች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በቴሌኮም ዘርፉ እንደተደረገው የኃይል አቅርቦት መሠረተ ልማቱ ተጠራርጎ እንደ አዲስ መሠራት አለበት፡፡ ቀውሱን የፈጠረው መሠረተ ልማቱ ስለሆነ፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ኃይል ማመንጨቱ መቀጠል አለበት፡፡ አሁን ችግር ባይሆንም ወደፊት ችግር መሆኑ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም የአገሪቱ ፍላጎት እየጨመረ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ መፍትሔው በርካታ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ማልማት አለብን፡፡ በመሆኑም 17,326 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ታቅዷል፡፡ ይህ የተቀረፀው በዓለም አቀፍ ደረጃ መካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላቸው አገሮች ኃይል የማንጨት አቅም ላይ መድረስ አለብን የሚል ግብ ተጥሎ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ባለንት ደረጃ መካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ካላቸው አንዳንድ አገሮች እኛ እንሻላለን፡፡ ይኼም ማለት በመካከለኛ ደረጃ ያለ አንድ አገር የነፍስ ወከፍ የኃይል ፍጆታን መሠረት አድርጎ ሲሰላ ከተቀመጠው የነፍስ ወከፍ ፍጆታ የእኛ የተሻለ ነው፡፡ ነገር ግን የነፍስ ወከፍ ፍጆታ እውነታውን አይገልጽም፡፡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሁንም የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ ስለዚህ በመካከለኛ ገቢ ሆኖ ምርጥ የሆነው ደረጃ ላይ ነው ለመድረስ ግብ የጣልነው፡፡ ስለዚህ መካለኛ ገቢ ለመድረስ ነው ዕቅዳችን፡፡ መካከለኛ ገቢ ለመድረስ የአሥር ዓመታት ጊዜ ነው የተቀመጠው፡፡ ነገር ግን የኃይል አቅርቦቱ ቀድሞ በአምስት ዓመት ውስጥ መድረስ አለበት ተብሎ ነው ግቡ የተጣለው፡፡ ከኢኮኖሚው ቀድሞ የኃይል አቅርቦቱ መምጣት አለበት፡፡ በእርግጥ ዕቅዱ የተለጠጠ ቢሆንም አብዛኞቹን ዕውን ማድረግ እንችላለን፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ዕቅድ ዕውን ለማድረግ መንግሥት የመረጠው የግል ዘርፉን ነው፡፡ በኃይል ማመንጨት ፕሮጀክቶች የራሳቸውን ፋይናንስ ይዘው እንዲገቡና ያመረቱትን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመንግሥት እንዲሸጡ ነው፡፡ በዕቅዱ መሠረትም ግልጽ ጨረታ ወጥቷል፡፡ ወዲዚህ ሥርዓት ለመግባት ምክንያቱ ምንድነው?

ዶ/ር ደብረ ጽዮን፡- በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በመንግሥት ኢንቨስትመንት ነው የመጣነው፡፡ በሁለተኛው ዕቅድ ዘመን ለማመንጨት የሚፈለገውን ስናሰላው ግን በመንግሥት ኢንቨስትመንት የሚቻል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፍላጎቱ በጣም ትልቅ ነው፡፡ የሚያስፈልገው ፋናንስም ወደ ትሪሊዮን ብር ይሆናል፡፡ ስለዚህ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በስፋት በማስገባት የመንግሥትን የኢንቨስትመንት ድርሻ ወደ 20 በመቶ ዝቅ እናድርገው የሚል አቋም ነው የተያዘው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትን የሚመለከተው ፖሊሲያችንም የግል ባለሀብቱ በዘርፉ እንዲሳተፍ ይፈቅዳል፡፡ በመሆኑም “Independent Power Production (IPP)” ወይም ባለሀብቶች የራሳቸውን ገንዘብ ይዘው የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በግላቸው አልምተው ለመንግሥት የሚሸጡበትን ሥርዓት ነው ለመከተል የመረጥነው፡፡ ለተጠቃሚው የማቅረብ ሥራ ግን የመንግሥት ይሆናል፡፡ በዚህ መሠረት በግልጽ የጨረታ ሥርዓት በአደባባይ ባለሀብቶችን እናስገባ፡፡ ከዚህ ቀደም የማናውቃቸው ኩባንያዎችም እንዲመጡ ድርድርን ዝግ በማድረግ ግልጽ ጨረታ ነው ያወጣነው፡፡ ውጤቱንም በግልጽ እያየነው እንገኛለን፡፡ አንድ መቶ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ለወጣ ጨረታ ከ63 እስከ 70 ኩባንያዎች ናቸው እየቀረቡ የሚገኙት፡፡ ይህ ተሰምቶ የማይታወቅ ነው፡፡ በራሳችን ገንዘብም እንደዚህ ዓይነት ፍላጎት ታይቶ አይታወቅም፡፡

ስለዚህ ስትራቴጂያችን በደንብ እንደሚሠራ ከወዲሁ መገንዘብ ችለናል፡፡ ስትራቴጂው ብዙ ጥቅሞችን ነው የሚያስገኘው፡፡ አንደኛው መንግሥት ስለፋይናንስ አይጨነቅም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን መንግሥት ፕሮጀክት የማስተዳደር ጫና ውስጥም አይገባም፡፡ ሌላው ደግሞ ከጊዜ አንፃር ነው፡፡ ገንዘባቸውን አውጥተው ፕሮጀክቶች ላይ ሊተኙ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ኃይል የማመንጨት አቅማችንም በፍጥነት ይገነባል ማለት ነው፡፡ ተደራራቢ ጥቅም ነው የምናገኘው፡፡ ዋናው ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባን ያመነጩትን ኃይል የሚሸጡበት ታሪፍ ላይ ጥሩ ተደራዳሪ በመሆን በቅናሽ ዋጋ መግዛት መቻል ላይ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ መሥራት ይኖርብናል፡፡ በመሆኑም የአገር ውስጥ አቅምን ወይም የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን እንዲያሳትፉ ግዴታ አስቀምጠናል፡፡ ከመወዳደሪያ መሥፈርቱ መካከል አንዱ ምን ያህል ፐርሰንት ለአገር ውስጥ ኩባንያ ለመስጠት ወይም ለመጣመር እንደሚፈልጉ መመዘን እንዲሆን አድርገናል፡፡ ምክንቱም የራሳችንን አቅም እየገነባን ካልሄድን በውጭ ተፅዕኖ መጫወቻ ነው የምንሆነው፡፡ እስካሁን እንደገመገምነው እስከ 35 በመቶ የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ለማሳተፍ ሰነዳቸውን ያስገቡ አይተናል፡፡ በብዛት መምጣታቸውም አነስተኛውን ዋጋ ለመምረጥና ዝቅተኛው ታሪፍ ላይ ለመደራደር ያስችለናል፡፡ በተለይ በፀሐይና በንፋስ ኃይል ማንጫዎች ላይ የጨረታ ሒደቱ ወደ ሁለተኛ ዙር ምዘና ተሸጋግረዋል፡፡ አዝማሚያውን ስናይ ከፀሐይና ከንፋስ ምንጮች ለማምረት ያቀድነው በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን ሙሉ በሙሉ ይሳካል፡፡ ከውኃ ኃይል ለማመንጨት ያቀድነው በዕቅድ ዘመኑ ሙሉ ለሙሉ ዕውን ባናደርግ እንኳን ረዥም ርቀት መሄድ እንችላለን፡፡