www.maledatimes.com ቅንጫቢ ፩ የሽብራዊ ያገዛዝ ታሪክ (ካልታተመ መፅሃፍ የተወሰደ በግደይ ገ/ኪዳን እና ተክሉ አስኳሉ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ቅንጫቢ ፩ የሽብራዊ ያገዛዝ ታሪክ (ካልታተመ መፅሃፍ የተወሰደ በግደይ ገ/ኪዳን እና ተክሉ አስኳሉ)

By   /   October 27, 2012  /   Comments Off on ቅንጫቢ ፩ የሽብራዊ ያገዛዝ ታሪክ (ካልታተመ መፅሃፍ የተወሰደ በግደይ ገ/ኪዳን እና ተክሉ አስኳሉ)

    Print       Email
0 0
Read Time:78 Minute, 39 Second
    የሽብራዊ ያገዛዝ ታሪክ
ሽብር ምንድ ነው? መንበረ ስልጣን የተቆጣጠረ ክፍል ሽብር ሊፈፅም ይችላል? በየትኛውም ስሌት ለበጎም ተባለ ለሌላ ሽብርን የሚደግፍ አይኖርም፡፡ አሸባሪዎች በምስልም ሆነ በታማኝ ምስክር ተረጋግጦባቸው እኩይ ተግባራቸው ቢጋለጥ የሚያስከፋው አይኖርም፡፡ የዛሬውን ውስብስብ ያሸባሪዎች ተግባር ለመፈተሽ በታሪክ ገዢዎች ዜጎቻቸው ላይ የፈፀሙትን ሽብር ማስታወስ ይኖርብናል፡፡ አሸባሪዎች ንፁሃን ናቸው ለማለት ሳይሆን እንደ አብዮታውያን መሳርያ ሁነዋል ወይ የሚለውን ለመመርመር ይረዳናል፡፡
 “ሰዎች አብዛኞቹ ማሰብ አይችሉም፣ የቀሩት ማሰብ አይፈልጉም፣ የሚያስቡት ከዚ የቀሩት እጅግ ጥቂቶቹ በደንብ አያስቡም፡፡ እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑት በቋሚነት፣ በትክክል፣ በስልታዊ መንገድና እራሳቸውን ሳያታልሉ የሚያስቡት -በረዥም ግዜ ልኬት- እነዚህ ናቸው ፋይዳ የሚኖራቸው፡፡”
ሮበርት ኸይንለይን (Robert Heinlein) – Paul J. Watson: Order Out of Chaos ላይ፡፡
ፖል ኮሊንስ (Paul David Collins) መጣጥፎቹን ካልሆነ መፃህፍቱን ማግኘት የተሳነን ተመራማሪ The Hidden Face of Terrorism: The Dark Side of Social Engineering, From Antiquity to September 11 ከተሰኘው መፅሃፉ በተቀነጨበው ፅሁፍ ላይ በዚህ ባለንበት ዘመናዊ ዓለም የሚጎረብጥ እውነት ሲኖር በፈጠራ ይቀየራሉ ይላል፡፡ ከነዚህ ፈጠራዎች አንዱ ሽብር ማለት ያኮረፉ ቡድኖች ተገንጥለው የፋይናንስና ሌላ አቅማቸውን በራሳቸው በማሟላት የሚፈፅሙት ዘግናኝ ተግባር ነው የሚለው ነው፡፡ የሽብር የበላይ ጠባቂዎች ግን እንደ ጋርዮሻውያን ስፖንሰሮች ሌሎች ለማመን የሚከብዱ አካሎች ናቸው፡፡ የሽብር እውነተኛ ምንነትን ለመረዳት በታሪክ የሚከሰቱት ዓበይት ክንውኖች ያጋጣሚ ናቸው ከሚለው የኦፊሻል አተራረክ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ የሽብር የመጀመርያው ወሳኝ ገፅታው በዓብዩ የሚፈፀመው የመንግስት ሽብር ነው፡፡ ሁለተኛ እንዲህ አይነቱ ሽብር መንግስት የነደፈውን የማህበረ-ፖለቲካዊ ፕሮጅክት ለማስፈፀም አብዝሃውን በማሸበር የጥቂቶችን ጥቅም ማስጠበቂያ አካል ነው፡፡ (Father Ignacio Martín-Baró “The Psychological Consequences of Political Terror” የላይኛው መፅሃፍ ላይ የተጠቀሰ፡፡)
“Fake Terror: The Road to Dictatorship” በሚለው መፅሃፉ ሚካኤል ሪቬሮ (Michael Rivero) ፡ “[ሽብር]በመፅሃፉ ያለ ጥንታዊው ዘዴ ነው፣ እስከ ሮም ግዜ ድረስ የሚመዘዝ፡ የሚያስፈልጉህን ጠላቶች መፍጠር፡፡” ነው ይለዋል ሽብርን፡፡ (የላይኛው መፅሃፍ) በዚህ ክፍል ይሄን መንግስታት ስፖንሰር የሚያደርጉትን ሽብር ታሪክ እንዳስሳለን፡፡ ይህን የምናደርገው ታሪክ እውነት መሆኑ ያረጋገጠው መንግታቱ ያመኑበትና ቅጥረኛ ታሪክ ፀሃፊዎቹ የፃፉትን ዋቢ በማድረግ ከተሰሩ ስራዎች ነው፡፡ መንግስት ያላመነበት የሽብር ጥቃት የመስከረም 11፣ 2001 ጥቃት ነው፣ ይህን ደሞ በሚቀጥሉ መእራፎች ማስተባበያቸው ደካማ ከመሆኑ የተነሳ ሳይንስ ተጠቅመን ቅጥፈቱን እናስነብባቹሃለን፡፡
ሮም ሲቃጠል ኒሮ ሲጫወት ነበር – Nero Fiddled While Rome Burned
“ፊድልድ” የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል ቫዮሊን መጫወት ወይም ማጭበርበር ተብሎ እንዳገባቡ ይፈታል የሮማ ከተማ በእሳት በተያያዘችበት ግዜ እብዱ ንጉሷ ኒሮ ቫዮሊን ሲጫወት ነበር ይባላል፣ ለእንሊዘኛ ተናጋሪው የተረፈው አባባልም ሁለት ትርጓሜ አለው፡ ሮም ስትቃጠል ኒሮ ቫዮሊን ሲጫወት አልያም ሲያጭበረብር ነበር የሚል ነው፡፡ የፖል ዋትሰን (Paul J. Watson): Order Out of Chaosየሚለው መፅሃፍ ታሪኩን ይነግረናል፡፡
ኒሮ ከ54 እስከ 68 ዓ.ም የገዛ ንጉስ ሲሆን አማካሪዎቹ በሞት ሲለዩት የፀባይ ለውጥ አመጣ፡ የሞት ቅጣት በማስቀረት፣ ግብር በመቀነስ፣ ባሮች ጌቶቻቸውን እንዲከሱ በመፍቀድ የሚታወቀው ተወዳጅ ንጉስ ተቀየረ፡፡ ብቻውን ስልጣን ፍፁም መቆጣጠሩ ፍፁም ይመርዘው ጀመር፡፡ ሮም ከመቃጠሏ በፊት የጀመረው እብደቱ በክህደት የተጠረጠረ በሞት እንዲቀጣ የሚያዝ ህግ አስተላልፎም ነበር፣ በዚህም ፖለቲካዊ ተፎካካሪዎቹን፣ ሚስቱንና እናቱን ሳይቀሩ አስወግዷቸዋል፡፡ ሲያበሳጩት የነበሩት ክርስትያኖችን የሚያገኝበትን ሰበብ ሲፈልግም ነበር፡፡ ክርስትያኖቹ ግዛቲቱ የምትከተለውን የበሰበሰ ተግባራትና የባእድ አምልኮን ሲነቅፉ ነበር፡፡ የታሪክ ምሁራን እሳት አደጋው በሚጀምርበት ግዜ ኒሮ ሮማ ነበር ወይስ አልነበረም የሚለውን ይከራከሩበታል፣ በርግጠኝነት ግን እሳቱ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ግዜ ሮማ ውስጥ ነበር፡፡ ህዝቡ ሲሞት ቅኔ ሲፅፍና ሲዘፍን ነበር የሚያያቸው፡፡ አባባሉም ከዚህ ነው የመጣው፡፡
ኒሮ ሲጫወት ዘቦቹን ጎዳናዎቹን እንዲጠብቁና ቃጠሎውን ለመቆጣጠር የሚደረግ ሙከራ እንዲያጨናግፉ ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ታዘን ነው በሚሉ ሰዎች እሳት የሚያዛምቱ ችቦዎች ቃጠሎው ላይ ሲጨምሩ ታይተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እሳቱን ያስጀመረው ኒሮ እራሱ ነው የሚል ጭምጭምታ ሊሰማ ችሏል፡፡ በትክክል ያስጀምረው ወይም እንዲባባስ ይፍቀድ ሊያከራክር ይችላል፣ ውጤቶቹ ግን አያከራክሩም፡፡ ኒሮ ለእሳቱ ወድያውኑ ክርስትያኖችን አወገዘ፡፡ ብቸኛ ማስረጃው አንዳንድ ክርስትያኖች ሌሎች ክርስትያኖች ላይ መስክረዋል የሚለው ነው፡፡ ይህ ደሞ እንዲህ እንዲሉ ታስረው ከተሰቃዩ በውኋላ የመጣ ነው፡፡ በከተማው የድሆች መኖርያ አካባቢ እሳቱ እንደመጀመሩ በዚሁ አካባቢ የሚኖሩትን ክርስትያኖቹን መጠርጠር መሰረተ-እውነት (ሎጂክ) የተከተለ አይደለም፡፡ ዓላማ ከነበራቸው የኒሮን ቤተመንግስትን እንጂ የራሳቸውን መኖርያ ለምን ያቃጥላሉ? እርሱ ግን የሚጠላውን የተዘበራረቀውን ቦታ አጥፍቶ እንደገና እንደልቡ ምኞት መገንባት ይፈልግ ነበር፡፡ ቃጠሎ እንዳበቃ ከተማዋ እንደአዲስ ንድፍ ወቶላት መገንባት ጀመረች፣ ለኒሮ ክብር ከሚገቡ አዳዲስ ቤተመንግስቶች ጋር፡፡ ማምለጫ የተደረጉት ክርስትያኖች ግን እጅ እግራቸው ለሰርከስ (ለህዝብ መዝናኛ) እየታዩ ባንበሶች ተቦጫጭቀው የሰው ችቦ ሁነው ነበር፡፡ ከቃጠሎ ኒሮ ሁለት ነገሮችን አትርፏል፡፡ ከተማዋን ዳግም ያነፃት ሲሆን ለስልጣኑ ያሰጋውን እንቅስቃሴንም ወግቷል፡፡ ላጭር ግዜ መንበረ ስልጣኑን ቢያጠናክርም በረዥም ግዜ ግን ከፈጣሪ በቀል አላመለጠም፣ የደረሰባቸው ግፍ እንደነ ጴጥሮስ እና ጳውሎስን ወደ ሰማእትነት አስቀይሯቸዋል፡፡ የሮም ሰዎች ሃዘኔታ ይሰማቸው ጀመር፣ የኒሮ ዘመንም በ68 ዓ.ም እራሱን ካጠፋ በውኋላ አበቃለት፡፡
ዲዮክሊትያን – Diocletian
ዲዮክሊትያን በ284 ዓ.ም ነበር ስልጣን የያዘው፡፡ የወታደሮች ጀነራልም የነበር ሲሆን ጨቋን አያያዝ ይጠቀም ነበር ይለናል የፖል ዋትሰን (Paul J. Watson): Order Out of Chaos የሚለው መፅሃፍ፡፡ መንግስቱንም ሲያካሂድ የነበረው አንድ ጀነራል ወታደሮቹን እንደሚይዛቸው አድርጎ ነበር፡፡ ለግዛቲቱ (ኢምፓየር) ስርአት መምጣት የሚችለው የግለሰባዊ ነፃነት ክፉኛ በቁጥጥር ስር ከዋለ ነው ብሎ ያምን ነበር፡፡ በ301 ዓ.ም ከጀርመኖችና ከሳሳኒዶች ጋር የነበረው ውጊያ ሲገባደድ ለጨቋኝ አገዛዙ ሰበብም አብሮ ተቋጨበት፡፡ ጨቋኝ አገዛዙን ለማስቀጠል አዲስ ጠላት አስፈለገው፡፡ በግዜውም ኢኮኖሚው ቀውስ ውስጥ ገብቷል በማለት የተጋነነ ግብር ጫነ፡፡ ህዝቡም ማንገራገር ጀመረ፡፡ እንደ-ባርያ የሆኑት ዜጎቹን ድጋፍ ለማግኘት አዲስ ጠላት መገኘት ነበረት፡፡ በመጀመርያ በተሳካ መልኩ ማኒካውያንን ካሳደደ በውኋላ፣ አውራ ጣቱን ቁልቁል ዘቅዝቆ ፊቱን ወደ ክርስትያኖች አዞረ፡፡ ይህ የሆነው ላለፉት አስራ አምስት አመታት ከናካቴው ረስቷቸው/ትቷቸው ከነበር በኋላ ነው፡፡ ላለፉት 50 አመታት የክርስትያኖች ቁጥር በእጥፍ በመጨመር ከግዛቲቱ አስር መቶኛ ደርሰው ነበር፡፡ ሁለት ንጉሶች ተቀይረው ነበር፡ የሰሜን ምስራቅ ሚሰፖታምያ የምትገኘው የኦርሶኢኔ (Osroene) ንጉስና የአርመንያ ንጉስ፡፡ በሮም ወታደር ውስጥ ሲያገለግሉም ነበር፣ በአካባቢያዊ አስተዳዳሪዎች ስርም ሰራተኞች ነበሩ፣ በንጉሳዊው ሰራተኞች ዝቅተኛ ቦታ ላይም ነበሩ፡፡ ዲዮክሊቲያን ሰበብ ይታየው ጀመር፡፡
በ302 ዓ.ም በሶርያ አንቶይችን ለስራ በሚጎበኝበት ወቅት እንደልማዱ የጣኦት አምልኮው በሚጠይቀው መሰረት መስዋእትነት ሲያካሂዱ ነበር፡፡ ክርስትያኖቹም ዘወትር እንደሚያደርጉት ክፉ ተፅኖን ለማስራቅ እያማተቡ እንዲህ አይነት የጣኦት ተግባር መቃወም ጀመሩ፡ ከነዚህ ክርስትያኖች ሮማነስ የተባለ የሚታወቀው ነበረበት፡፡ ዲዮክሊቲያን ተበሳጨ፡፡ የተሰዋውን እንሰሳ ሰውነት አካሎች እያየ የሚተረጉመው በክርስትያኖቹ ተፅእኖ ምክንያት ሊታየው እንዳልቻለ ይናገራል፡፡ ዲዮክሊቲያን በመቆጣት በዘውዱ አካባቢ ያሉ ሁሉም መስዋእትነት ስርአት እንዲፈፅሙ ያዛል፡፡ በዚህም ትእዛዝ ማሳደዱን ለመጀመር ሰበብ አገኘ፡፡ ሮማነስ ምላሱ ተቆርጦ ለአንድ አመት በወህኒ ማቀቀ፡፡ በግዜውም ዲዮክሊቲያን ክርስትያነኖች ለመንግስት አማልክት መስዋእትነት እንዲፈፅሙ አልያ ቅጣት እንዲቀበሉ አዘዘ፡፡ የንጉሱ ምክትልም ጋሌሪየስ(Galerius) ቤተመንግስት ቢቃጠል ዘመቻው እንደሚጧጧፍለት ይመክረዋል፣ በ16 ቀናት ውስጥ እንዳጋጣሚ ሁለቴ ኒቆመድያ የሚገኘው ቤተመንግስቱ ቃጠሎ ደረሰበት፡፡ ወድያው ክርስትያኖቹ ተወቀሱ፡፡ ክርስትያኖች መሰባሰብ ተከለከሉ፡፡ መፅሀፍ ቅዱስ ተሰብስቦ ተቃጠለ፡፡ የክርስትያኖቹን ጥፋተኝነት ተታሎ ያመነ ህዝብ በሚገፋፋቸው አራዊቶች ተበሉ፡፡ ሌሎቹ ታስረው አንድ የጣኦት መስዋእትነት ስነስርአት ከፈፀሙ ትለቀቃላችሁ ተባሉ፡፡ አብዛኞቹ አልተቀበሉትም፣ ዲዮክሊቲያን ክርስትያኖቹን ለመከፋፈል ያላደረጉትን መስዋእትነት አደረጉ የሚል ምልክት ያደርግባቸው ጀመር፡፡ ይህ እስከ 305 ዓ.ም ድረስ ቀጠለ፣ በዚህን ግዜ ክርስቲያኖችን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በማይቻል መልኩ በግዛቲቱ ተስፋፍተው ነበር፡፡ በ305 ዓ.ም አምባገነኑ ታሞ ሞተ፡፡ ምክትሉ ጋሌሪየስ ከምእራቡ ግዛት ምክትል ንጉስ ከነበረው ኮንስታንተይስ ጋር በመሆን መግዛት ጀመረ፡፡ በ306 ዓ.ም ኮንስታትየስ በጦር አውድማ ሞተ፣ ልጁም ኮንስታንታይን ተካው፡፡  በዲዮክሊቲያን የተጨፈጨፉት በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስትያኖች በከንቱ አልሞቱም፡፡ ኮንስታንታይን የመጀመርያው ክርስትያን ንጉስ በመሆን ዓለምን ቀየረ፡፡
የባሩዱ ሴራ (Gunpowder Plot)
በእንግሊዛውያን ቀን መቁጠርያ ላይ እስከዛሬ ድረስ የጋይ ፋውከስ ቀን (Guy Fawkes’ Day) ተብሎ የሚታሰበው ህዳር 5፣1605 ላይ የተመዘገበው ለፖለቲካዊ ትርፍ የተቀነባበረው የሽብር ውሎን እናገኛለን፡፡ ዌብስተር ታርፕለይ /Webster Tarplay፡ 9/11 Synthetic Terror Made in USA በሚለው መፅሃፉ ታሪኩን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ንጉስ የነበረው ቀዳማዊ ጀምስ ስትዋርት በስብእናው ስኮትላንድንና ኢንግላድን ያዋሃደ ፕሮቴስታንት ነበር፣ ቁንጮ የካቶሊክ ሃይል ከሆነችው ስፔን ጋር ስምምነት የሚያወርድበትን መንገድ ሲያፈላልግ ነበር፡፡ እንግሊዝ ውስጥ ካሉ ካቶሊኮች ጋርም የመቻቻል እርምጃዎችን ሲወስድ ነበር፣ በሰሜን የነበሩት ባላባቶች በግዜው ለሮማ ታማኝ ነበሩ፡፡ ለግላቸው ጥቅም እንደሚያገኙ ተስፋ ያደረጉ የቬኔሽያ ቁንጮዎች የላኳቸው ሰላዮች ጄምስን ከስፔን ጋር ሊያጋጩ መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ለነሱም ካቶሊኮች መንግስት ቢያሳድዳቸው እንደሚጠቀሙበት አሰሉ፡፡ ከነዚህ ጦር ናፋቂዎች ዋናው በዘውዳዊው ገዢ ስር ቻንስለር (ጠ/ሚኒስትር) የሆነው የሳሊስበሬ መኳንንት የነበረው ሎርድ ሮበርት ሴሲል (Lord Robert Cecil) ነው፡፡ ይህ ሰው እቅዶቹ ንጉሱ እንዲቀበል የተጠቀመበት ዘዴ ሽብር ነበር፡፡ ራሱን ከትእይንቱ በስተጀርባ በመደበቅ በህቡእ ካቶሊኮችን መቀስቀስ ጀመረ፣ ከነዚህ ዋናው ሎርድ ቶማስ ፐርሲን (Thomas Percy) ነበር የተንኮል ቀለበቱ ውስጥ የከተተው፡፡ ይህን ከፍተኛ የካቶሊክ ቤተሰብ በመጠቀም ፅንፈኛና ጀብደኛ የሆኑ ገራገር ካቶሊኮችን በተዘዋዋሪ በማሰባሰብ የሽብር ቡድን መጠንሰስ ጀመረ፡፡ ከነዚህ ሞኞች አንዱ ጋይ ፋውከስ ነው፡፡ ቶማስ ፐርሲ አክራሪ ካቶሊክ ነው ቢባልም እውነቱ ግን ሁለት ሚስቶች የነበሩት ሰው ነው፡፡
እኚህ ፅንፈኛ ካቶሊኮች ፓርላማው አካባቢ ካለ ቤት ምድር ለምድር በመቆፈር ከተከራዩት የፓርላማው ምድር ቤት በኩል በመውጣት ምድርቤቱን በተቀጣጣይ ባሩድ (ፈንጅ) በመሙላት ንጉሱ ህዳር ላይ ምክር ቤቱን ለማስጀመር በሚመጣበትና የባላባቶቹና የታችኛው ም/ቤቶች በሚሰባሰቡበት ወቅት ማፈንዳት የሚል ነበር፡፡ ሆኖም ጋይ ፋውከስ ወንጀሉን በቀጠሮው መሰረት እንደነገ ሊፈፅም ማታ ላይ ወደ ምድርቤቱ ሲገባ በቁጥጥር ስር ውሎ ከሸፈ፡፡ ፋውከስና ቡድኑ ተሰቃይተው በስቅላት ተገደሉ፣ ሌሎች የካቶሊክ ቀሳውስትም ሰለባ ሆኑ፡፡ ጄምስ ካቶሊኮችን መቻቻል የሚለውን እቅዱን ተወው፣ በመቀጠልም ከስፔንና ፖርቱጋል ግዛቶች ጋር ድፍን ክፍለ ዘመን የፈጀውን ጦርነት እንግሊዝ ጀመረች፣ ከዚህም የብሪታንያ ግዛት (ኢምፓየር) ውልደቱን አገኘ፡፡ የጋይ ፋውከስ ቀን “የእንቢ ለጳጳሱ” /“no popery”  እና ለስፔን ጥላቻ የሚታስብበት በዓል ሆነ፡፡
ይን የባሩዱን ሴራ በተመለከተ የሱሳዊው (ጀስዊት-የካቶሊክ ቀሳውስት ህቡእ ማህበር) የሆነው ጌራርድ እንደሚከተለው ብሎታል፡
“በግዜው የነበረው አስተዳደር (የሴሲል) ለዓላማው ሲል ሴረኞቹ እቅዳቸውን እንዲፈፅሙ የሚያነሳሳበትን መንገድ አግኝቷል ወይም ቢያንስ ከጅምሩ ጀምሮ የሚደረገውን እያወቁ ለራሳቸው ጥቅም የሚያገኙበት ደረጃ ላይ እስኪደርስ ድረስ ሴራውን ሲንከባከቡና ሲጠብቁት ነበር፡፡ ምንም እንኳ ትክክለኛ ባህርያቱን ለመረዳት የሚከብደን ቢሆንም ሴረኞቹ ወይም አብዛኞቹ ታላቅ ጉዳት ለማድረስ ብለው ከልብ ይሰሩ የነበሩ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም ግን ከነሱ የረቀቁ ሴረኞች ባዘጋጁት ጨዋታ የተታለሉ ተሳታፊዎች መሆናቸው ቢረጋገጥ’ኳ ከጥፋተኝነት አይፀዱም፡፡” Gerard, John, S.J. What Was the Gunpowder Plot? The Traditional Story Tested by Original Evidence
ይህ የዛሬ 406 ዓመት ስለተስተናገደ ሴራ በ1897 የተፃፈ ዓ.ነገርን ደግመው ያንብቡት ዛሬ ላይ እየተሰራ ስላለው የዓለም አቀፋዊው የሽብር ትእይንት የሚለው ብዙ አለው፡፡ ይህ መንግስት አስተዳደር ስፖንሰር ስለሚደረግ ሽብር የተሰጠ ጥሩ ፍቺ ነው፡፡
እዚህ ላይ መጨመር ያለበት ቀዳማዊ ጄምስ ስለሴራው አስቀድሞ የሚያውቀው ነገር እንዳልነበረ ነው፡፡ ሴራው ያነጣጠረው ጄምስ ላይ ነበር፤ በአንድ በተፈለገ የፖሊሲ አቅጣጫ እንዲሄድ ነው ያደረጉት፡፡ ከድርጊቱ በውኋላ ንጉሱ የሴሲል እጅ ምን ያህል እንደነበረበት የተረዳ ይመስላል፡፡
የኦተስ የፈጠራ ሴራ
በ17ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ አውራ የካቶሊክ ሃይል ሆና የወጣችው ፈረንሳይ ነበረች፡፡ ዳግም የእንግሊዝ ፓርላማ አሁን በእንግሊዝ ካቶሊክን ዳግም ለማደስ እያሴረች ያለችው ፈረንሳይ መሆኗን መስረጃ እንዳገኘ በአንድ አጭበርባሪ ታይተስ ኦተስ (Titus Oates) የተባለ መስካሪ ተደርጎ ማስረጃ ቀረበ፡፡ እንግሊዝ ዳግም በፀረ ጳጳሱ እንቅስቃሴ ተናጠች ካቶሊኮች ተገደሉ ታሪክ እራሱን እየደገመ ቀጠለ፡፡ በ1678 መጨረሻ ሴራው ተቀባይነት ከማግኘትም በላይ ስለሴራው መኖር የማይቀበል እንደ አገር ከሃዲ ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡ ይህ የኦተስ ሴራ እየተባለ የሚታወቀው ፈጠራ በእንግሊዝ ውስጥ ሰብአዊ ርህራሄ እንዲጠፋ ያደረገ ፈጠራ ነበር፡፡
የዚህ ታይተስ ኦተስ የተባለ አጭበርባሪ ሰው ፈጠራ ስፖንሰሮች የነበረው አንቶኒ አሽሊ ኩፐር፣ ሎርድ ሻፍትስበሪ፣ የዊግ ፓርቲ መስራች እና CABAL የሚባለው የቁንጮዎች ካቢኔ አባል የነበረው ነው፡፡ CABAL የስማቸው መጀመርያ ሲሆን አርሊግቶን፣ ባኪንግሃም፣ አሽሊ እና ላውደርዴል የነበሩበት ነው፡፡ ፈላስፋው ጆን ሎክ የአሽሊ ፀሃፊ ነበር፡፡ በ1679 ጫጫታው መብረድ ጀመረ፣ ታይተስ ኦተስም ውሸታምና አጭበርባሪ መሆኑ ተደረሰበት፡፡ በዚህን ግዜ ንጉሱ ቻርለስ 2ኛ አሽሊ በክህደት ወንጀል ፍርድቤት እንዲቀርብ አደረገ፡፡ አሽሊ ብይን አምልጦ የሂወት ዘመኑን በጨረሰባት ሆላድ ተሰደደ፡፡
አዶልፍ ሂትለር
የዚህ ሰው ስም በክፉ የሚነሳበትን ያህል ሴራዎቹ ባግባቡ አይገለፁም፡፡ የስኬቱ ሚስጥር ፋይናንስ ያደረጉትን ምእራባውያን ቁንጮዎች በክፍል አንድ አይተነዋል፡፡ ባገር ውስጥ ዲሞክራሲውን ሰርዞ እራሱን ፉረር ማለትም “መሪ” ለማድረግ የተጠቀመበት ስልት ሽብር ነበር፡፡ የሽብሩ ሚስጥርም ለሃገሪቱ ሳይሆን ለሂትለር ታማኝ የሆኑ ፖሊሶች በኸርማን ጎሪንግ (Herman Goering) የፕረሽያ ፖሊስ ሃላፊ ሲሆን በሃገሪቱ ፖሊስ እንዲገቡ መደረጉ ነው፡፡ እነዚህ ፖሊሶች የመንግስት ጠላትን እንዲጠሉ ተደርገው የሚሰለጥኑ ናቸው፡፡
የፖል ዋትሰን (Paul J. Watson): Order Out of Chaos የሚለው መፅሃፍ እንደሚከተለው ያስነብበናል፡፡ በየካቲት 1933 ኸርማን ጎሪንግ፣ ጆሴፍ ጎቤልስ (ፕሮፖጋንዳ ሚኒስቴር) እና ሂትለር የፓርላማውን ህንፃ በእሳት የሚያነዱበት እቅዳቸውን አጠናቀቁ፡፡ ሶስቱም ከሺህ አመታት በፊት የፈፀመውን የኒሮን ተግባር አጥንተው ነበር ማለት ነው፡፡ በዚሁ ወር ማሪነስ ቫን ደር ሉቤ የተባለ የአይምሮ ችግር ያለበት የዳች ተወላጅ የመንግስት ህንፃዎችን የማቃጠል እቅድ አነግቦ በርሊን ውስጥ ሲዘዋወር ነበር፡፡ በሂትለር ቁጥጥር ስር የገባው ፖሊስ ሰውየውን ለማሰር ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ በመጨረሻ ቫን ደር ሉቤ ፓርላማ ጠባቂዎችን አስቶ በመግባት ሸሚዙን አቀጣጥሎ ፓርላማውን ለማጋየት ሞከረ፡፡ የጎሪንግ ክፍል ምድርቤት ከፓርላማው ምድርቤት ጋር የሚያገናኝ የምድርስር መተላለፍያ ተጠቅመው የሂትለር ፖሊሶች (SA) እና መሪያቸው ካርል ኧርነስት (Karl Ernst) ጋዝ በማርከፍከፍ እሳቱን አባብሰው በገቡበት ተመልሰው አመለጡ፡፡ ሂትለርና ፕሮፖጋንዳ ሚኒስትሩ ቶሎ ብለው ለዚህ ተጠያቂው ኮሚኒስቶች እንደሆኑ አሳወቁ፡፡ ሂትለር ለጋዜጠኞች፡ “አሁን በጀርመን ታሪክ የታላቅ ዘመን ጅማሮን እያያቹ ነው፡፡ …ይህ እሳት የመጀመርያው ነው፡፡” ብሏቸው ነበር፡፡ ከዚህ በውኋላ ይህ “የኮሚኒስቶች ሴራ” በመገናኛ ተደጋግሞ ተለፈፈ፡፡ ሂትለርም ከቃጠሎ በፊት የተዘጋጀበትን ሁሉ ፈፀመ፣ ተቃዋሚዎቹን ማሰር ጨምሮ፡፡
ከቃጠሎው በነጋታው ሂትለር ያስቸኳይ ግዜ አዋጅ አስተላለፈ፣ አንቀፅ 48ን ስራ ላይ አዋለ፡- የግለሰባዊ ነፃነቶችን፣ የመናገርና የመፃፍ ነፃነትን፣ የመሰብሰብ ነፃነት፣ የፖስታ፣ የቴሌግራፍና ቴሌፎን ግንኙነት ሚስጥርነትን፣ የቤት ፍተሻ ትእዛዝ፣ የንብረት መውረስና የአጠቃቀም ገደብ ትዛዝ ባንቀፁ እንደተጠቀሰው እስከተፈቀደ ድረስ እንዲጣሱ የሚያውጀውን አንቀፅ ወደትግበራ አስገባው፡፡ እንዲህም ሁኖ ሂትለር አምባገነን ፉረር ለመሆን የሚያስችለውን ሁለት ሶስተኛ ድምፅ ማግኘት አልተቻለውም፡፡ ለዚህም ሂተለር ፕሬዚደንቱ ሂንደንበርግ ከዚህም የባሱ አዋጆችን እንዲፈርም ጫና ይፈጥርበት ጀመር፡፡ በዚህም ስልት ናዚዎችን መውቀስ በህግ የሚያስቀጣ ተግባር በማስደረግና መከላከያ፣ ታዛቢ ፈራጆች (jury) እና የህግ አማካሪ የሌሉበት የወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በማቆም የህዝብ ተወካዮችን በፍራቻ በማሸበር መቆጣጠር ጀመረ፡፡ አዲስ ፓርላማ በሚመረጥበት ወቅት ሂትለር የይሁንታ አዋጅን (Enabling Act) በፈጠረው የፍራቻ ምህዳር ስር ሁነው እንዲያፀድቁ በማድረግ ህጋዊ አምባገነን ለመሆን ቻለ፡፡ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው በዛች እሳት አደጋ ተጀምሮ ነው፡፡
ዌብስተር ታርፕለይ /Webster Tarplay፡ 9/11 Synthetic Terror Made in USA የሚለው መፅሃፍ ሂትለር ሽብርን የተጠቀመበት ህጋዊ አምባገነን ለመሆን ብቻ አይደለም አብዛኛው ሰው ጦርነትን እንደማይደግፍ ስላወቀ ጦርነት የጀመረበት የፖላንድ ወረራውንም ሰበብ ባቀነባበረው ሽብር ውጤት ነበር ይለናል፡፡ በነሐሴ 1939 በጀርመን ማርሚያ ቤት የሚገኙ ወንጀለኞች ቡድን በማሰባሰብ የፖላንድ ወታደሮች መለዮ በማስለበስ ፖላንድ ድንበር አቅራቢያ ከሚገኝ ግሌዊትዝ ሬድዮ ጣብያ ወሰዳቸው፡፡ እነዚህ መከረኞች ወደ ሬድዮ ጣብያው ተወስደው ተረሸኑ፡፡ ሬሳቸውም በሬድዮ ጣብያው ዙርያ ጥቃት ሲሰነዝሩ እንደሞቱ እንዲመስል ተስተካከሎ ተበተነ፡፡ ከዛም የናዚ ሰዎች ሲተላለፍ የነበረውን ፕሮግራም አቋርጠው በፖሊሽ ቋንቋ ፀረ-ጀርመን ንግግር መለፈፍ ጀመሩ፡፡ ይህ ቀፋፊ ተውኔት በፕሮፖጋንዳ ሚኒስትሩ መቶ ግዜ ሲለፈፍ ህዝቡ ከፖላንድ ጋር የማይቀረውን ጦርነት እንዲቀበል አደረገው፡፡ መስከረም 1፣ 1939 ጦርነቱ ጀመረ፡፡
ዘመቻ ኖርዝዉድስ / Operation Northwoods
አሜሪካን ወደአንደኛና ሁለተኛ አለም ጦርነት ለማስገባት የተፈፀሙትን ሴራዎች ክፍል አንድ ላይ ተመልክተናቸዋል፣ እነሱን እያስታወስን እዚህ ደግሞ ሶስተኛ የዓለም ጦርነት ሊያስጀምር ብሎ የነበረውን እቅድ እናስነብባችኋለን፡፡ ይህ ዘመቻ ኖርዝዉድስ የተባለው ሰነድ የወታደራዊ የበላይ መኮንኖች ጥምረት ሊቀመንበር የሆነው ለይማን ሌሚንቲዘር አጋሮቹ መኮንኖች ካስትሮን ከኩባ ለማስወገድ ያለመ የሽብር ዘመቻ እቅድ የያዘ ሰነድ ነው፡፡ የመኮንኖቹ ትክክለኛ ፍላጎት በውል ለማወቅ ግልፅ አይደለም፡፡ ከካስትሮ ጋር ጦር መማዘዝ እንደፈለጉ ግን ግለፅ ነው፡፡ ይህ Body of Secrets ለሚለው መፅሃፉ ሲመረምር ይፋ ያደረገው ጄምስ ባምፎርድ (James Bamford) የተባለ የቀድሞ የኤቢሲ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ይህ ሰነድ ጦርነቱን የአሜሪካ ህዝብ እንዲደግፈው አሜሪካ ላይ ሽብር መንዛትን እቅድ የያዘ ነበር፡፡ ዘመቻ ኖርዝዉድስ ያሉት እቅዳቸው በአሜሪካ ጎዳናዎች ላይ ንፁሃን ዜጎች እንዲገደሉ፣ ከኩባ የሚሰደዱ ባህር ላይ እንዲሰምጡ፣ በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሚያሚና ሌሎች ቦታዎች የአሜሪካ ሰራዊት ከባድ የሽብር ማእበል እንዲነዛ የሚጠይቅ ሰነድ ነበር፡፡ ሰዎች ባልፈፀሙት የቦምብ ጥቃት እንዲጠየቁ፣ በተራቀቀ ቴክኖሎጂ አውሮፕላኖች እንዲጠለፉ ወይም ሰው አልባ አየሮች (በርቀት መቆጣጠርያ የሚነዱ) በማፈንዳት ኩባ ያደረገችው በማስመሰል ለጦርነት ምክንያት ማግኛ የታቀዱ ነበሩ፡፡ መኮንኖቹ በወታደሮቻቸው ላይም ሞት ከመሸረብ አልተመለሱም፡- ወዳጅ ኩባውያንን የካስትሮ ደንብ ልብስ በማልበስ ጓንታናሞ ቤይ የሚገኘውን የአሜሪካ ባህር ሃይል እንዲያጠቁ ማድረግም እንዳማራጭ ያቀርባል፡፡
ዘመቻ ኖርዝዉድስ ታሪክንም እንደማጣቀሻ በመጠቀም ለሽብር ፈጠራቸው ሃሳብ ያፈልቃሉ፡- በ1898 በሃቫና ወደብ ፍንዳታ የደረሰባት ማይኔ (Maine) የምትባለዋ የአሜሪካ የጦር መርከብ በማስታወስ በጓንታናሞ ቤይ የአሜሪካ መርከብን በማፈንዳት ኩባን መውቀስ እንችላለን ይላሉ፡፡ የማይኔ የጦር መርከብ በ1898 በፍንዳታ መስመጧ አሜሪካ የመጀመርያውን ኢምፐርያሊስት ጦርነት እንድታረግ ያረጋት ታሪክ ያስቀየረ ክስተት ነበር፡፡ ለዚች መርከብ መስመጥ ስፔኖች ቢወቀሱም ከአስርት አመታት በውኋላ በሰመጠችው መርከብ ቅሪት በተደረገው ምርበራ መርከቧ ከውስጥ በተነሳ ፍንዳታ መስመጧ ተረጋግጧል፡፡ በግዜው የነበረው የቁንጮዎች ጋዜጣ ስፔንን ወቅሶ ጦርነት ሲወተውት ነበር፡፡
ወደ ኖርዝዉድስ ስንመለስ በአሜሪካ ያሉ ቁንጮዎች መንግስት ስፖንሰር ያደረገው ሽብርን ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይሉ ያሳየ ሰነድ ነው፡፡ ፕሬዚደንት ኬነዲ እቅዱን ውድቅ ባያደርገው ኑሮ መኮንኖቹ በዛ ቀዝቃዛው ጦርነት በጦፈበት የኩባ ሚሳይል ቀውስ ግዜ ሶስተኛ የዓለም ጦርነትን ከማስጀመር የሚገታቸው አይኖርም ነበር፡፡ አሁን የኬነዲ አሟሟት እየተረዳነው ያለን ይመስለናል፡፡
ሃማስና ሊኩድ ፓርቲ
ይህ የማይታመን ግን እውን የሆነ ጥምረት ነው፡፡ እስራኤል ለሃማስ ካደረገችለት ድጋፍ ተጠቃሹ፡ ፅንፈኝነቱ እየታወቀ ለሚያንቀሳቅሳቸው ምግብ ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ ት/ቤቶች፣ መዋእለ ህፃናት እውቅና በመስጠት የፋታህን አማራጭ አስተዳደር ስርአትን እንዲፎካከር ይደረግ ነበር፡፡ እነዚህ “የመንደር ሊጎች” - ‘Village Leagues’ በመባል ይታወቁ ነበር፣ የታወቁ የሃማስ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ አንቀሳቃሽ ሰዎች መሰረታቸውም ነበሩ፡፡ ይህ የተጀመረው ቀድሞ ራሱ አሸባሪ የነበረው የእስራኤል ጠ/ሚኒስቴር ሜናኬም ቤጊን(Menachem Begin) ሼክ አህመድ ያሲን የእስላማዊ ማህበር ለመመስረት የሚጠይቅ ማመልከቻ ሲያስገባ ፈቃድ በሚሰጠው ግዜ ነበር፡፡ ይህ ማህበር ነው በ1987 ወታደራዊ ክንፉን ሃማስ በማለት የከፈተው፡፡ የእስራኤል ፅንፈኛ ቀኝ ዘመሙ ሊኩድ ፓርቲ ፈቃዱን የሰጠው አንድ አይነት አጀንዳ ስለነበራቸው ነው፡ የያሲን አረፋትን ፋታህን ማወክ የሚል፡፡ የመንደር ሊጎቹ ለፍልስጤማውያን ስልጠና ለመስጠት ብቻ ሳይሆን የጠቀሙት በሺዎች የሚቆጠሩ ወሬ አቀባዮችንም አስገኝቷል፡፡ በ1993 የኦስሎ ስምምነት ከተደረገ በኋላም ድጋፉና ፈንዱ ሲሰጠው ነበር፡፡ ተቀናቃኝ ቡድን ማስገባቱ የፍልስጤም ነፃ አውጪ /ፒ.ኤል.ኦ/ ድርጅት እንዲሳሳ አድርጓል፡፡ በውኋላ ጠ/ሚ የሆነው ኤርያል ሻሮን የዚህ ፖሊሲ ዋና አስፈፃሚ ነበር፡፡ በ1994 የአጥፍቶ ማጥፋቱ ጥቃት ማእበል ከጀመረ በውኋላ እስራኤል ከፒ.ኤል.ኦ ጋር በማገናኘት ስሙን ታጎድፍ ነበር፡፡ ወግ አጥባቂው ሊኩድ ፓርቲም ከጨቋኝ ፖሊሲዎቹ ጋር ተቀባይነት እንዲኖረው ያስችላል፣ ባሸባሪ ፍልስጤማውያን ላይ አፀፋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ቃል በመግባት፡፡ በዌስት ባንክ የሚፈጠረው ግርግርና ስርአት አልበኝነት ለሊኩድ ፓርቲ ስርአት መዘርጊያ ይሆናል፡፡ ሃማስ ከእስራኤል ጋር ያለው ግንኙነት የአረቡ አለም ያደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ሃማስ እስራኤል የሚያሰጓትን የፒ.ኤል.ኦ አመራሮችንም ያስወግድላታል፡፡
በፍልስጤምና እስራኤል መካከል ሰላም ሊያወርድ ተቃርቦ የነበረውን የእስራኤል መሪ ይሳቅ ራቢንን የገደለው ዪጋል አሚር ያሰለጠነው የእስራኤል ሺን ቤት የተባለው ያገር ውስጥ ደህንነት ነው፡፡ ሺን ቤት መሪያቸው ይሳቅ ራቢን ሂወት ላይ ጥቃት እንደሚፈፀም ተደጋጋሚ ጥቆማ ደርሶት ነበር፡፡ ማንኛው የታጠቀ ሰው ሰልፍ ሰብሮ ሲገባ ወድያው እንዲተኩሱበት የሰለጠኑት የራቢን ጠባቂዎች ገዳዩ ከስድስት ጫማ ርቀት አጠገባቸው ሁኖ ሲተኩስበት ፀጥ ብለው ማየታቸው እንግዳ ነው፡፡ ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው ከሆነ ራቢን ተነስቶ ወደ ሊሞዚን መኪናው እየሄደ “ያማል፣ ግን ያን ያህል አይደለም” እያለ ተሰምቶ ነበር ወደ ሆስፒታል የተወሰደው፡፡ እዛም ሲደርሱ ሹፌሩ ከመኪናው ወጥቶ የድረሱ ጥሪ ለማሰማት ተገዶ ነበር፡፡ የተጎዳውን ጠ/ሚኒስትር ለመርዳት በተጠንቀቅ ሲጠብቅ የነበረ የሕክምና ቡድን አለመኖሩ የማይጠበቅ ነው፡፡ እንዲሞት የፈለጉት ቡድኖች እንዲሞት እንዳረጉት የሚያሳይ ነው፡፡
የራቢን ባለቤት ለሞቱ በቀጥታ ተጠያቂ ያደረችው የሊኩድ ፓርቲን ሲሆን በተለይም ደም የተጠማው መሪውን ቤናሚን ኔታንያሁን ወቅሳለች፡፡ የራቢን ግድያ የሃማስ ሞኞች አልያም የራሳቸው የእስራኤል ኤጀንቶች እንደተገበሩት የሚያሳይ ሲሆን ስልቱና ዓላማው ሁሌም አንድ ነው፡፡ የእስራኤል የቀኝ ክንፍ ቁንጮዎችና ሉላዊ ጌቶቻቸው ከራቢን ሞት በፊት የነበረው የትኛውንም የሰላም ተስፋ ለማጨናገፍ የያዙትን እቅድ የሚያሳይ ነው፡፡
ለራቢን መሞት ሌላው ምክንያት እስራኤል ለሃማስ የምታደርገውን ድጋፍ መቃወሙ ነበር፡፡ በ1992 ወደ 400 የሚሆኑ የሃማስ ሰዎችን ከእስራኤል ያባረረ ሲሆን፣ ከመሞቱ በፊት ባሉ ወራቶች ደግሞ 4,000 የሚሆኑትን አስሯቸው ነበር፡፡ (በቅርቡ በኔታንያሁ የሚመራው አስተዳደር ከሃማስ ጋር የእስረኛ ልውውጥ አድርጓል፡፡) ሃማስ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ የሚል አቋም በመያዝ ከተቃዋሚ ፓርቲ የነበረው ሊኩድ ጋር ጥምረት ፈጠረ፡፡ እንዲህ አይነቱ መረጃ አረፋት ወይም ራቢን ያሰራጩት ፕሮፖጋንዳ ነው የሚለውን ከግምት በማስገባት የ Jerusalem Post  በርእሰ አንቀፁ የሃማስ-ሊኩድ አጋርነት የአምባጓሮ መፍጠርያ ፕሮፖጋንዳ ሳይሆን እንዲህ አይነቱ ጥምረት “የተለመደ እውቀት/ተግባር” (“conventional wisdom”) ነው ይለዋል፡፡ ‘The Hamas-Likud Pairing’ – Jerusalem Post – August 25 1995 – http://www.prisonplanet.com/news_alert_hamas4.html ከትእይንቱ በስተጀርባ ያልተለመደ የአገዛዝ ስልት የለም፡፡ በዚህ ላይ ይበልጥ ለማንበብ የፖል ዋትሰን (Paul J. Watson): Order Out of Chaos ይመልከቱ፡፡ በቀጣይ ምእራፎች ጠለቅ ብለን ስለ ምእራቡና የሙስሊም ፅንፈኞች ህቡእ ትስስር እንዳስሳለን፡፡
ጠላትህን መፍጠር፡ ኢራን፣ ሰሜን ኮርያ እና ቻይና
የሰሜን ኮርያ ገዥዎች ደጋግመው አለምን እንደሚያጠፉ በመዛት ይታወቃሉ፡፡ ሰሜን ኮርያ በጋርዮሻውያን ስርወ መንግስት የምትገዛ አገር ነች፡፡ ሰ.ኮርያ አንድ ሚሊዮን ሰራዊት፣ በሌሎች ግምት ደሞ 4 ሚሊዮን አላት የምትባል አገር ስትሆን፣ ገዢዎቿ ህዝቡን በማስራብና በሰፋፊ ማጎርያ ካምፖች በማከማቸት የስታሊን አርአያን የሚከተሉ ናቸው፡፡ የኢራቅ ገዢዎች ሰብአዊ መብት ጥሰትና ሌሎችም ጉዳዮች ተወንጅለው ሰራዊት ተዘምቶ ተወግደዋል፡፡ ከሰ.ኮርያ ጋር ሲነፃፀሩ ኢራቆቹ የመዋእለ ህፃናት ተማሪዎች ነው የሚሆኑት፡፡ ለሰ.ኮርያ ገዢዎች እንኳን ሊነኩ ቀርቶ በአሜሪካ የኒኩለር አቅማቸው እየተገነባላቸው ነው፡፡ በ1994 በክሊንተን አስተዳደር ስር በተደረገ ስምምነት አሜሪካ የሰ.ኮርያን የኒኩሌር ማብሰልሰያን ወደ ቀላል የውሃ ኒኩሌር ማብሰልሰያ ለመቀየር ተስማማታለች፡፡ መንግስት የከፈላቸው ሙያተኞች ይህ የውሃ ኒኩለር ማብሰልሰያ መሳርያ ለመስራት እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡ ይህ አባባል የኒኩለር መሳርያ ያለማልማት ስምምነት ፖሊሲ ትምህርት ማእከል በዋሽንግተን ሃላፊ የሆነው ሄነሪ ሶኮልስኪ አይስማማበትም፡፡
“ቀላል ውሃ ማብሰልሰያዎች የመሳርያ ደረጃ ያለው ፕሉቶንየም በሰሜን ኮርያም ሆነ በኢራን ደርዘን ቦምቦችን ለመስራት ያስችላሉ፡፡ ይህ ለማንኛውንም የቀላል ውሃ ማብሰልሰያ የሚሰራ እውነት ነው፡- ይህ አሳዛኝ የሆነ እውነታን የዩ.ኤስ. ፖሊሲ አውጪዎች ሊሸሽጉት ችለዋል፡፡” (‘Nuclear Succor for North Korea’ – Matt Bivens – Moscow Times – Septemner 16 2002)
ሶኮሊስኪ በሌላ ግዜም የሚከተለውን ብሏል፡-
እኚህ ማብሰልሰያዎች እንደማንኛውም ማብሰልሰያዎች ናቸው፣ መሳርያ የመስራት አቅም አላቸው፡፡ እናም መጨረሻ ላይ እንዳይኖረው ለምንፈልገው አደገኛ የኒኩሌር ጥሰት ፈፃሚ ለሆነው የኒኩሌር መሳርያ የሚያገኝበትን መንገድ አቅራቢ ልንሆን እንችላለን፡፡ (‘US grants N Korea nuclear funds’ – BBC – April 3 2002)
የዩኤስ ውጭ ጉዳይ ቢሮም ጉዳዩን ያጠናክርልናል፣ የእምነት ቃሉን በመስጠት ሳይሆን ልክ በቲቪ እንደምናያቸው ቀሽም ዋሾዎቻቸው ቢሮውም ይቀባዥራል፡፡ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ቀላል የውሃ ማብሰልሰያዎች ቦምብ ለመስራት አይሆኑም የሚል አቋም የሚያራምድ ሲሆን በ2002 ራሽያ ከኢራን ጋር የምታደርገውነ የኒኩሌር ትብብር ኢራንን የኒኩሌር ማሳርያ ባለቤት እንዳያረጋት እንድታቆም ጠይቃለች፡፡ ራሽያ በኢራን የቀላል ውሃ ማብሰልሰያ ስትገነባ ነበር፡፡ ውጭ ጉዳይ በድረ-ገፁ ለራሽያ በተደጋጋሚ ከኢራን ጋር የምታደርገውን ማናቸውም የኒኩሌር ትብብር የቀለል ውሃ ማብሰልሰያን ጨምሮ እንድታቆም መጠየቁን ገልፅዋል፡፡ (‘State Department on Russia-Iran Nuclear Cooperation’– U.S. Department of State – January 31 2003 -http://usinfo.state.gov/topical/pol/arms/03020321.htm)
እንደቢሮው ከሆነ ቴክኖሎጂው በኢራን ለመሳርያ መስርያ የሚሆን ሲሆን በሰሜን ኮርያ ግን አይውልም፡፡ በዚህ ግን አሜሪካ ኢራን ጡንቻዋን አፈርጥማ ማስፈራርያ እድትሆን አይረዷትም ማለት አይደለም፡፡ ዝርዝሩን በቀጣይ ምእራፎች እናየዋለን አሁን ግን የአሜሪካ ቀኝ እጅ የሆነችው ብሪታንያ ለኢራን የቦምብ ደረጃ ያለው ግብአቶች መስጠቷን እንይ፡፡ አንድ የቢቢሲ ዘገባ እንደሚከተለው ብሎ ነበር፡-
ፕሮግራሙ እንደዘገበው ቃለመጠይቅ ያደረገለት በዩ.ኬ. ዋነኛ የኒኩሌር ጦር መሳርያ ሙያተኛ የንግድና ኢንዱስትሪ መስርያቤቱ ወደ ኢራን እንዲላክ ፈቃድ የተሰጠባቸው የቤሪሊየምና ሌሎች ዝርዝሮች በአጠቃላይ ለኒኩሌር ጦር መሳርያ ፕሮግራም የሚሆኑ ናቸው ይላል፡፡ (‘UK sells bomb material to Iran’ – BBC – September 23 2002)
የቤሪልየም ብረት ለኒኩሌር ጦር መሳርያ ስራ ከመዋል ውጪ ለሌላ ለምንም ነገር አይጠቅምም፡፡
ቻይናስ? ቻይናም ብትሆን ከፀጋው ተቋድሳለች፡፡ ታሊባኖችን ትደግፋለች፣ ከፓኪስታን ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላት፡፡ በዚህ ዙርያ አሜሪካ ምን አደረገች? በቡሽ አስተዳደር ግዜ ለብሄራዊ ደህንነት አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ሲያሸጋግሩላት ነበሩ፡፡ ብቸኛ ጥቅሙ የኒኩሌር ጦር መሳርያ መስራት የሆነ የኮምፒውተር ፕሮግራም ቻይና ተሰጧታል፡፡ (‘High-Tech Transfers To China Continue’ – Zoli Simon – Insight Magazine – July 8 2002) ለቻይና የሚደረግላት ድጋፍ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ከስር ካልታተመው የአሜሪካ የሚስጥር ተቋም የትርጉም መፅሃፋችን የወስደነውን እናንብ፡-
ልክ የቡሽ ቤተሰቦች በመጀመርያ አካባቢ ሶቭየት ህብረትን ሲገነቡ፣ ከዛም ናዚዎችን ፋይናንስ ሲያረጉ፣ በብዥታ ደሞ ከአንጎላ በስተጀርባ እንዳገኘናቸው፣ አሁን ደሞ ቡሽ የሚለው ስም አዲስ ዲያሌክቲክ ክንድ ሲገነባ እናገኘዋለን፡ ኮሚውኒስት ቻይናን፡፡
ሚር. ኒክሰን ጆርጅ በ1971 “ፖፒ” (“Poppy”)  ቡሽን (ከኦርደሩ 1948) በተ.መ.ድ. የዩ.ኤስ. አምባደር አርጎ ሾመ፣ ከዛ በፊት ምንም የዲፐሎማሲያዊ ስራ ልምድ ባይኖረውም’ኳ፡፡ እንደዋና የዩ.ኤስ መልእክተኛነቱ ቡሽ የቻይና ሪፐብሊክን (መጀመርያ ነፃ የተ.መ.ድ. አባል የነበረችውን) ከኮሚውኒስት ቻይና ጥቃት መከላከል ይጠበቅበት ነበር፡፡ መጠቀም የሚችለውን ሰፊ የአሜሪካን ጉልበት á‹­á‹ž ቡሽ በሚያሳዝን አኳኋን ወድቋል፡፡ ሪፓብሊኳ ተባራ ኮሚውኒስት ቻይና ቦታዋን ተረከበች፡፡ ከዚህ ግዙፍ ውድቀት በውኋላ ቡሽ የተባበሩት መንግስታትን ትቶ የሪፐብሊካን ብሄራዊ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሆነ፡፡
ይህ የአሜሪካ እጅ በቻይና ያለውን ጠቅላላ ታሪክ እሚነገርበት ቦታ አይደለም፡፡ የተጀመረው ዎል ስትሪት በ1911 የሰን ያት ሰን (Sun Yat Sen) አብዮት ጣልቃ ሲገባ ነው – እስካሁን ህዝብ በሚያውቀው መልኩ ያልተመዘገበ ታሪክ፡፡
በ2ኛዓ.ጦ. ግዜ á‹©. ኤስ. የቻይና ኮሚውኒስቶች ወደስልጣን እንዲመጡ ረዳቻቸው፡፡ አንድ የቻይና ጥናት ላይ በሚያተኩር ቺን-ተንግ ሊያንግ (Chin-tung Liang) የተባለ ስለ ጀነራል ጆሴፍ ደብሊው. ስቲልዌል (General Joseph W. Stilwell) ከ1942-1944 የዩ.ኤስ. ተወካይ በቻይና ስለሆነው እንደፃፈው ከሆነ፡ “ኮሚውኒዝምን ከመታገል አኳያ ከታየ…(ስቲልዌል) ለቻይና ታላቅኢ-አገልግሎትን አድርጎላታል፡፡” ይላል፡፡ (Chin-Tun Liang, General Stilwell In Chino, 1942-1944: The Full Story. St. John’s University 1972, p. 12.)
ስቲልዌል ከጀነራል ጆርጅ ሲ. ማርሻል ከዋሽንግተን የተላከለትን ትእዛዝ ብቻ ነበር የሚያንፀባርቀው፡፡ አድማይራል ኩክ ለኮንግረስ እንደተናገረው ከሆነ፣ “…በ1946 ጀነራል ማርሻል በስውር መልኩ ቻይናዎችን ትጥቅ አልባ ለማድረግ የጥይት መጓጓዝን እንዲቆም አድርጓል፡፡” ብሏል (Ibid., p. 278.)
ወደ ጀነራል ማርሻል ስንደርስ ግን ማወቅ ያለብን በዩ.ኤስ. የሲቪል ባለ ስልጣኑ በወታደራዊ ጉዳይ የመጨረሻው ቃል ያለው መሆኑንና ይህ ደሞ ወደጦር ሹሙ (ሚ/ሩ) ሄነሪ ስቲምሰን (Henry L. Stimson) ይወስደናል-የማርሻል የበላይና የኦርደሩ አባል (ከኦርደሩ1888)፡፡ በሚገርም መገጣጠም በ1911 በሰን ያት ሰን አብዮት ግዜ የጦር ሹም የነበረው እራሱ ስቲምሰን ነበር፡፡
ቻይናን የመካድ ታሪክና የኦርደሩ ሚና ሌላ ቅፅ መጠበቅ ሊኖርበት ነው፡፡ ለአሁን ግን የኮሚውኒስት ቻይናን እንደአዲስ የዲያሌክቲኩ ክንድ ለመገንባት የተወሰደውን ውሳኔ ብቻ ለማስመዝገብ እንፈልጋለን – በፕሬዚደንት ሪቻርድ ኒክሰን የተወሰደ እርምጃና ወደትግበራ የተገባው በሄነሪ ኪሲንጀር (ቼዝ ማንሃተን ባንክ) እና ጆርጅ “ፖፒ” ቡሽ (ከኦርደሩ) ነው፡፡
ይህ ስራ ወደ ህትመት እየተሄደ እያለ (በ1984 መጀመርያ) ባችቴል ኮርፖሬሽን አዲስ ባችቴል ቻይና ኢንክ. (Bechtel China, Inc.)የተባለ ካምፓኒን መስርቷል -ልማትን፣ ኢንጂነሪንግንና ኮንስትራክሽን ኮትራቶችን ለቻይና መንግስት ሊይዝ፡፡ የባችቴል ቻይና ኢንክ. አዲሱ ፕሬዚደንት ሲድኒ ቢ. ፎርድ ነው፣ ቀድሞ የባችቴል ሲቪልና ሚነራል ኢንክ. ማርኬቲንግ ማናጀር የነበረ፡፡ አሁን ባችቴል እየሰራ የሚገኘው ለቻይና ብሄራዊ ከሰል ልማት ኮርፖሬሽንና ለቻይና ኦፍሾር ኦይል ኮርፖሬሽን ጥናትን ነው- ያው ሁለቱም የቻይና ኮሚውኒስት ድርጅቶች ናቸው፡፡
ይህ እንግዲ የሚመስለው ምንድን ነው ዲትሮይት ከነበረው አልበርት ካን ኢንክ. (Albert Kahn, Inc) የተጫወተውን ሚና ሊጫወት ነው ማለት ነው – አልበርት ካን በ1928 ለሶቭየት ህብረት የመጀመርያውን አምስት አመት እቅድ ቅድመ ጥናት ያካሄደው ድርጅት ነው፡፡
በ2000 ዓ.ም. ኮሚውኒስት ቻይና “ልእለ-ሃያል” ሃገር ትሆናለች ማለት ነው፣ በአሜሪካ ቴክኖሎጂና ሙያ ተገንብታ፡፡ [ይህን ሲፅፍ1984 ላይ ሁኖ ነበር፣ በውነትም የኦርደሩን እንቅስቃሴ መተንበይ ችሏል፣ ዛሬ ቻይና ምን ላይ እንደምትገኝ እናውቃለንና፡፡] የኦርደሩ አላማ ነው ተብሎ አንደሚገመተው ይህን ሃይል ከሶቭየት ህብረት ጋር በግጭት መስመር ውስጥ እንደሚያስገባ ነው፡፡
ባችቴል ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ጥርጥር የለውም፡፡ የቀድሞ የሲ.አይ.ኤ. ዳይሬክተር ሪቻርድ ሄልምስ ለባችቴል ይሰራል፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበረው ጆርጅ ሹልትዝና (George Shultz) መከላከያ ሚኒስቴር የነበረው ካስፓር ዌንበርገርም (Caspar Weinberger)ቢሆኑ ለባችቴል እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አንዱ ከዋሽንግተን ያለ ከብሄራዊ ደህንነት ጋር የተያያዘ እቅድ አውጪ ከመስመር ወጥቶ ቢቃወም ይህ በቂ ሃይለኛ ተፅእኖ አድራጊ ጥምረት ይገጥመዋል፡፡
ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን ኦርደሩ የተሳሳተ ስሌት አድርጓል፡፡ ለዚህ ዲያሌክቲክ ለውጥ የሞስኮ ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል? ከተለመደው የራሽያ የጥርጣሬ በሽታ ውጪም ቢሆን እዚህ ላይ ትንሽ ጭንቀት ቢያሳዩ ይቅር ሊባሉ ይገባል፡፡ ማን ነው የቻይና ኮሚውኒስቶች ከ2000 በውኋላ ከሞስኮ ጋር ሰላም ፈጥረው ልእለ-ልእለ-ሃያል የሆነች ዩ.ኤስ.ን ለማስወገድ አይጣመሩም ያለው?
ሌሎች የሽብር አገዛዝ ምሳሌዎች
የቬትናም ጦርነትን ያስጀመረው የቶንኪን ባህረ ሰላጤ ክስተት (The Gulf of Tonkin) በሁለት ገጠመኞች ላይ ተመስርቶ ነበር፡፡ ከኬነዲ መሞት በውኋላ የተተካው ሊንደን ቢ. ጆንሰን አስተዳደር ሰሜን ቪየትናም ላይ ጦርነት እንዲያውጅ ያደረገው፡- የመጀመርያው ትንኮሳ ሲሆን የአሜሪካ መርከብ ላይ ደረሰ የተባለው ጥቃት የአሜሪካ ጥፋት ነበር፡፡ (ያለ ቦታው ለስለላ የሄደ የአሜሪካ መርከብ ስለነበር ተንኳሿ እራሷ አሜሪካ ነች፡፡) ሁለተኛው ደግሞ ባዶ ሜዳ ላይ በመተኮስ ተጠቃን ተብሎ የተተወነ ፈጠራ/ውሸት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ በዚህ ጦርነት አንድ ሚሊዮን ቪየትናማውያንና 58,000 አሜሪካውያን ሂወታቸውን አጥተዋል፡፡
የኦክለሆማ ከተማ ፍንዳታ የቀኝ ዘመም ፅንፈኛ ሚሊሻዎች ያደረሱት ጥቃት ነው ተብሎ የተፈረጀው የሽብር ጥቃት ብዙ ክፍተቶች ያሉበት ነበር፡፡ በፍንዳታው የተጠቃው ህንፃ ሙራ ፌደራል ህንፃ (Murrah Federal Building) እንዲያፀዳው ስራው የተሰጠውControlled Demolition, Inc. ለተባለው ድርጅት ነበር፣ ይህ ድርጅት የዓለም ንግድ ማእከል ከፈረሰ በኋላም እንዲጠራርገው የተደረገው ነው፡፡ ፖሊስ በዚህ ህንፃ ፅንፈኞቹ የተባሉት በመኪና ደጅ ካስቀመጡት ውጪ ህንፃው ውስጥ የተጠመዱ ሁለት ፈንጆችን አግኝቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ጋዜጠኞችም ዘግበውታል፡፡ ጡረታ የወጣው ብርጋዴር ጀነራል ቤንቶን ኬ. ፓርቲን (Benton K. Partin) በፍንዳታ ልዩ ሙያተኛና በዩ.ኤስ. አየር ሃይል የ31 ዓመት ልምድ ያለው ሙያተኛ በ1997 ለዩ.ኤስ. ምክርቤት ህንፃው ከደጅ መኪና ላይ በተጠመደ ሳይሆን ከውስጥ በተጠመዱ ፈንጆች እንደወደመ የሚያሳይ ማስረጃ ፅሁፉን አንብቦ ነበር፡፡ በዚሁ ዓመት á‹©.ኤስ. ኢንግሊን፣ ፍሎሪዳ ያለው አየር ሃይል በሙራ ህንፃ ፍንዳታ ላይ ያደረገውን የ56 ገፅ ጥናቱን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ የብርጋዴር ጀነራሉን ግኝት የሚደገፍ ነበር፡፡ አው – በነገራችን ላይ እንደሁልግዜው ባካባቢው የነበሩ የጥበቃ ምስል መቅረጫዎች የቀረፁት ምስል ለህዝብ ይፋ አልሆነም፣ እንደሁልግዜው አደረጉት ከተባሉት ውጪ ሌሎች ፊቶች ሲሰሩ እንዲታዩ አይፈለግምና፡፡ ምንጭ antiglobalconspiracy
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 12 years ago on October 27, 2012
  • By:
  • Last Modified: October 27, 2012 @ 9:48 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar