www.maledatimes.com ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና ልኡካን አባቶች ረቡዕ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋራ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ፤ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ዛሬ መግለጫ ይሰጣሉ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና ልኡካን አባቶች ረቡዕ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋራ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ፤ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ዛሬ መግለጫ ይሰጣሉ

By   /   July 29, 2018  /   Comments Off on ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስና ልኡካን አባቶች ረቡዕ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋራ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ፤ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ዛሬ መግለጫ ይሰጣሉ

    Print       Email
0 0
Read Time:2 Minute, 32 Second

abune merqorewos back to ethiopia

  • በመጪው መስከረም ለመመለስ ቢያስቡም፣ በጠ/ሚሩ ጥሪ አሳጠሩት፤
  • የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአቀባበል ዐቢይ ኮሚቴ ዝግጅቱን እያጣደፈ ነው፤
  • በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ፣ከ17 በላይ የተሟሉ ማረፊያዎች ተዘጋጁ፤
  • ይፋዊ የአቀባበል መርሐ ግብሩ፣ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይከናወናል፤
  • “ለመቀበል እየተዘጋጀን ነው፤ታላቅ ደስታ ነው፤”/ብፁዕ ዋና ሥ/አስኪያጁ/

†††

የቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊ አንድነት በአባቶች ዕርቀ ሰላም መመለሱን ተከትሎ፣ ላለፉት 26 ዓመታት በአሜሪካ በስደት የቆዩት 4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በመጪው ሳምንት ረቡዕ፣ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ሀገራቸው እንደሚመለሱ ተገለጸ፡፡

“ግንቡን እናፍርስ፤ ድልድዩን እንገንባ” በሚል መሪ ቃል በዚያው በአሜሪካ፣ ከኢትዮጵያውንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋራ በመወያየት ላይ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ትላንት ቅዳሜ፣ ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠዋት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን አግኝተው አነጋግረዋቸዋል፡፡

FB_IMG_1532731037091

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባረፉበት ሆቴል በተዘጋጀው የቁርስ መርሐ ግብር ላይ በተደረገው በዚሁ ውይይት፣ ቅዱስነታቸው በተቻለ ፍጥነት ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ ዶ/ር ዐቢይ ጠይቀዋቸዋል፡፡ ከተቻለና ፈቃደኛ ከኾኑም፣ ከእርሳቸው ጋራ ወደ ሀገራቸው መምጣት እንደሚችሉ ገልጸውላቸዋል።

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስም፣ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ያቀዱት፣ በመጪው ዓመት መስከረም 8 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደነበረ ቢገልጹም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው፣ በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ፣ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ ላለፉት 26 ዓመታት በስደት ወደተለዩዋት ሀገራቸው ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ አስታውቀዋል፡፡

ከቅዱስነታቸው ጋራ አብረው ከሚመለሱት መካከል፣በኹለቱም ወገን በዕርቀ ሰላም ውይይቱ የተሳተፉት ስድስቱ ልኡካን አባቶች እንዲሁም የሰላምና አንድነት ኮሚቴው አባላት እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

37880248_1833264223430975_2632994675354501120_n

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በፓትርያርክነት ክብርና ደረጃ ወደ ቅድስት ሀገራቸው ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ፤ በመንበረ ፓትርያርኩም፣ ደረጃውን የጠበቀ ማረፊያ ተዘጋጅቶና የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ ተሟልቶ በጸሎትና ቡራኬ በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እያገለገሉ እንደሚቀመጡ በስምምነቱ ተገልጿል፡፡

“በሱባኤና በጸሎት ሲተጉ ለነበሩት ብፁዓን አባቶችና ምእመናን ምስጋና ይኹንና የመለያየቱ ጊዜ አብቅቷል፤” ሲሉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ቅዱስነታቸውንና ወንድም አባቶችን፣ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን በታላቅ ደስታ ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ እንዳለ አስታውቀዋል፡፡

በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት፣በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሰብሳቢነት የሚመራና ከጠቅላይ ጽ/ቤቱ መምሪያ ሓላፊዎች የተውጣጣ ዐሥር አባላት ያሉት የአቀባበል ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየሠራ እንዳለ ብፁዕነታቸው ተናግረዋል፡፡ የሥነ ጽሑፍና ሚዲያ ኮሚቴ (በምክትል ሥራ አስኪያጅ ርእሰ ደብር መሐሪ ኃይሉ)፣ የፕሮቶኮል ኮሚቴ(በመጋቤ ሰላም ሰሎሞን ቶልቻ)፣ የጸጥታና ሥርዐት ኮሚቴ(በሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ)፣ የካህናት አስተባባሪ ኮሚቴ(በመጋቤ ካህናት ኃይለ ሥላሴ ዘማርያም)፣ የሰንበት ት/ቤቶች አስተባባሪ ኮሚቴ(በመ/ር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ)፣ የትራንስፖርት ኮሚቴ(በአፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት)፣ የመድረክ ዝግጅት ኮሚቴ(በሊቀ ኅሩያን ሠርጸ አበበ)፣ የመስተንግዶ ኮሚቴ(በመ/ር ኤርሚያስ ተድላ)፣ የማረፊያ ቤት ዝግጅት ኮሚቴ(በመጋቤ ሐዲስ ሐዋዘ ብርሃን ጫኔ) እየተመሩ ቅድመ ዝግጅቱ እየተጣደፈ ይገኛል፡፡

FB_IMG_1532731453359

የፕትርክና መንበሩንና የባለጉዳይ ማነጋገሪያን ጨምሮ አስፈላጊው ነገር የተሟላለት መቀመጫና ቢሮ በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ፣ ለ4ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ መዘጋጀቱ ተጠቅሷል፡፡ የቀድሞው የግብጹ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ የተስተናገዱበት ሲኾን፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጽ/ቤት ኹኖም አገልግሏል፡፡ በዚሁ ሕንፃ የሚገኙ ከ17 ያላነሱ ሌሎች የተሟሉ ዘመናዊ ክፍሎችም፣ ከቅዱስነታቸው ጋራ ለሚመጡ አባቶችና ልኡካን ማረፊያነት ዕድሳታቸውና ጽዳታቸው ተጠናቆ እንደተዘጋጁ ታውቋል፡፡

ቅዱስነታቸው የሚመለሱበት ኹነኛ ቀን ከታወቀበት ከትላንት ቅዳሜ ማምሻውን ጀምሮ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አስቸኳይ ስብሰባ የተጠራው ዐቢይ ኮሚቴው፣ ዛሬም ቅድመ ዝግጅቱን በየዘርፉ ሲያከናውን ውሏል፤ በቤተ ክርስቲያን ደረጃ የታቀደው ይፋዊ አቀባበል፣ ቅዱስነታቸውና ልኡካን አባቶች የፊታችን ረቡዕ በገቡበት ሰዓት፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡ ይህን አስመልክቶም፣ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ዛሬ እሑድ ከቀኑ 10 ሰዓት፣በጽ/ቤታቸው መግለጫ እንደሚሰጡ ተጠቁሟል፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 6 years ago on July 29, 2018
  • By:
  • Last Modified: July 29, 2018 @ 5:47 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar