
የትምባሆ፣ የአልኮል፣ የመድኃኒትና ምግብ ነክ ምርቶችን ለመቆጣጠር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ አዋጅ የበለጠ ጥብቅ እንዲሆን የጤናጥበቃ ሚኒስትሩ ምክር ቤቱን ጠየቁ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕፃናት ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር ለመመርመር ዛሬ ረቡዕ ታኅሳስ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ሕዝባዊ የውይይት መድረክ ላይ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር አሚር አማን በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጡ ክልከላዎች በቂ አለመሆናቸውንበመገንዘብ ክልከላዎቹ የበለጠ ጥብቅ እንዲሆኑ የማሻሻያ ሐሳብ ለቋሚ ኮሚቴው አቀረቡ።
ካቀረቧቸው ጥብቅ የማሻሻያ ክልከላዎች መካከል እንደ ቢራ ያሉ የአልኮል ምርቶች በኤሌክትሮኒክ ሚዲያዎች ማለትም በሬዲዮና በቴሌቪዥን ከምሽቱ 3፡00ሰዓት እስከ ሌሊት 12፡00 ሰዓት ብቻ እንዲተዋወቁ በረቂቁ ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ተሻሽሎ፣ የአልኮል ምርቶች በተጠቀሱት ሚዲያዎች ሙሉ ለሙሉእንዳይተዋወቁ ክልከላ እንዲጣል የሚል የማሻሻያ ሐሳብ አቅርበዋል።
የአልኮል ምርቶች ማለት የአልኮል ይዘታቸው ከሁለት በመቶ በላይ መሆኑን የሚገልጸው የረቂቅ አዋጁ ትርጓሜ ተሻሽሎ የአልኮል ይዘቱ ከ0.5 በመቶ በላይበሚል እንዲሻሻልም የጠየቁ ሲሆን፣ ለዚህ ያቀረቡት ምክንያትም አልኮል የሚያመርቱ ኩባንያዎች ከሁለት በመቶ በታች የሆኑ የአልኮል ምርት ዓይነቶችንበማምረት የአልኮል መጠጦች በተጠቀሱት ሚዲያዎች እንዲተዋወቁ ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ነው።
የአልኮል መጠጦችን ለማስተዋወቅና ገበያውን ለማስፋት ከፍተኛ ሽልማቶችን የሚያስገኙ ዕጣዎችን በቆርኪ ላይ ማያያዝ ክልከላ እንዲደረግበትም ሐሳብአቅርበዋል።
ሚኒስትሩ እነዚህ ጥብቅ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ቋሚ ኮሚቴውን በጽሑፍ መጠየቃቸውን ተናግረዋል። ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በሕዝባዊ ውይይትመድረኩ ላይ የተገኙ የጤና ባለሙያዎች፣ ታዋቂ አርቲስቶች፣ ወጣት ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻዎች ረቂቅ አዋጁ የበለጠ ጥብቅ እንዲሆንና የአልኮልማስታወቂያ እንዲቆም በተደጋጋሚ በመጠየቃቸው ነው።
የትምባሆና አልኮል ሽያጭን በተመለከተ ረቂቅ ሕጉ ላይ ሁለቱም ምርቶች ከ18 ዓመት ዕድሜ በታች እንዳይሸጡ የሚደነግገው አንቀጽ ተሻሽሎ ከ21 ዓመትበታች እንዲባል ጠይቀዋል። ይኼን ሐሳብም በሕዝባዊ የውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት አብዛኞቹ ደግፈውታል።
የኢትዮጵያ ትምባሆ ኢንተርፕራይዝ የሥራ ኃላፊዎች በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው ረቂቅ የቁጥጥር ሕጉ በኩባንያው ላይ ሊያደርስ ይችላል ያሏቸውንሥጋቶች አንስተዋል።
ካነሷቸውም ሥጋቶች መካከል ዋነኛው በረቂቁ የተቀመጡ የቁጥጥር ሕጎች የኮንትሮባንድ የሲጋራ ንግድን ያበረታታል የሚል ነው። ይኼም ከሥጋት ባለፈተጨባጭ መሆኑን ለማስረዳት በአሁኑ ወቅት እንኳን የአገሪቱ የሲጋራ ገበያ 44 በመቶው በኮንትሮባንድ በሚመጡ ምርቶች የተያዘ መሆኑን አንስተዋል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ምላሽ አጠቃላይ የኮንትሮባንድ ንግድን በተመለከተ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንጠቅሰው፣ የሲጋራ ኮንትሮባንድ ንግድን በተመለከተ ግን የትምባሆ አምራች ኩባንያዎች ጥብቅ የቁጥጥር ሕግ መንግሥታት እንዳያወጡባቸው ሲሉ ራሳቸውየኮንትሮባንድ የሲጋራ ንግድ እንዲስፋፋ በማድረግ አልያም መስፋፋቱን በመደገፍ መንግሥት የቁጥጥር ሕግ ቢያወጣ ኮንትሮባንድ እንዲስፋፋ ከማድረግየዘለለ ትርጉም እንደማይኖረው ለማስመሰል እንደሚሞክሩ ለመድረኩ አስረድተዋል።
ከመድኃኒት አስመጪዎችም በርከት ያሉ ሥጋቶች የተነሱ ሲሆን፣ ቋሚ ኮሚቴው የተነሱትን በግብዓትነት ወስዶ ተጨማሪ የውይይት መድረክ መጥራት አስፈላጊመሆኑን ካመነበት የሚከለክለው ነገር ባለመኖሩ ሊጠራ እንደሚችል ገልጿል።
ይሁን እንጂ ረቂቅ አዋጁ የንግድ ጥቅማቸውን የሚነካባቸውም ሆኑ ሌሎች ለቋሚ ኮሚቴው አመራሮችና አባሎች በግል ስልካቸው ላይ በመደወል ማስቸገርእንደሌለባቸውና ተግባሩ እንዲቆም አሳስበዋል።
Average Rating