በተያዘው የበጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ 48 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንደሚጀመር ቢታቀድም፣ ግንባታው ሳይጀመር የበጀት ዓመቱ የመጀመርያው ስድስት ወራት ተጠናቀቁ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶቹን ግንባታ ለማካሄድ አቅዶ የነበረው በቦሌ ክፍለ ከተማ፣ በቦሌ አራብሳ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ በኮዬ ፊጬ አካባቢዎች በሚገኙ ስምንት ሳይቶች ነበር፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች ልማት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዘርይሁን ዓምደ ማርያም (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቤቶቹን ግንባታ ማካሄድ ያልተቻለው ቦታዎቹ ከይገባኛል ነፃ መሆን ስላልቻሉ ነው፡፡
‹‹የከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ቦታዎቹን ነፃ አድርጎ እንዲያስረክበን ወይም ተለዋጭ መሬት እንዲሰጠን ጠይቀናል፤›› ሲሉ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በሁለት ክፍላተ ከተሞች ከሚገኙ ስምንት ቦታዎች በአጠቃላይ 500 ሔክታር መሬት ተዘጋጅቷል ከተባለ ሦስት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ በምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የሚመራው የከተማው አስተዳደር ግንባታውን ለማካሄድ ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅት፣ ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች መኖራቸውን መረዳቱ ተገልጿል፡፡
የመሬት ዝግጅቱ የተካሄደው በቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ጊዜ ቢሆንም፣ በምክትል ከንቲባ ታከለ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ሥልት የሚያራምድ በመሆኑ በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ የማካሄድ ፍላጎት አለማሳየቱን የሚናገሩ አሉ፡፡
በኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ የተሰማሩ ኮንትራክተሮች እንደሚናገሩት፣ አዲሱ አስተዳደር የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በማስፋፊያ አካባቢዎች ከመገንባት ይልቅ በመሀል ከተማ በሚገኙ ቦታዎች ማካሄድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው የሚል አቋም ይዛል፡፡
ምክትል ከንቲባ ታከለ በተደጋጋሚ እንደገለጹት፣ ከዚህ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄድ ልማት ነባር ነዋሪዎችን አካቶ እንጂ አፈናቅሎ አይደለም፡፡ በመሀል አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎችን ማፈናቀል አርሶ አደሩንም ማፈናቀል ስለሆነ፣ ይህንን አሠራር ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ነዋሪዎችን በቦታቸው የሚያቅፍ ልማት ተመራጭ መሆኑን ምክትል ከንቲባው ይናገራሉ፡፡
ኮንትራክተሮቹ በምክትል ከንቲባው ሐሳብ ቢስማሙም፣ ነገር ግን ሥጋታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ኮንትራክተሮቹ እንደሚሉት፣ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ስታንዳርድ መሠረት በአንድ ቦታ አምስት ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤቶች መገንባት አለባቸው፡፡ የቤቶቹን ግንባታ ለማካሄድ ቢያንስ 50 ሔክታር መሬት ያስፈልጋል፡፡
በማስፋፊያ አካባቢዎች በዚህ ደረጃ ስፋት ያላቸውን ቦታዎች ማግኘት ብዙም ከባድ አይደለም፡፡ በቦሌ አራብሳና በኮዬ ፊጬ አካባቢዎች 500 ሔክታር መሬት ለ48 ሺሕ ቤቶች ግንባታ ተዘጋጅቶ ነበር በማለት ያስረዳሉ፡፡
ኮንትራክተሮቹ እንደሚሉት በመሀል ከተማ ይኼንን ያህል ስፋት ያለው መሬት ማግኘት የሚከብድ ነው፡፡ የመኖሪያ ቤት ለማግኘት ተመዝግበው የሚጠባበቁ ነዋሪዎችንም ብዙ ሊያስጠብቅ ይችላል በማለት ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በ20/80 ፕሮግራም 94,114 ቤቶች፣ በ40/60 ፕሮግራም 38,240 ቤቶች ከ2010 ዓ.ም. በፊት ተጀምረው በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ግንባታ ሲጀመር በ18 ወራት ይጠናቀቃል ቢባልም፣ እየሆነ ያለው ግን ከአራት ዓመታት በላይ ሳይጠናቀቁ መቆየታቸው ነው፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ይጀመራሉ የተባሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለመጀመራቸው፣ ተመዝግበው ለሚጠባበቁ ነዋሪዎችም ከፍተኛ የቅሬታ መንስዔ እየሆኑ ነው፡፡
Average Rating