www.maledatimes.com የአዱዋው ድል አብነት! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአዱዋው ድል አብነት!

By   /   May 1, 2020  /   Comments Off on የአዱዋው ድል አብነት!

    Print       Email
0 0
Read Time:9 Minute, 20 Second

https://www.youtube.com/channel/UCqAuXzJD_f5q7zV1ItVKAdA?view_as=subscriber 

ከእኛ ጋር በተለያዩ መረጃዎች መቆየት ይፈልጋሉ እንግዲያውስ ዩቲዩባችንን በመከተል አብረውን ይሁኑ አዳዲስ መረጃዎች እናደርስዎታለን

(በሰሎሞን ተሰማ ጂ.) 

  1. መግቢያ፤

የአዱዋውን ድል የተጎናፀፍንበት ዕለት፣ በአለማችን ላይ ከተከሰቱት 15ቱ ታላላቅ ቀናት መካከል የምናስቀምጠው ነው፡፡ በአዲስጉዳይ መጽሔት ላይ  በሁለት ተከታታይ መጣጥፎች እንደገለጽኩት፣ የሰውን ልጆች ሰብዓዊ ክብርና የመንፈስ ሙላት ላቅ በማድረግ ከሚወሱት/ከሚጠቀሱት ቀናት መካከል አንዱ፣ “የአዱዋው ድል” ነው፡፡ የድሉ አብነት/ተምሳሌት፣ ብሎም የዘር-መድሎን በመፈወስ ሃይሉና የእኩልነትን አዋጅ በማወጅ አቅሙ አዱዋን የሚስተካከል የለም፡፡ ድሉ፣ የስልጡኗ አውሮፓንና የኋላ-ቀሯን አፍሪካ ጦርነት ነው የአሸናፊዎች አሸናፊ መለያም ነው፡፡ አንዳንድ ተንታኞች ደግሞ አልፈው-ተርፈው “የጥቁሮችና የነጮች ፍልሚያ” አድርገው ተመልክተውታል፡፡ የሃይማኖትን ታሪክ አጥኚ የሆኑት ምሁራን በበኩላቸው፣ የካቶሊካዊቷ ሮማና የኦርቶዶክሳዊቷ ኢትዮጵያ ፍልሚያ አድርገው አስበውታል፡፡ እርግጥ ነው፣ የጊዮርጊስ ጽላት/ታቦትና አቡኑና እጨጌውም በጦርነቱ ሥፍራ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል፣ በአድዋው ጦርነት ወቅትና ከአርባ ዓመታት በኋላ በተደረገው የአምስት ዓመቱ የወረራም ዘመን ጅማሮ ላይ የሮማ ሊቃነ-ጳጳሳት በአደባባይ ተገኝተው የፋሺስትን ጦር በካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ስም ባርከው ልከዋል፡፡ በመሆኑም፣ ጦርነቱ የጊዮርጊስ ጽላት/ታቦት ተሸክመው የዘመቱት “ኦርቶዶክሳዊያን” እና በሊቀ-ጳጳሳቶቻቸው ቡራኬ አገር እንዲያቀኑ ተባርከው የተሸኙት “ኮተሊኮች ጦርነት” ሆነ፡፡ ውጤቱም ለኦርቶዶክሳውያኑ ያደላ ሆነ፡፡

  1. በአዱዋ ጦርነት ዋዜማ፤

የአዱዋ ጦርነት መንስኤ የታወቀው የውጫሌ ውል ነው፡፡ (ውጫሌ በአንባሰልና በየጁ መካከል የሚገኝ፣ ለሐይቅ እስጢፋኖስ ቀረብ ያለ ቦታ ስም ነው፡፡) ይህ ስምምነት ሃያ አንቀፆች ያሉት ሲሆን፣ በሚያዝያ 25 ቀን 1881ዓ.ም ተፈረመ፡፡ ለውዝግቡም ጉልሁን ድርሻ የሚወስደው “አንቀጽ 17” የተባለው አንቀጽ ነበር፡፡ ውሉን ከፈረንሳይኛ ወደ አማርኛ የተረጎሙት (ወይም የአማርኛውን ዘር ያረቀቁት ሰው፣) ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሤ ይባላሉ፡፡ የጣሊያንኛውንም ቅጂ ያሰናዳው አንቶንሌ ነበር፡፡ አንቶንሌ ከአስር ዓመታት በላይ አንኮበርና በእንጦጦ አብያተ-መንግሥታት አካባቢ ስለኖረ አማርኛን አቀላጥፎ ይናገራል፡፡ ስለሆነም የሕጋዊ ዘይቤና አገባብ ያላቸውን ቃላትና ፍቺዎቻቸውንም አብጠርጥሮ እስከማወቅም ደርሶ ነበር፡፡ በዚህም እውቀቱ ተጠቅሞ በአማርኛና በጣሊያንኛ የተለያዩ ትርጓሜዎች ያሉትን አንቀጽ 17ን አሰናዳ፡፡ የአማርኛው እንዲህ ይላል፤ “የኢትዮጵያ መንግሥት ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር መገናኘት ከፈለገ የኢጣሊያንን መንግሥት አገልግሎት ሊጠቀም ይችላል፤” ሲል-የጣሊያንኛው ቅጂ ደግሞ “የኢትዮጵያ መንግሥት ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር መገናኘት ከፈለገ የኢጣሊያንን መንግሥት በኩል ይገለገላል፤” ይላል፡፡

አንቶንሌ የሸረበው ተንኮል “በገዛ ዳቦው፣ ልብ-ልቡን አሳጣሁት!” ዓይነት ነው፡፡ ለአማርኛ አንባቢዎች የሚስማማ ሃረግ ነው ያለውን “ሊጠቀም ይችላል” ብሎ አስረቀቀ፡፡ (ውዴታንና ፈቃደኛነትን የሚጠቁም ነው፡፡ የኢጣሊያንን መንግሥት አገልግሎት ካልፈለገ ደግሞ፣ “አለመጠቀምም ይችላል” ማለት ነው፡፡ በአማርኛው ላይ ያለው ሃረግ፣ የጣሊያንን መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት “ወዳጅ/Partner” አድርጎ ይደነግጋል፡፡) ለጣሊያንኛ ተናጋሪ ጌቶቹ ደግሞ “ይገለገላል” የሚል አስገዳጅ ቃል አሰናድቶ ሰጣቸውና አስደሰታቸው፡፡ (በዚህ ቃልም መሠረት፣ ጣሊያን የኢትዮጵያ “ገዢ” ሆነች ማለት ነው፡፡ ወዳጅነት የለም፤ ያለው ገዢነትና ተገዢነት ነው፡፡ የአንቶንሌ ሤራ መጋለጥ የጀመረው ወዲያውኑ ነበር፡፡ የጣሊያንኛው ቅጂ እንደደረሳቸው፡- የሩሲያ መንግሥት ወዲያውኑ ውድቅ ሲያደርገው፡፡  የፈረንሳይ መንግሥት ደግሞ ትልቅ የጥያቄ ምልክት አስቀምጦበት ነገሩን ለኢትዮጵያ መንግሥትም አስታወቀ፡፡ (ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ ዳግማዊ ምኒልክ-የአዲሱ ሥልጣኔ መስራች፣ 1956ዓ.ም፣ ገጽ-226፡፡)

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በጥቅምት 25 ቀን 1882ዓ.ም በእንጦጦ ማርያም ቤተ-ክርስቲያን “ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” ተብለው ነገሡ፡፡ ይህንን ክብርና ማዕረግ ለመቀዳጀት ዐስር ዓመታት ያህል ታግሰዋል፡፡ ያንን ትዕግሥታቸውንም በማውሳት እንዲህ ተብሎ ተዘመረላቸው፤ “እንታገል ይላል፣ ጉልበቱን ያመነ፤ መጣል እንዳንተ ነው እያመነመነ፡፡” ተባለላቸው፡፡ ይሄንኑም የንግሥና በዓላቸውንና ንጉሠ ነገሥትነታቸውን ለአውሮፓ መንግሥታት ለማስታወቅ ደብዳቤ ፃፉ፡፡ ከሩሲያና ፈረንሳይ መንግሥታት በስተቀር፣ ሌሎቹ የአውሮፓ መንግሥታትም “በገዢያችሁ የጣሊያን መንግሥት በኩል ይድረሰን እንጂ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የምናደርገው ምንም ዓይነት የዲፕሎማሲ ግንኙነት አይኖረንም!” ሲሉ በራቸውን ጠረቀሙ፡፡ ይህ ብሔራዊ ክብርንና ኩራትን የሚያሳጣ ሤራ የተነደፈው በአንቶሌ ስለነበረ፣ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በቀጥታ ለጣሊያኑ ንጉሥ ኡምቤርቶ በጥቅምት 4/1883ዓም ዳብዳቤ ጻፈ፡፡ የደብዳቤውም ይዘት፣ “አንቀጽ-17 ከውጫሌው ውል እንዲሰረዝ፤” የሚል ትዕዛዝ አዘል መልዕክት ነበር፡፡

ያሤረው ተንኮል የተጋለጠበት አንቶንሌ ሲገሰግሥ ከሮም ተነስቶ ሸዋ ደረሰ፡፡ በየካቲት 4/1883ዓ.ም ቤተ-መንግሥት ቀረበ፡፡ ከአንድ ሀገር መንግሥት መልዕክተኛ በማይጠበቅ ኹኔታም ብልግናን አሳየ፡፡ የውጫሌውን ውል አንድ ቅጂ ብጭቅጭቅ አድርጎ እፊታቸው ወረወረው፡፡ በስፍራው የነበሩትም ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በአስቸኳይ አገር ለቆ እንዲወጣ አደረጉት፡፡ ከዚያ በኋላም የጣሊያን መንግሥት አፄ ምኒልክን እንደምንም አግባብቶ፣ አንቀጽ-17ን ሳይሰረዝ እንዲቆይ ለማድረግ መጣር ጀመረ፡፡ በመሆኑም፣ ዶ/ር ትራቬርሲ የሚባል ፀጉረ-ልውጥ ሰው ወደሸዋ ላከ፡፡ በየካቲት 1885ዓ.ም መግቢያ ላይ፣ ዶ/ሩ ከጣሊያን መንግሥት በተገኘ ብድር 2,000,000/ሁለት ሚሊዮን ጥይት  ለእጅ መንሻ ገዝቶ አምጥቶ ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ መልዕክተኛውን በጨዋነት ካስተናገዱ በኋላ፣ በየካቲት 25/1885ዓ.ም የውጫሌ ውል በተግባር መፍረሱን ለአውሮፓ መንግሥታት አስታወቁ፡፡ ይሄንንም ሲያደርጉ፣ ከጣሊያን መንግሥት ተበድረውት የነበረውን ብድር በሙሉ ከፍለው እንዳጠናቀቁ ነበር፡፡ ዶ/ር ትራቬርሲም እስከ ሰኔ-1885ዓ.ም ድረስ አዲስ አበባ ቆይቶ የመጣበት ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ አንዳችም ጋት ፈቀቅ ሳይል ወደሀገሩ ተመለሰ፡፡ (ዳግማዊ አፄ ምኒልክም ውስጥ-ውስጡን ሠራዊታቸውን በማደራጀትና የሕዝቡን ወኔ ለጦርነቱ በመቀስቀስ ለወሳኙ ጦርነት ሲዘጋጁ ከረሙ፡፡ አራሹ ማሳውን ሲያርስ፣ አረሙንም ሲያርም ቆየ፤ ነጋዴውም ሲነግድ፣ ካህናቱም ሲሰብኩና ሕዝቡን ለመስዋዕትነት ሲያዘጋጁት ከረሙ፡፡ በመስከረምም አጋማሽ ላይ ሽንብራው ተዘርቶ እንዳለቀ “ምታ ነጋሪቱን፣ ክተት ሠራዊቱን!” አወጀ፡፡

በአዱዋው ጦርነት ዋዜማ ላይ (ከሰኔ 1885 እስከ ጥቅምት 1888ዓ.ም ድረስ) ኢትዮጵያና ጣሊያን በየፊናቸው ዝግጅቶቻቸውን ሲያድርጉ ከረሙ፡፡ በጣሊያን በኩል የተለመደውን ተንኮልና ማጭበርበር ቀጠለ፡፡ ዋነኛው ተንኮል የከብት በሽታን ወደኢትዮጵያ ማስገባት ነበር፡፡ በዚህም ሰበብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶች አለቁ፡፡ ገበሬው ለእርሻ የሚጠቀምባቸው በሮችም አለቁ፡፡ በመሆኑም፣ ዋነኛው የእርሻ ግብዓት በበሽታው በመጠቃቱ፣ የገበሬው ምርታማነት እጅግ አሽቆለቆለ፡፡ ረሃብና ጠኔ በመላ ሀገሪቱ ተንሰራፋ፡፡ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ በኢትዮጵያ ምድር ተከሰተ፡፡ አዝማሪው እንዲህ ሲል አዜመ፤ “የበሬዎቹ ስም ጠፍብኝ ነበረ፤ አሁንስ ባስታውስ ከብት ዓለም ነበረ፡፡” አለ፡፡ እጅግ የታወቀው “ሞጣ ቀራኒዮ ምነው አይታረስ፤ በሬሳ ላይ መጣሁ፣ ከዚህ እስከዚያ ድረስ፡፡”ም የተባለው በዚያ ወቅት ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ያለቁትን ኢትዮጵያውያን በተመለከተ ፀሐፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “ይኼ ዘመን የእግዚአብሔር መዓት ከሰማይ የወረደበት” ዘመን ነው ብለውታል፡፡ ይህንን ዘመን ሕዝቡ፣ “የክፉ ቀን” እያለ ሲጠራው፣ ሰብዓዊ ቀውሱ የትየሌሌ ነበር፡፡ ገጣሚው እንዲህ ሲል ገልፆታል፤

                                                “ልጅ እናቷን ጠላች፣ አባትም ልጁን ጠላ፤

                                                “እህትም ወንድሟን ጠላች፣ ወንድምም እህቱን ጠላ፤

“ይኼንን ሁሉ ነገር ብናሰላስለው፤

“ፍቅሩንስ ያልፈጀው፣ ሆድና እንጀራ ነው፡፡”

ከዚህም ባለፈ የደረሰውን መዓት ሌላኛው ገጣሚ እንዲህ ሲል አንጎራጉሮታል፡፡ ገጣሚው ጣሊያን ሕዝቡን በቸነፈርና በሀባር አስጨርሶ ባዶውን መሬት ለመረከብ እያሤረ እንደነበረ ታውቆታል፡፡ እንዲህ ይላሉ ስንኞቹ፤ “ኧረ-ግፋ ግፋ፣ ወንዙን እንሻገር፤ ያለሰው ቢወዱት፣ ምን ይሆናል አገር፡፡”ም ተብሎ ነበር፡፡

በዚህ ወቅት ነበር የሞጃ ቤተሰብ ግንባር ቀደም መሪ የነበሩት ደጃ/ች ገርማሜ ለክፉ ቀን ብለው ያከማቹትን እህልና የዘር ሰብል ለሕዝቡ በነፃ የደሉት፡፡ በትውልድ አጥቢያቸው የነበሩትም አለቃ ገብረሃናም (ፍትሐ ነገሥቱ በሚያዘው መሠረት፣) ቤተ-ክርስቲያኗ ያከማቸችውን እህልና ገንዘብ አውጥተው ለምዕመናኑ ያደሉት በዚህ ወቅት ነበር፡፡ የደሰው ቀውስና በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ጠቅላላ አቋም ላይ የፈጠረው ጫና እጅግ መራራ ነበር፡፡ ነገር ግን በንጉሠ ነገሥቱ ቆራጥ አመራርና በነበሯቸው ቆፍጣና ባለሟሎች ብርቱ ትጋት 1886 እና 87ዓ.ም እንዳያልፉት የለምና አለፈ፡፡ ጣሊያንም በነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ እንደፍልፈል እየተሳበ ከመረብ ምላሽ ወደሰሜንና ደቡብ ትግራይ አቅጣጫ መስፋፋት ጀመረ፡፡ ይህንን ዘመን በአኮኖሚም ሆነ በወታደራዊ ጥንካሬያችን እጅግ የተፈተንበት ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህ ዘመን ጋር የሚስተካከሉ ታሪካዊ ወቅቶች ካሉም የአህመድ ግራኝ ዘመንና የ1928-1933ዓ.ም የነበረው የወረራ ዘመናት ናቸው፡፡

ያም ሆኖ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እልህ አስጨራሽ ትግልና የአደጋ መከላከል ሥራ ሲከናወን ቆየ፡፡ በመሆኑም፣ ያለማንም ወዳጅ አገር ርዳታና ምጽዋት የሞተው ሞቶ፣ ያለቀውም ከብትና እንሰሳት ሁሉ በየፈፋው ቀርተው በ1887ዓ.ም የበረከት ተስፋ ፈነጠቀ፡፡ በሚያዝያ 1887ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው ዶማና አካፋ ይዘው ለበልግ እርሻ ወጡ፡፡ ባለሟሎቻቸውና መሳፍንቱም የእረሳቸውን አርዓያነት ተከተሉ፡፡ በ1887ዓ.ም ገበሬው አረሰ፤ ነጋዴው ነገደ፤ ሸማኔውም ሸመነ፤ ቀጥቃጩም ብረቱን አዘበጠ፤ ወታደሩም ወኔው ተንተገተገ፡፡ የኢትዮጵያውያን የአትንኩኝ ባይነት መንፈስ እንደገና ታደሰ፡፡ “ክፉ ቀን” ኢትዮጵየውያንን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ አንድ አደረጋቸው፡፡ የጣሊያን መንግሥት ሊጠቀመው የሞከረውን ያረጀና ያፈጀ የሮማውያን ከፋፍለህ-ግዛ ስልት መልበስ ተጀመረ፡፡ ለዚህ ደግሞ የግንባር ቀደምነቱን ሚና የተጫወቱት የአፄ ዮሐንስ ልጅ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ናቸው፡፡ ቀጥ ብለው አዲስ አበባ አፄ ምኒልክ ዘንድ መጥተው በብሔራዊ ጥቅምና በሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ወዛና ፈዛዛ እንደማያሳዩ አረጋገጡ፡፡ (ቪቫ ራስ መንገሻ! ቪቫ-ቪቫ!)

3. ቪቫ ኢትዮጵያ! ቪቫ ምኒልክ!

ከጥቅምት 2 ቀን 1888 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነስቶ በ87ኛ ቀኑ መቀሌ የገባው የኢትዮጵያ ጦር ከፍተኛ የሆነ የሞራልና የሰብዕና አቅም ነበረው፡፡ በተለይም፣ “አፄ ምኒልክ የመንፈሥ ልዕልናና ቆራጥነት የሚያስከብራቸውና የኢትዮጵያን ሕዝብም የሚያኮራ ነበር፡፡” (መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፤ ገጽ 136)፡፡ አፄ ምኒልክ የጣሊያንን ጦር መቀሌ ላይ ድባቅ ከመቱት በኋላ፣ ለጋሊያኖና ለሚመራው ጦር 500 ግመሎችና በቅሎዎችን እንዲገዙ ፈቀዱላቸው፡፡ ለሻለቃ ጋሊያኖም “በማለፊያ መርገፍ ኮርቻ የተጫነች በቅሎ ሰጥተው ወደእናት ክፍለ-ጦሩ እንዲሄድ አደረጉት፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ከላይ በጠቀስነው መጽሐፍ በገጽ 135 ላይ እንዲህ ሲሉ ይጠይቃሉ፤ “በየት አገር ነው ጠላቱን ካሸነፈና ካንበረከከው በኋላ እንዲህ ያለ ንክብካቤ የሚደረግለት?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ እውነት አላቸው፡፡ ይህም እውነተኛ ጨዋነትና ፈሪሃ-እግዚአብሔር ነው የጣሊያናዊውን ቱራቲን ልብ ማርኮና ለአድናቆት አነሳስቶ “ቪቫ ምኒልክ!” ያሰኘው፡፡ (በነገራችን ላይ፣ በጣሊያንኛ “ቪቫ” ማለት “ረጅም እድሜ ይስጥህ!” እንደማለት ነው፡፡ ስለሆነም፣ “ቪቫ ምኒልክ” ሲባል፣ “ረጅም ዕድሜ-ለምኒልክ!” እንደማለት ነው፡፡)

ሌላም መታወስ ያለበት ነጥብ አለ፡፡ የአድዋን ድል ተከትሎ ስለመጣው የኢትዮጵያ ወሰን ጉዳይ ነው፡፡  በግንቦት 1889ዓ.ም ጣሊያኖቹ ከአፄ ምኒልክ ጋር ስለወሰን ጉዳይ እንዲነጋገር ኔራዚኒ የተባለውን መልዕከተኛ ላኩት፡፡ አፄ ምኒልክ ራሳቸው፣ በአንድ ካርታ ላይ የኢትዮጵያን ወሰን አስመልክተው መስመር አሰመሩና ማስመሩም ላይ ማኅተማቸውን አድርገውበት ሲያበቁ፣ “የኢትዮጵያ ወሰን ከዚህ እስከዚህ ድረስ ነው፤” ብለው ለኔራዚኒ ሰጡት፡፡ ከሁለት ወራት በኋላም የጣሊያን መንግሥት የአፄ ምኒልክን የወሰን ካርታ እንደተቀበለው አስታወቀ፡፡ ሆኖም፣ አፄ ምኒልክ አንድ ትልቅ ስኅተት ሠሩ፡፡ ለኔራዚኒ ካርታውን ሲሠጡት ለራሳቸው ቅጂ አላስቀሩም ነበር (መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፤ ገጽ 148)፡፡ ከዚህም ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የኢትዮጵያ ወሰን በሰሜን-ከኤርትራ፣ በምስራቅ ከሶማሊያ እና በምዕራብም ከሱዳን ጋር እንደላስቲክ እንዳንዴ ሲሳብ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲሰበሰብ አንድ መቶ አስራ አምስት አመታት ተቆጠሩ፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ በ1999 ዓ.ም ባሳተመውና፣ ፊ/ሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም “የሕይወቴ ታሪክ/ኦቶባዮግራፊ” ብለው በጻፉት መጽሐፋቸው በገጽ-73 ላይ እንደገለጹት፣ “ራስ መኮንንና አፄ ምኒልክ በዘመናቸው የሠሩት ሥራ የሚደነቅ ነው፡፡ ነገር ግን፤ ስህተታቸውን አውሮፓ ለትምህርት ከሔድኩ በኋላ እየገመትኩት መገረሜ አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ፣ የዚያን ጊዜ ዕውቀትና ኃይል በማነሱ ይቅርታ ሊደረግላቸው የተገባ ነው፡፡ እነሱ በደከሙበት ሥራ ብዙ ተጠቅመናል፡፡ በስህተታቸውም አደጋ ተቀብለንበታል፡፡ …የጣሊያን መንግሥት በዐዱዋ ጊዜ ዕውቀቱም ኃይሉም ትንሽ ነበር፡፡ …በእኛ ስህተት አገር-በጁ እንደሆነ ስለቀረ (ኤርትራን ማለታቸው ነው፤) ሃምሳ ዓመታት ያህል ቆይቶ ተሰናዳና አጠቃን፤….” ሲሉ እርር ድብን ይላሉ፡፡  ከፍ ብለውም፣ “ዐዱዋ ላይ ያን ያህል ሰዎች ተላለቁና፣ ጣሊያን የወሰደብንን አገር ሳናስለቅቅ ሄድን፡፡…የድሉን ዋጋ ዐዱዋ ከራስ መኮንን ጋር በዘመትኩ ጊዜ ለመገመቻ የሚሆን ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ ኋላ፣ በአውሮፓ መማር ከጀመርኩ በኋላ ግን እያስታወስኩት እንደ እሳት ያቃጥለኝ ጀመር፡፡” እያሉ  ስለዐዱዋ ድልና ጥሎት ስላለፈው ጠባሳ ይገልጻሉ፡፡

  1. ማጠቃለያ፤ 

የአዱዋን ድል ባከበርን ቁጥር የምናወሳቸው አብነቶች አሉን፡፡ መሪው ዳግማዊ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ ጀግናው ፊታውራሪ ገበየሁ አባጎራው፣ የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴና የደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶንስ ተጋድሎ ማን ይዘነጋቸዋል? የእነ፤- ራስ አባተ ቧ-ያለውንና ራስ መኮንንንስ የመሪነት ተሳትፎ ማን ይረሳዋል? የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሆኑትን፡- ራስ አሉላ አባ-ነጋን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስን፣ ራስ ስብሐቱንና የባሻ አውአሎምንስ ውለታ ከቶ ማን ይዘነጋዋል? ኢትዮጵያዊነትና ድል አድራጊነት በቀውጢ ቀንም ቱባ-ቱባ ጀግኖችን እንደሚያመርት አረጋግጦልናል፡፡ በተለይም የዳግማዊ አፄ ምኒልክን የመሪነት ችሎታ የተለየ የሚያደርጓቸው መገለጫዎችም በገሃድ ታይተዋል፡፡ በዳኝነትና በፍርድ ቅቡልነት ስላገኙ፣ ህዝቡ “አባ ዳኘው” በሚል የፈረስ ስማቸውም ቢጠራቸውም ቅሉ፤ እንደ አባትም እንደእናትም ሆነው ለህዝቡ በመታየታቸው፣ “እምዬ ምኒልክ” የሚል ቅጽል ስምም  ሰጥቷቸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የፃፍኩት ቢሆንም፣ በውስጥም ሆነ በውጪ የምኒልክን ያህል መስፈሬ-ግርማ የተጎናጸፈ መሪ የለም፡፡ የፈረንጅን ጦር በአዱዋ ጦር ሜዳ ላይ ድል መትቶ፣ ከፈረንጅ መንግሥት ጋር በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የዕርቅና የሰላም ውል የተዋዋለ አፍሪካዊ መሪ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ብቻ ናቸው፡፡ በፖለቲካና በዲፕሎማሲ ጥበብም ያስመዘገቡት ድል ከአዱዋው ድል ያልተናነሰ ነው፡፡ አራቱ የአውሮፓ ኃያላን (ጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና እንግሊዝ) ኢትዮጵያን ሊቀራመቷት አሰፍስፈው በነበረበት በዚያ ቀውጢ ወቅት፣ ከቅኝ-ግዛት ቅርምት የታደጋት የአዱዋው ድል ብቻ አይደለም፤ የንጉሡ የዲፕሎማሲና የፖለቲካም ጥበብ ነው፡፡ አንዱን በማባበል፤ ሌላውን በማስፈራራት፤ የአንዱን የጥቅም ዝንባሌ አጢኖ ከሌላው ግብዝ ጋር በማጋጨት እርስ-በርስ እንዲፋጠጡ በማድረግ የአራቱንም ኮሎኒያሊስቶች ፖሊሲ እንዳይስማማ አድርገውታል፡፡ (ዘንድሮም ደግመን፣ ቪቫ ኢትዮጵያ! ቪቫ ምኒልክ! ልንል እንወደለን፡፡…መልካም የአዱዋ የድል በዓል ይሁንልን፡፡)

አዲስጉዳይ መጽሔት፣ በቅጽ 8 ቁጥር 205፣ ቅዳሜ የካቲት 22፣ 2006 ዓ.ም ዕትም ላይ የወጣ ነው፡፡)

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 4 years ago on May 1, 2020
  • By:
  • Last Modified: May 3, 2020 @ 2:18 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar