www.maledatimes.com መንትያ ጥበባት፤ ግጥምና ሙዚቃ! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

መንትያ ጥበባት፤ ግጥምና ሙዚቃ!

By   /   May 1, 2020  /   Comments Off on መንትያ ጥበባት፤ ግጥምና ሙዚቃ!

    Print       Email
0 0
Read Time:7 Minute, 33 Second

https://www.youtube.com/channel/UCqAuXzJD_f5q7zV1ItVKAdA?view_as=subscriber የተለያዩ ታሪኮችን እና ዜናዎችን በዩቲዩብ መረጃ እንዲደርስዎ ከፈለጉ ከላይ ያለውን ሊንክ ይጫኑ እና ሰብስክራይብ ያድርጉ

ሰሎሞን ተሠማ ጂ.

“የአንድን አገር የሥልጣኔ ደረጃ ለማወቅ ብትሻ፤ ሙዚቃውን አድምጥ፣ ሥነ-ጽሑፉን አንብ!” ብሎ ነበር – ዲዜሬል፡፡ ፕ/ር አሸናፊ ከበደም፣ “የአንዲት አገር ሥልጣኔ አቋም በሳይንስ፣ በፖለቲካ፣ በኤኮኖሚ፣ በቴክኖለጂና በሚሊታሪ ኃይሉ ብቻ ሳይሆን በሙዚቃ፣ ሥነ-ጽሑፍና በሌሎችም የኪነ-ጥበባት ዘርፎች የተደላደለ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ሙዚቃና ሥነ-ጽሑፍ ረቂቅ አስተሳሰብና ዲሲፕሊንን ስለሚፈጥሩ ሥልጣኔው ተስፋፍቶ መገኘት አለበት፡፡ የቴክኖሎጂና የኤኮኖሚ እድገት ሊኖር የሚችለው የረቂቁ አስተሳሰብ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ሲኖሩ ነው” ይሉ ነበር (መነን መጽሔት፣ ሰኔ 1957 ዓ.ም፤ ገጽ 22)፡፡ በማስከተልም፣ “በአዕምሮና በልብ ምንነቱ ሳይታወቅ የሚታሰብ ነገር በሙዚቃ አካል ይኖረዋል በሥነ-ጽሑፍም ግዝፎ ይወጣል፡፡ ታላቅ የተባሉት ሁሉ ዘጠና-ዘጠኝ ከመቶ የሚሆኑት የጥበባዊ (ካላሲክ) ሙዚቃ ተጨዋች የሥነ-ጽሑፍም አፍቃሪዎች ነበሩ፤” ብለዋል (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ የካቲት 8 ቀን 1960 ዓ.ም፤ ገጽ 5)፡፡  አይንስታይንም ሆነ ዶክተር ኒኮላ ቴስላ በጥበባዊ ሙዚቃና ሥነ-ጽሑፍ አፍቃሪነታቸው የታወቁ ነበሩ፡፡

በሃገራችንም ቢሆን ጥልቁና ረቂቁ ፍልስፍና የገባውና የኖረው በዜማና በቅኔ አማካኝነት ነው፡፡ በሙዚቃ የተራቀቁት ሊቃውንት – በዜማ ቤት፣ በቅኔ ቤትና መጽሐፍት ቤት ውስጥ ሚስጢራትን አቀላጥፈው የሚያውቁ ምሁራን ስለነበሩ ምናባቸው ሰፊ፣ ሥነ-ሥርዓታቸውም ሥልጡንና የተገራ ነበር (ኃይለ ገብርኤል ዳኜ፤ 1970፣ ገጽ 89-90)፡፡ የዜማ ቤት በአራት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው ድጓ ቤት ነው፡፡ ዓመቱን ሙሉ በቅዳሴና በሰዐታት ጊዜ የሚዘመሩትን ዜማዎች ያጠናሉ፡፡ በመቀጠልም፣ ከቅዳሴ በኋላ በደባትሮች በህብር የሚዘመረውን “ዝማሬ” እና በቀብር ስነ-ሥርዓት እንዲሁም በዝክር ጊዜ የሚዘመረውን “መዋሲት” ያካትታል፡፡ በሦስተኛ ደረጃም መምህራንና የዜማ ሊቃውንት መሆን የሚፈልጉ “ቅዳሴና ሰዐታትን” የተመሰገነ አስተማሪ ዘንድ ሄደው ያጠናሉ፡፡

ድጓ ቤት፣ ዝማሬና መዋሲት፣ እንዲሁም ቅዳሴና ሰዐታት የዜማ ተማሪው በተናጠል የሚያዜማቸው ናቸው፡፡ አራተኛውና የመጨረሻው ደግሞ፣ “አቋቋም” ይባላል፡፡ አቋቋም፣ በዜማ ቤት ውስጥ የወረብ፣ ዝማሜና ማሕሌት መማሪያ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ስልት ያለው ውዝዋዜ (ዳንስ) ነው፡፡ ይህ ክፍል በህብረት ጽናጽልና መቋሚያ ተይዞ ንፋስ ከንበል-ቀና እንደሚያደርገው ሰንበሌጥ በስልት ይወዛወዛሉ (ኃይለ ገብርኤል ዳኜ፤ 1970፣ ገጽ 91)፡፡ የነዚህ የዜማ ቤት ሊቃውንት የቀለምና የሙዚቃ ዕውቀታቸውን በሃይማኖታዊውም ሆነ በዓለማዊው ምግባራቸው ሲገለጥ ኖሯል፡፡

ከዜማ ቤት ቀጠሎም በቅኔ ቤት ቆይታቸው ዘጠኝ ዓይነት አቀኛኘቶችን ያጠናሉ፤ ይለማመዳሉም፡፡ ከባለሁለት ስንኝ (ጉባኤ ቃና) ጀምረው ባለሦስት፣ አራት እስከ ዕጣነ-ሞገር ወይም መወድስ ድረስ (ባለሰባት ወይም ስምንት ስንኝ ያላቸው ሰምና ወርቅ ግጥሞችን) መግጠም ያጠናሉ፡፡ ይጽፋሉም፡፡ የቅኔን አዝመራ የቆረጠመ ምናቡና ምርምሩ የላቀ መሆኑ አይጠረጠርም፡፡ የቅኔ ቤትን ያጠናቀቀ ሙያተኛ አርዕስታዊ የሆነ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ እንደልቡ ሃሳቡን በቃላት አማካኝነት ትርጉም መስጠት አያቅተውም፡፡ እርግጡን ለመናገር፣ የምርምርን ክህሎት ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ችሎታንም ያዳብል፡፡ ቅኔን ያወቀና ያጠናቀቀ ኩረጃን (Hates an imitation of an imitation) ይጠየፋል::

በተመሳሳይ ሁኔታም፣ ለምዕራባውያንም ሙዚቃ ማለት ግጥም ነው፡፡ ግጥምና ሙዚቃ ትርጓሜያቸው አንድ ነው፡፡ በሌላ አነገገር፣ ሙዚቃ ሥነ-ጸሑፍ ነው፡፡ ዕውቀት ነው፡፡ ምናብ ነው፡፡ ፈጠራ ነው፡፡ ጥበባዊ ክህሎትን የሚጠይቅም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አዕምሮአዊ ነው፡፡ በመሆኑም ምዕራባዊያኑ ሊቃውንት፣ “አዕምሮአዊ አረዳዱ ዝቅተኛ የሆነ ሰው ሥነ-ጽሑፍም ስለማይገባው፣ ጥበባዊ (ክላሲክ) ሙዚቃም ምን እንደሆነ በግልፅ አይታየውም፤” ይላሉ፡፡ ስለሆነም፣ ምዕራባውያን ዜማንና ሥነ-ጽሑፍን ጎን ለጎን ለታዳጊዎቻቸው ያስተምራሉ፡፡ የታዳጊው አዕምሮ በዜማና በሥነ-ጽሑፍ ረገድ መንትያ ዕድገት እንዲኖረው ይደረጋል፡፡ በመጨረሻም፣ ታዳጊው ወደሚያዘነብልበት በኩል እንዲያተኩር ይደረጋል፡፡                                               

በኢትዮጵያ ባህላዊ አስተምህሮት ግን ነገሩ የተለየ ነው፡፡ አንድ ሰው የዜማ ቤትን ሲያጠናቅቅ ወደ ቅኔ ቤትና ወደ መጽሐፍት ቤት ያመራል፡፡ ዜማ ማለዘቢያ ነው፡፡ ዜማ የቅኔና የመጽሐፍት ቤቶች መንደርደሪያ ነው፡፡ አዕምሮን ለጥልቁና ረቂቁ የቅኔና የመጽሐፍት እንዲሁም የሊቃውንት ጥናት የሚያዘጋጀው ዜማ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ፣ ዜማና ሥነ-ጽሑፍ በኢትዮጵያም ሆነ በአውሮፓውያን አስተምህሮቶች ዘንድ የአንድ አላድ ሁለት ገፅታዎች ናቸው፡፡ ይህንን መረዳትና መገንዘብም የተገባ ነው፡፡

ከላይ እንዳወሳነው፣ መዚቃና ሥነ-ጽሑፍ በተለይም ሙዚቃና ግጥም መንትያ ናቸው፡፡ ግጥምና ሙዚቃ የሚከወኑት ለጆሮ ነው፡፡ ለዕዝነ-ልቦና ነው፡፡ ግጥም በአሰኛኘቱ በስድስት ቤቶች ይከፈላል፡፡ ማለትም፤ የቡሄ በሉ ቤት፣ የሠደፌ ቤት፣ የወል ቤት፣ የሰንጎ መገን ቤት፣ የወዳጄ ዘመዴ ቤትና የመዲና ቤት ናቸው (ተሾመ ይመር፣ የኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት፡፡ ሐምሌ 1997፡፡ ገጽ 89-123)፡፡ እንደግጥም ሁሉ፣ ሙዚቃም ብዙ ዓይነቶች አሉት፡፡ በድምፅ አሳክቶና አቀናብሮ የታቀደውን ሃሳብ በሰሚው መንፈስና ስሜት፣ እንዲሁም በሰሚው አእምሮ ላይ ትርጉም እንዲያገኝ ለማድረግ ዘዴውንና እውቀቱን ከችሎታ ጋር መጠየቁን ማወቅ የሙዚቃ ባለሙያው ግዴታ ነው፡፡ አድማጩም ቢሆን ለዚህ ዓይነቱ የሙዚቃ ዝግጅት የሠለጠነ መሆን ያስፈልገዋል፡፡

ከይዘት አንጻር ግጥም በሁለት ይከፈላል፡፡ ኃይማኖታዊና ዓለማዊ ይዘት ያላቸው ግጥሞች ይባላሉ፡፡ ለአንባቢውና ለአድማጩ ዕዝነ-ልቦና ባላቸው የመደመጥና የመነበብ ኃይላቸው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የዱሮውንም የአሁኑንና የመጪውን ትውልድ ዓይንና ጆሮ በመያዝና ባለመያዝ አቅማቸው በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነርሱም ጥበባዊ (Classical) ኃይል ያላቸው እና ጊዜያዊ (popular) ስሜትን ለማጫር ሲባል የሚገጠሙ ግጥሞች ናቸው፡፡ አከፋፈሉ ከአድማጩ አንፃር መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡

በተመሳሳይ ሁናቴም ከይዘት አንፃር፣ “ማንኛውም ሙዚቃ ሁለት ታላላቅ የዓይነት መክፈያዎች አሉት፡፡ እነርሱም 1ኛ/ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ሙዚቃዎችና 2ኛ/ ዓለማዊ ይዘት ያላቸው ሙዚቃዎች ተብለው ነው፡፡ እንደግጥም ሁሉ ሙዚቃዎችም በአድማጩ ዕዝነ-ልቦና ላይ ባላቸው የመደመጥ ኃይልና እንደወይን እያደር በቀማሹ ላይ በሚኖራቸው የማምጠቅ ቃና በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይከፈላሉ፡፡ 1ኛ/ ጥበባዊ (Classical music) ሙዚቃ የሚባሉት ሲሆኑ 2ኛ/ ደግሞ ጊዜያዊ (popular music) ሙዚቃ ተብለው ነው፡፡ ጥበባዊና ጊዜያዊ ሙዚቃዎች በአቀራረብ ስልታቸው መሰረት በሦስት ንዑስ ክፍሎችና ዓይነቶች ይከፈላሉ፡፡ 1ኛ/ ድምፃዊ ሙዚቃ 2ኛ/ መሳሪያዊ ሙዚቃ ሲሆኑ 3ኛ/ የድምጻዊና የመሳሪያዊ ሙዚቃዎች ውሁድነት የሚቀርቡና የሚቀርቡበት ስልት ነው” (ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፡፡ የካቲት 8 ቀን 1960 ዓ.ም፤ ገጽ 5)፡፡

ከላይ ያተትነውን አከፋፈል በምሳሌ እናብራራው፡፡ አንደኛ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ሙዚቃ በጠቅላላው ከይዘት አንፃር ሃይማኖታዊ ነው፡፡ በአድማጩ ዕዝነ-ልቦናም ላይ ባለው አቅም ጥበባዊ ክፍልም ውስጥ ይመደባል፡፡ በዚያ ላይ ድምፃዊም ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ ሁለተኛነትም የምናያቸው ሙዚቃዎች እነ“ምን ታደርጊዋለሽ” ወይም እነ“ሸግዬ – ሸግዬ” የተባሉትን  ዘፈኖች ነው፡፡ በጠቅላላው እነዚህን የመሳሰሉት የአዝማሪዎችም ሆነ የዘመናዊዎቹ ድምፃዊያን የሚዜሙትን ዘፈኖች ከይዘት አንፃር በዓለማዊ የሙዚቃ አይነትነት ስር እንመድባቸዋለን፡፡ በአድማጩ ዕዝነ-ልቦና ላይ ባላቸውም ኃይል ጊዜያዊ የሙዚቃ ስልትነት ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ድምፃዊና መሣሪያዊ የሙዚቃ ዓይነቶችም ናቸው፡፡ (ድምፃዊው በመሣሪያ ታጅቦ የሚያቀርባቸው ንዑስ ክፍሎች ናቸው፡፡)

3ኛ/ የፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ “እረኛው ባለዋሽንት”ና ወይም “ኒርቫናህ” የተባሉት ሙዚቃዎች፣ ወይም የሙላቱ አስታጥቄ “የልቤ ትዝታ” እና ሌሎቹም ቅንብሮቹ ደግሞ ጥበባዊ ናቸው፡፡ ዓለማዊም ናቸው፡፡ መሳሪያዊ ብቻ ናቸው፡፡ ….. “ጥበባዊ ሙዚቃ” ናቸው ስልም፤ “የታቀደውን የሙዚቃ አርእስትና ሃሳብ በድምፅ አሳክቶ፣ አዳብሮና አስፋፍቶ ለአድማጩ መንፈስ፣ አእምሮና ስሜት እንደታቀደው ለማስተላለፍ የሚችለውን ዓይነት ሙዚቃዎች ናቸው” ለማለት ነው፡፡ እነዚህ ሙዚቃዎች የደራሲውን የጥበባዊ ሙዚቃ ቅመራ ችሎታ ብቻ ሳይሆን የአድማጩንም የአእምሮ ጉልምስና ይጠይቃሉ፡፡ ጆሮና ዕዝነ-ልቦናው ያልተገራውን አድማጭ ጨርሶ ላይወዘውዙትም ይችላሉ፡፡

ጊዜያዊ (Popular Music) ሙዚቃ የሚባለው ዓይነት ብዙው ጊዜ የስሜት ብቻ ማስደሰቻ፣ የዳንኪራ መምቻ፣ የሽለላና የፉከራም ማሰሚያ ነው፡፡ ግጥሙም ሆነ ሙዚቃው ያልተያያዘና ያልተገጣጠመ፣ በመሳሪያና በድምፅ ጩኸትና ኳኳታ ብቻ የተሸፋፈነ ሲሆን ጠለቅ ብለው የማይመራመሩና ጊዜያዊ ጭፈራዎችን የሚሹትን አድማጮች ስሜት ቀስቃሽ ነው፡፡ በብዙ መልኩ ከንግድና ከትርፍ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ጊዜያዊ (Popular Music) ሙዚቃ ብዙውን ጊዜ የአድማጮችን “ጊዜያዊ ደስታ” ብቻ ዓላማው ስለሚያደርግ በጥበባዊ ዝግጅት በኩል በብዛት “ባዶ” መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ “ባዶ ጩኸት ብቻ ነው፡፡” ምክንያቱም 1ኛ/ ተጫዋቾቹ የመዚቃ ችሎታ ስለሌላቸውና ችሎታቸውንም ለማሻሻል ስለማይጥሩ፤ ሲሆን 2ኛ/ የሚበዛው የዓለም ሕዝብ የሚወደው ይሄንኑ ዓይነት ጩኸትና አደንቋሪ ስልት ስለሆነ ነው፡፡ ተለይም በትንሽ ድካም ብዙ ገንዘብ የሚተረፍበት የሙዚቃ ዓይነት ስለሆነ ነው ጥበባዊ ይዘቱ ኦና ነው፡፡ 3ኛ/ ሙዚቃውና ግጥሙም በትንሽ ድካምና ልምምድ (የውጭ አገሩን ዜማ በመመንዘርና በመኮረጅ የጊዜውን ትኩሳት ለመቀስቀሻነት የሚሆኑትን ቃላት በግጥም መልክ በማሳካት) ተዘጋጅቶ የሚቀርብበት ስልት ነው፡፡

4ኛ/ የተጫዋቾች የቀለምና የሙዚቃ ትምህርት ደረጃቸው በጣም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ በመሆኑ መጥፎውንና ጥሩውን ግጥምና ዜማም ስለማይዩት የለብ ለብ ስራ ይሰራሉ፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ባላቸው አቅምና ችሎታ ሕዝብን ለማስደሰት ከመጣጣር አላቋረጡም፡፡

የቀለም ትምህርቱንና የሙዚቃ ትምህርቱን ያጣመሩ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፡፡ የኢትዮጵያን ቅኔና ዜማ ስልት ጠንቅቀው ያጠኑና የሚያውቁ የባሕላዊና ዘመናዊ መሣሪያዎችን ለመጫወት የሚችሉ፣ የሙዚቃ ሰዋሰውንና አገባብን በቅጡ የሚያውቁ፣ ድምፅንና ሙዚቃን በአንድነት የሚያቀናብሩና የሚያቀርቡ የሙዚቃ ደራሲዎች ያስፈልጉናል፡፡ ጊዜያዊው ሙዚቃም በነርሱ ምሳሌነት ይሻሻላል፡፡ የምዕራብ አፍሪካን ወይም የሱዳን፣ የደቡብ አፍሪካን ወይም የመካከለኛው አፍሪካን ስልቶችና ዜማዎች በመኮረጅ የትም አንደርስም፡፡ የምዕራባዊያኑንም ሆነ የአረቦቹን ስልት ከኦሪጂናል ድምፃዊያኑ ልሳንና አልበሞች ልንሰማው እንችላለን፡፡ ወደ አማርኛ ወይም ኦሮምኛ ቋንቋ የሚተረጉምልን ቱርጁማን አያስፈልገንም፡፡ ምክንያቱም ሙዚቃ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ ነው፡፡ የቃላቱን ፍቺ ባናውቀው ግድ አይሰጠንም፤ ወይም ሙዚቃ ውስጥ የቃላቱ ረብ ሳየሆን የአርዕስቱ ጉልበት ነው ዕዝነ-ልቦናን የሚገዛው፡፡

አድማጩን አያውቅም ብሎ መናቅ ወይም ለመሸወድ መሞከር ይቅር፡፡ አድማጭ ከሌለ ማንኛውም ሙዚቃ ሊዳብርም ሆነ ሊሻሻል አይችልም፡፡ ጊዜያዊ ሙዚቃና ግጥሙ (ጥሩም ሆነ መጥፎ) አሁን ብዙ አድማጭና ፈላጊ እንዳለው እናውቃለን፡፡ ሆኖም፣ በኢትዮጵያ ጥበባዊ ሙዚቃ ከቤተ – ክህነት ውጪ ገና አልተጀመረም ለማለት ያስደፍራል፡፡ ቢኖሩም ከሦስትና አራት የማይበልጡ የተናጠል ጥረቶች ናቸው የሚስተዋሉት፡፡ በ1960ዎቹ ከቤተ-ክህነት ውጭ ጅምሮች ነበሩ፡፡ በብሔራዊ ቴያትር ነርሲስ ናልባንዲያን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ – የባሕል ማዕከል ውስጥ አቶ ተስፋዬ ለማ እና በተፈሪ መኮንን ት/ቤት እንዲሁም በናዝሬት የአፄ ገላውዲዮስ ትምህርት ቤት ሕብረ-ዝማሬዎች ብቅ-ብቅ ማለት ጀምረው ነበር፡፡ ግን ወዲያው ጠፉ፡፡ በደርጉ ዘመን፣ ኪነት ለጥበባዊነቷ ሳይሆን በጊዜያዊ የፕሮፖጋንዳ ተግባር ላይ ተጠምዳ ኖረች፡፡ አሁንም ቢሆን ያው ነው፡፡ ጊዜያዊ ነው! ጊዜያዊ ሆያ ሆዬ የተጠናወታት ነች! በአንድ ሙዚቃ ውስጥ የሰባት ስምንት ብሔረሰቦችን ችፋሮ ማየት ልማድ ሆኗል፡፡ ጥበባዊነት ቀርቶ ስልቱ የሰመረ መሆኑ እንኳን ግር ያሰኛል፡፡ በልዩነት ውስጥ አንድነትን እናሳያለን የሚሉት ቀማሪዎች የወቅቱ ፖለቲካ ደራሽ ጎርፍ ሆኖ እብስ አደረጋቸው፡፡ የከያኒ ነፍሳቸው በፖለቲካ አሸብሻቢነት ተዋጠች፡፡ ጥበባዊት ቆሌያቸውን የወቅቱ ሁናቴ አስደነበረባቸው፡፡ሙዚቃዊ ምቱ፣ ስልቱም ሆነ ጭፈራው ሚስቶ ሆነ፡፡…በቃ ይሄው ነው! ይሄንን ነው በየቴሌቪዥኑ መስኮት የምናየው፡፡ “አፍሪካ! አፍሪካ! አፍሪካ! አገራችን!” የምትለውን የነርሲስ ናልባንዲያንን ሕብረ-ዝማሬ የሚተካከል ሙዚቃ አቀናባሪ ጠፍቶ ሌት ከእንቅልፍ እንደሚቀሰቀስ አረሆ ጯሂ ተራ ስልት ያለ ድብልቅልቅ ነው የሚሰማው፡፡…..

የጥበባዊ ሙዚቃ አድማጮች ውሱን ናቸው፡፡ ጥበባዊ ሙዚቃ ሰሪዎቹም ውሱን ናቸው፡፡ በሸራተን አዲስና በጣይቱ ሆቴልም የተጀመሩ የግለሰብ ሙከራዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ግለሰቦች ጥረትም፣… ለወደፊቱ የጥበባዊ ሙዚቃ አፍሪቃዎችና አድማጮች ይፈጠራሉ፡፡ ቁጥራቸው ያነሱ ቢሆኑም ቅሉ ዛሬም አሉ፡፡ ወደፊት ደግሞ ይጨምራሉ፡፡ የዛሬዎቹ ግን ቢያንሱም በመሪነታቸው ብዙ ተከታዮችን ያገኛሉ፡፡ የሙላቱ አስታጥቄን ስኬት መመልከቱ ብቻ ይበቃል፡፡

ሙዚቃ በቃላት (ወይም በጽሑፍ) የሚገለጥና የሚከራከሩበት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሙዚቃ በድምፅ የሚደረስ ወይም የሚጫወቱት፣ በሰሚውና በተጫዋቹ መካከል የሚደረግ የመንፈስ ግንኙነትና መግባባትን የሚፈጠር አስቸጋሪ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ነው፡፡ ስለዚህም፣ ለሙዚቀኛ በቃላት ኃይል መጠቀምና መልዕክቱን ማስተላለፍ ቅር ያሰኘዋል፡፡ ትንሽም ሆነ ትልቅ በሙዚቃ ምሳሌነት ያለው ሙዚቃዊ በረከት፣ ፍሬያማ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ስለሙዚቃ ሰው ማወቅ የሚችለው በሙዚቃ ትምህርት ውስጥ ገብቶ ሲማር ነው፡፡ ያን ጊዜ፣ ብዙ ብዙ አሸናፊ ከበደዎች፣ ነርሲስ ናልባዲያኖች፣ ሙላቱ አስታጥቄዎችና ግርማ ይፍራሸዋዎች እናገኛለን፡፡ እነርሱም፣ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ጥበባዊ ያደርጉታል፡፡ ዳግማዊ የሆኑ ያሬዶችን በጉጉት እንጠባበቃለን፡፡ የዚያ ሰው ይበለን!

(ይህ መጣጥፍ በአዲስ ጉዳይ መፅሔት ሐምሌ 22 ቀን 2004 ዓ.ም ቁጥር 123 ዕትም ላይ ወጥቶ ነበር፡፡)

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 4 years ago on May 1, 2020
  • By:
  • Last Modified: May 1, 2020 @ 11:17 pm
  • Filed Under: Ethiopia

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar