www.maledatimes.com “““ገዳይ እና ሟች ከወሰንሰገድ ገ/ኪዳን (ጋዜጠኛ) - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“““ገዳይ እና ሟች ከወሰንሰገድ ገ/ኪዳን (ጋዜጠኛ)

By   /   January 26, 2013  /   Comments Off on “““ገዳይ እና ሟች ከወሰንሰገድ ገ/ኪዳን (ጋዜጠኛ)

    Print       Email
0 0
Read Time:26 Minute, 14 Second

wosenseged1
ይህንን ፅሁፍ ለማዘጋጀት ያሰብኩት ከሳምንት በፊት ነበር፡፡ “ለነገ ይደር” ብዬ አዘገሁት፡፡ እንዲያም ሆኖ ሀሳቡ ሽው ባለኝ ጊዜ፣ ሰአንድ ወጥ በመቆጨት ስሜት “ገዳይ እና ሟች” በሚል ርዕስ የከተብኩት ግጥም ነበር ቀድሞ ወደ ህሊናዬ የመጣው፡፡ግጥሙ ዘለግ ያለ ቢሆንም፣ የብዙዎችን ስሜት የነካ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በመድረክ ላይ ሳነበው የተቀረፅኩትም
ባህርማዶ ተሻግሮ ተደምጧል መሰለኝ፡-እንደተነገረኝ፡፡ ለዚህ ዘለግ ያለግጥም ብርታትና ጉልበት የሆነው ከአንድ ሃሳብ ወደ ሌላ ሃሳብ መሸጋገሪያ ወይም ማቀንቀኛው ነው፡፡
“…ወንድም ወንድሙን ገደለው
እየለመነው ገደለው
እየገደለው ለመነው…” ይላል፡- የግጥሙ ማቀንቀኛ፡፡
የማቀንቀኛው ገዳይ ለሟች፣ ሟችም ለገዳይ የወንድማማችነት ቦታ እንዳላቸው የሚያሳይ መሰለኝ፡፡ ይህንን ዕውነት እያውጠነጠንኩ ሳለ፣ ሁለት ሀገርኛ ተረቶች ታወሱኝ፡፡ የመጀመሪያው አንድ የአይነሥውርን ይወክላል፡፡ ሁለተኛው “የአይጦች ወግ” ሊባል የሚችል ነው፡፡ ሁለቱም ተረቶች ዝቅ ብዬ ለማነሳው ፈትለነገር (team)ማዋዣ ይሆኑኝ ዘንድ ወደ ኋላ ላይ
ልጠቀምባቸው ወደድኩ፡፡ ለማንኛውም ወደ ዋናው ጉዳይ ልዝለቅ፡-
• 1 –
ጉዳዩ የተከሰተው ወደ ባህር ማዶ ነው፡- ሀገረ አሜሪካ፡፡ ጥር 1 ቀን 2005 ዓ.ም ነው ዜናው የተሰራጨው፡፡ “የFBI መርማሪዎች አበበ ገላውን ለመግደል የታቀደውን ሴራ አከሸፉ፤….በሴራው ከተሳተፉት አንዱ ጉዕሽ አበራ ነው፡፡…” የሚል ነው፡፡ ዜናው ከተሰማበት ደቂቃ ጀምሮ የኢትዮጵያውን ዲያስፖራ ድረ-ገፆች እና ሌሎች የመገናኛ አውታሮች ዋነኛ ጉዳይ
ይኸው ዜና ሆነ፡፡ እስካሁንም ድረስ የሚወቀጠው፣ የሚሰለቀው፣ የሚደቆሰው፣ የአጀንዳዎች ሁሉ አጀንዳ ለመሆን የበቃው፤ አብዛኞቹን የሃገሬን ዲያስፖራ ድረ-ገፆች ሌሎች መገናኛ አውታሮችን እንዳስጨነቀ ያለው ይኸው ጉዳይ ሆኗል፡፡
በእርግጥም ጉዳዩ አነጋጋሪነት አለው፡፡ ዜናው ከዜናነት ባሻገር ይታይ ሊመረመር፣ ዕውነታው ጠርቶ ሊወጣ ይገባል፡፡ FBIን ያህል የዓለማችን ፊታአውራሪ የፖሊስ ተቋም አነፍንፎ የደረሰበት ይህ “የግድያ ሴራ” እንዲህ በዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡
የረቀቀ መሆን አለበት፡፡ ማን አረቀቀው? ለምን? በምን የተነሳ? የሚሉ ስስ ጥያቄዎች መልስ ያገኙ ዘንድ ግድ ነበር፡፡ እኔም የምጠብቀው ይህንን ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ዜናው ከተሰማበት ድረስ እስካሁን (አንድ ወር ሙሉ) አብዛኞቹ የሃገሬ ዲያስፖራዎች እና ድረ-ገፆች እና ሌሎች መገናኛ አውታሮቻቸው ጉዳዩን በዋነኛ አጀንዳነት የያዙት በተቃራኒው መልኩ መሆኑ ነው ብእሬን እንዳነሳ ያስገደደኝ፡፡
ዕውነታ ለይቶ ጥርት አድርጎ ከማውጣት ይልቅ ማደፍረስ፣ ማደፈራረስን የተያያዙ ነው የሆኑብኝ፡፡
አብዛኞቹ የሃገሬ ዲያስፖራዎች እና ድረ-ገፆች እና ሌሎች መገናኛ አውታሮቻቸው ዜናው ከተናፈሰበት ዕለት ማግስት አንስቶ፣የሚዘግቧቸው ዘገባዎች፣ የአንባቢ የሚያቀርቧቸው መጣጥፎች፣ የሚያስተናግዷቸው የግለሰብ አስተያየቶች ልክም ለከትም የሌላቸው ዓይነት ነበሩ፡፡ ናቸውም፡፡ ፍፁም ሥነምግባር የሚባል ነገር ያልዳበሳቸው መረን የወጡ የሚያስጠይፉ ስድቦች
የታጨቁባቸው ፍረጃዎች፣ “የዜናውን ዕውነትነት ካልተቀበልክ አንተም ነፍሰ ገዳይ ነህ” የሚሉ ዘለፋዎችና ተራ-አተካራዎች…ናቸው በየመገናኛ አውታሮቻቸው ላይ ሲናኙ የከረሙት፡፡ አሁንም የሚናኙት፡፡ የፌስቡክ ገፆቻችንንም ያጨናነቀው እንዲህ ያለው መረን የወጣ አተካራ ነው፡፡ ዝም ብሎ መጮህ መጯጯህ አይነት ነገር፡፡ “ሴራ” የተባለው ዜና ከተሰማ በሳምንቱ ይሁን በቀጣዩ ሳምንት ያሬድ አይቼህ የተባሉ “ዲያስፖራዊ” (ላይሆኑም ይችላሉ) ዘ- ሐበሻ የተባለ ድረገፅ ላይ “ኧረ እንረጋጋ!” የሚል ፅሁፍ አንብቤ ነበር፡፡ ፀሐፊው በዚህች መጣጥፋቸው ተጠርጣሪው ጉዕሽ አበራ በፓልቶክ ሲቪሊቲ የሰጠውን ያለምልልስ መስማታቸውን ጠቅሰው፡- “ጉዕሽ አበራ ከተናገረው የተረዳሁት፤ በፌስ ቡክ ሰጣ ገባ አንጀቱን ያሳርሩታል፤ እሱም የሚለውን ይላል፤ በቃ፤ እኛ ምን ይሁን ብለን ነው ነገሩን የምናጦዘው?” የሚል ሃሳብ ነበር በደምሳሳው የሰነዘሩት፡፡ ከዚህ በኋላ የወረደባቸው የስድብ ናዳ የሚነገር አይደለም፡፡ የሚቀፍ፣ የሚያሳቅቅ፣ ግብረገብነት የጎደለው የሥድብ ናዳ ወረደባቸው፡፡ እንደው ለአብነት ያህል ይህንን ጠቀስኩ እንጂ በየድረገፁና በሌሎች መገናኛ አውታሮች
ያነበብኳቸውና የሰማኋቸው የሥነምግባር ቅንጣት የጎደላቸው መረን የወጡ “ሃሳቦች” በርካታ ናቸው፡፡ ከብዛታቸው የፀያፍነታቸው ነገር በ10 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምገኘውን እኔን ባላገሩን ኢትዮጵያዊ የሚያሳቅቁ ናቸው ብል አላገነንኩም፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የግድያ ሙከራ ታቅዶበታል በሚባለው በጋዜጠኛ አበበ ገላው ስም በፌስ የተለቀቀ (መቼም የፌስ ቡክ ስም አይታመንም) የ3 ደቂቃ የመሰዳደብ ዲስኩር ሰምቻለሁ፡፡ ኧረ እንደውም ለመረጃነት ከፌስቡክ ገጼ ላይ አስቀርቸዋለሁ፡፡ እንደሚመስለኝ የአበበ ገላው ቤተሰብ የሆነች አንዲት ሴት ላይ የሥልክ ማስፈራሪያ እየተሰነዘረባት ነው፡፡ ደቂቃ ሙሉ “የሚዝተውም”፤ “የሚዛትባትም” በስድብ እኩል ይሞላለጫሉ፡፡ ዛቻ ሰንዛሪውም “እናትሽን!” ይላል፡፡ ዛቻ እየተሰነበራትም “እናትክን” ትላለች፡፡ ጨዋ ለመሆን እንጂ ሁለቱም ያልሰደቡት ዘመድ አዝማድ የላቸውም፡፡
ይኼ የፌስቡክ ማስረጃ ዛቻ አልመስልህ ነው ያለኝ፡፡ ሁለቱም ወገኖች የስድብ ውድድር የያዙ ነው የመሰለኝ፡፡ ለሰማሁበት ጆሮዬ ነው ያዘንኩለት፡፡ በጣም ነው ያፈርኩት፤ ያዘንኩትም፡፡ እነዚህ የሚሳደደሱት እህትና ወንድሞቼ እውነት ኢትዮጵያዊ ናቸው? እስክል ድረስ፡፡ ቀድሞ ነገር እኔን ያስገረመኝና ያሳፈረኝ ይህን የስድብ ውርጅብኝ ስሙልኝ የሚባል መሆኑ ነው፡፡
እንኳን ስሙልኝ ሊባል ሊታሰብም የሚገባ አልሆንህ ብሎኝ መፍረድ ቸገረኝ፡፡

የሆነ ሆኖ በዚህ መልኩ ዕለት ዕለት እየታደሰ ዋነኛው የዲያስፖራ አጀንዳ ሆኖ ለወር ያህል የቀጠለው የአበበ ገላው እና የግዑሽ አበራ ጉዳይ የዓይነስውሩን ተረት ነው ያስታወሰኝ፡፡
ሰውየው በተፈጥሮ ዓይነስውር ነው አሉ ፡፡ ከበርካታ ዓይናማ ጓደኞቹ ጋር በፍቅር የሚኖር፡፡ አንድ ቀን ግን፣ ከአንዱ ዓይናማ ጓደኛው ጋር ተጠላ፡፡ እንደዘበት የተከሰተው አለመግባባት፣ ምርር ክርር ወዳለ ፀብ ተሸጋገረ፡፡ ዓይነ ስውሩ ራሱን መቆጣጠር ተሳነው፡፡ ዓይናማውን በጡንቻው መደቆስ አሰኘው፡፡ ዓይናማው ግን ሸሸ፡፡ የኋላ ኋላ የሚከሰተውን በማሰብ
ከነገሩ ለመራቅ ሮጠ፡፡ አመለጠ፡፡ ይኼኔ ዓይነስውሩ ወደመሬት ጎንበስ አለና በእጁ እየዳበሰ ድንጋይ ፈለገ፡፡ እጁ የገባለትን ድንጋይ፣ ፀበኛው የሮጠበትን አቅጣጫ ሳይለይ ወረወረ፡፡ ወዲያው ራቅ ካለ ቦታ ጩኸት ሰማ፡፡ የ“እሪታ” ድምፅ ሲሰማ፣ ዒላማውን መምታቱን ቢያምንም ጆሮውን ተጠራጠረ፡፡ እናም በአቅራቢያው ያለውን ሰው እንዲህ ሲል ጠየቀ፡-
“መታሁት?”
“አልመታኸውም” አለው በአቅራቢያው ያለው ሰው፡፡
“ታዲያ የምን ጩኸት ነው የምሰማው?”
“ወርውረህ የመታኸው ፀበኛህን ሳይሆን፣ ምንም የማያውቀውን ሠላማዊውን ሰው ነው” ከዚህ በኋላ ያለው የዓይነስውሩ ምላሽ ነው የሚያስገርመው፡፡ ለዚህ ፅሁፌም መልዕክታዊ አንደምታውን የሚያጎላልኝ የዓይነስውሩ ተከታዩ ምላሽ ነው፡፡ እነሆ፡-
“የወረወርኩት ድንጋይ ማንንም ይምታ ማንን፣ ዋናው ቁምነገሩ አለመሳቴ ነው!!”
ልክ እንደዚያው ሁሉ፣ በ“ግድያ ሙከራው” ላይ የሚሰነዘሩ የአብዛኛው ዲያስፖራዎች (የሁሉም) አስተያየት መረጋጋት የሌለባቸው፣ ስክነት የጎደላቸው፣ በነሲብ የሚወረወሩ፣ ግብረ ገብነት የጎደላቸው፣ በፀያፍ ቃላት የታጀሉ፣ ዓላማቸውንም ዒላማቸውንም የሳቱ፣ በነሲብ የሚወነጨፉ ወዘተ ናቸው፡፡ ኧረ ያገር ያለህ የሚያሰኙ ናቸው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ እኔን ብዕር ያስመዘዘኝ የጉዳዩ መነሻ አይደለም፡፡ ማንኛውም የዲያስፖራ ድረ-ገፅ፣ ማንኛውም የዲያስፖራ የመገኛኛ አውታር ጉዳዩን ጉዳዬ ሊለው አይገባም የሚል ሙግትም አልገጥምም፡፡ ዜናውን መዘገብ፣ ዕውነታውን መመርመር ለይቶ ማውጣት የመገናኛ ብዙሃናት አይነተኛ አይነተኛ ተግባር መሆኑንም ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን የያዙበት
መንገድ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ የአንዱን ወገን ትክክለኝነት ብቻ ማጉላት፣ የሌላውን ወገን ሃሳብ ማጣጣል ለማንም ለምንም የሚበጅ አይመስለኝም፡፡
የግድያ “ሴራ አሴረ” የተባለው ሰው ጥፋት ለማድረግና የሃገሪቷ ጠላት መሆኑን ለማጉላት የFBIን ሥም ማጣቀስ ብቻ ተዓማኒ አያሰኝም፡፡ እንኳንስ FBI የአ/በባ ፖሊስ ጥቆማ ከደረሰው፣ የደረሰውን ጥቆማ ማጣራቱ ግድ ነው፡፡ እንዲ FBI  ነቢይ አይደለም፡፡ FBI ተጠርጣሪውን ጠይቆታል፡፡ ጉዳዩ የከፋ ነገር ባለመሆኑ አላሰረውም፡፡ የኋላ ኋላ ቪኦኤ ግዑሽ አበራን
ሲያነጋግረው የተረዳሁት FBI በጥቆማ የጠየቀው መሆኑን ነው፡፡ ይኼ FBI የመግደል ሙከራውን ደረሰበት የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ ነው ጉዳዩ ሳይሆን፣ የጉዳዩ አያያዝ (አጯጯህ፣ግነት፣ አጧጧዝ) አግባብ አልመሰለኝም የምለው፡፡
በሌላ በኩል አበበ ገላው የግድያ ሙከራ ሊቃጣበት እንደማይገባም አምናለሁ፡፡ እንኳን ሊቃጣበት ሊታሰብበት አይገባም ባይ ነኝ፡፡ አበበ ገላው፣ በካምፕ ዴቪድ ሜሪላንድ አለምአቀፍ ስብሰባ ላይ ተጋባዥ የነበሩትን ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊን “የነፃነት ያለህ” ብሎ የጠየቀ ደፋር ኢትዮጵያዊ ነው፡- ነፍሳቸውን ይማርና፡፡ አበበ ነፃነትን የመጠየቅ ፍፁማዊና ተፈጥሮአዊ መብት
አለው፡፡ ነፃነትን በመጠየቁ፣ ስለነፃነት በመሟገቱ ብቻ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ መብት ግን ሊኖረው አይገባም፡፡ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ መብት ሊኖረው አይችልም፡፡ “አበበ ገላው ጀግና ነው” ማለት ይቻላል፡፡ እኔም አላለሁ፡፡ ሌላውም ሌላ ጀግና ሊኖረው ይችላል፡፡ ሁሉም እንደየአመለካከቱ፣ እንደየእምነቱ የመኖር መብት የማሰብ መብት አለው ማለት ነው፡፡ የእኔን
የእኔ ያላለ ጠላት ነው የሚል አስተሳሰብ የትም አያደርስም፡፡ ለራስም ለሃገርም አይጠቅምም፡፡ ሊጠቅምም አይችልም፡፡
እንደእኔ እንደኔ አበበ ገላውም ሆነ ጉዕሽ አበራ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ የጆሮ ጌጥ እና የአንገት ኃብል ናቸው እንደማለት፡፡ ሁለቱም ለሃገራቸው የማሰብ እኩል መብት አላቸው፡፡ እኩል የማለም መብት አላቸው፡፡ በአስተሳሰባቸው ወይም በአመለካከታቸው ልዩነት የተነሳ አንዱን ፍፁም ኢትዮጵያዊ አንዱን የኢትዮጵያ ጠላት ማድረግ የሚቻል
አይመስለኝም፡፡
ለማለት የፈለግኩት የአበበ እና የጉዕሽ ጉዳይ ብቻውን ተነጥሎ ይህንን ያህል የሚጎላበት ምክንያት የለም ነው፡፡ ሰዎቹ ልዩ አጀንዳ ሆነው፣ ሌላው አጀንዳ ሁሉ የሚያስጥሉበት ምክንያት የለም ነው፡፡ በአጭሩ ሀገር አይደሉም ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የእነሱን ጉዳይ ስናባትል የጋራ ሃገራችን ጉዳይ ቀስ በቀስ ጥላን ባዶ እጃችንን የሚያስቀረን ሊሆን አይገባም ነው፡፡ ከእነሱ
በላይ፣ ከማንኛችንም በላይ ኢትዮጵያ የምንላት ሃገር አለች፡፡ አቶ መለስ ከዚህ ዓለም በሞት አልፈዋል፡፡ ብዙ ታሪክ የሰሩ ሰዎችም ሞተዋል፡፡ አበበ ገላውም ያልፋል፡፡ እኔም አልፋለሁ፡፡ ሌላውም ሰው እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያ ግን ለዘላለም ትኖራለች፡፡ ይህንን ስል የአይጧ ተረት ታወሰኝ፡፡

ከወደ ሰሜን ሸዋ ነው ተረቱን የሰማሁት፡፡ አንዲት በጠና የታመመች አይጥ ልጆቿን ሰብስባ እንዲ አለቻቸው – አሉ፡- “እንግዲ መሞቻዬ ተቃርቧል፤ ስሞት የምትቀብሩኝ ታዲያ ደብረሊባኖስ ነው…”ልጆቿ “…ይኼ ጉዳይ ከባድ ስለሆነ እንወያይበትና መልሱን እንነግርሻለን..” አሏት፡፡ ከአጠገቧ ዞር ብለው መከሩና ምላሽ ይዘው መጡ፡፡ “…እናታችን ነሽ፡፡ ትዕዛዝሽን ሰምተናል፡፡ ትዕዛዝሽን ልንፈፅምም ይገባን ነበር፡፡ ግን ትዕዛዝሽን መፈፀም ይቸግነረናል፡፡…”
“ችግሩ ምንድነው?” ስትል እያቃሰተች ጠየቀች እናት፡፡
“…አንቺን ለመቅበር በሰማይ እንዳንሄድ አሞራ ይበላናል፤ በምድር ሬሳሽን ይዘን እንዳንጓዝ ድመት ያስቸግረናል፡፡” ሲሉ መልስ ሰጧት ልጆቿ፡፡ የተናገሩትን በፅሞና ከሰማች በኋላ የመጨረሻ ቃሏን ሰነዘረች፡፡
“አይ!…እኔም የጠየኳችሁ ይፈፀማል ብዬ አይደለም፤ ሳትናገር ሞተች እንዳልባል ብዬ ነው፡፡” አለች አሉ፡፡እኔም ነገሩ አላግባብ ሲከር ሲካረር፣ ፅንፍ ለፅንፍ ሲያነታርክ፣ ሲያጠዛጥዝ፣ ሲያናችፍ፣ ዲያስፖራ ወገኖቼን እርስ በእርስ ሲያባላ፣ ሲያብላላ ዝም ከማለት ብዬ ነው ሃሳቤን የምሰነዝረነው፡፡ እከሌን ጠላት ነው ብለን ስንፈርጅ፣ እሱም እኛን በጠላትነት ሲፈርጅ፤ እከሌን የጠላት ቅጥረኛ ነው ብለን ጥርስ ስንነክስበት፣ እሱም ጥርሱን ሲነክስብን….እርስ በርስ ተጠላልፈን፣ እርስበርስ ተሻኩተን እርስ በርስ ተጣጥለን፣ እርስበርስ ተናክሰን…መቀበሪያችንን፣ ሃገራችንን፣ ኢትዮጵያችንን እንዳናጣት ነው ስጋቴ፡፡ አበው “ከአነጋገር ይፈረዳል ከአያያዝ ይቀደዳል” እንዲሉ፤ ዲያስፖራ ወገኖቼ ሆይ አያያዛችሁ
አላማረኝም ለማለት ነው ይህንን ሁሉ የምዘበዝበው፡፡ አበቃሁ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on January 26, 2013
  • By:
  • Last Modified: January 26, 2013 @ 10:05 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar