www.maledatimes.com “መንግሥት የለም ወይ?!”- የማንና ምን አይነት መንግሥት?by Mesfin Negash - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

“መንግሥት የለም ወይ?!”- የማንና ምን አይነት መንግሥት?by Mesfin Negash

By   /   March 20, 2013  /   Comments Off on “መንግሥት የለም ወይ?!”- የማንና ምን አይነት መንግሥት?by Mesfin Negash

    Print       Email
0 0
Read Time:12 Minute, 31 Second

ይህ ጥያቄ አከል አቤቱታ ቢያንስ ከተሜውን ጨምሮ በአማርኛ ተናጋሪው ኅብረተሰብ ዘንድ ፍትሕን ፍለጋ ከሚጠቀሱ የተለመዱ አነጋገሮች አንዱ ነው። “ሕግ የለም ወይ?!” የሚል በመሠረቱ ተመሳሳይ ጭብጥ ያለው የአቤቱታና የፍትሕ ጥያቄም አለ። (በሌሎች የአገራችን ቋንቋዎች ተመሳሳይ አነጋገሮች ይኖሩ እንደሆነ እገምታለሁ።) ለምሳሌ በመካሔድ ላይ በሚገኘው የሙስሊም ወገኖቻችን የመብት ጥያቄ ጎልተው ከወጡት፣ ደጋግመው በዝማሬ መልክ በዜማ ከሚሰሙት ድምጾች አንዱ ይኼው ነው፤ “መንግሥት የለም ወይ?! መንግሥት የለም ወይ?! መንግሥት የለም ወይ?!”

 

ይህን ጥሪና ጩኸት ሰምቶ “መንግሥትማ ኖሮ አሁን የምትቃወሙትን ነገር አደረጋባችሁ፤ መልሳችሁ እርሱኑ ትጣራላችሁን?” ብሎ የሚጠይቅ አይጠፋ ይሆናል። የጥሪው፣ የጩኸቱ፣ የጥያቄው ትርጉም ባይገባው ነው። የመንግሥት ሐላፊዎችም የገባቸው አይመስሉም።

 

አንድ ሰው “መንግሥት የለም ወይ?!” ብሎ ብሶቱን ቢገልጽ የአነጋገሩ ትርጉም ምን እንደሆነ ግልጽ ነው። በአጭሩ “ይህ ሁሉ ነገር ሲሆን፣ ይህን የመሰለ ግፍ ሲፈጸምብኝ፣ እንዲህ ፍትሕን ስነፈግና ስጠቃ…የሚመለከት፣ የሚከላከልልኝ፣ የሚቆምልኝ፣ የሚያድነኝ መንግሥት የለም ወይ” በማለት የመንግሥትን መኖር፣ ካለም ደርሶ ያስጥለው እንደሆነ መጠየቅ ነው። ወይም “እንዲህ ስጠቃ ሊከላከልልኝ ይገባው የነበረው መንግሥት የት ሔደ?” በማለት መንግሥትን “ሐላፊነትህን አልተወጣህም” እንደማለትም ሊሆን ይችላል። በሌላ አነጋገር “እኔን የመጠበቅ ሐላፊነት የነበረበት መንግሥት ምን እየሠራ ነው” ብሎ መንግሥትን “ድረስልኝ” ብሎ እንደመጣራት ነው። ምናልባትም ደግሞ ለግፍ ፈጻሚው የቀረበ ማሳሳቢያ ሊሆን ይችላል፤ በሕግ የሚጠይቀው፣ ለተጠቂዎች የሚቆም መንግሥት መኖሩን እንዲያስታውስ የሚገፋፋ የማንቂያ ደውል ይመስል። ግፍ ፈጻሚው “መንግሥት መጥቶ ይ(ያስ)ቀጣኛል፣ ለሕግ ያቀርበኛል” ብሎ ከተግባሩ ይቆጠብ እንደሆነ።

 

“መንግሥት የለም ወይ?!” የሚለው ጩኸት ሦስት ወገኖችን አንድ ላይ የሚያመጣ ነው፤ ተበዳይ (ነኝ ባይ)፣ በዳይ (ነህ ተባይ) እና ዳኛ የሆነው (ይሆናል ተብሎ የሚገመተው) መንግሥት። ይህ አነጋገር (መንግሥት የለም ወይ?!) ሦስቱም ወገኖች አንዱ ስለሌላው ያላቸውን አመለካከት፣ አንዱ ለሌላው ያለበትን ሐላፊነት ጭምር ታሳቢ ያደረጉ መነሻዎች አሉት። አንባቢዎቼ የቀረውን እንደሚሞሉት በማመን እኔ የተበዳይን እሳቤ (አሰምሽን) እና እምነት ብቻ ላብራራ።

“መንግሥት የለም ወይ?!” ብሎ የሚጮህ ተበዳይ (1) መንግሥት ዜጎቹን ከጉልበተኞች ጥቃት የመጠበቅና ፍትሕን የማስፈን ፍላጎት እና/ወይም ሐላፊነት እንዳለበት፣ (2) መንግሥት ዜጎቹን ከግፍ የሚጠብቅበትና ፍትህን የሚያሰፍንበት አቅም እንዳለው ያምናል። ሰውየው “መንግሥት የለም ወይ?!” ወይም “የመንግሥት ያለህ!” ብሎ ሲጮህ መንግሥት ቢቻል እርሱን እንዲደግፍ፣ ይህም ባይሆን በፍትሕ እንዲዳኘው፣ ከግፍ እንዲታደገው በማመን ነው። (3) ይህ “የድረስልኝ” ጥሪ መንግሥት ራሱ በዳይ ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ አያደርግም ብሎ መከራከር ይቻል ይሆናል። ይህ ግምት ትክክል ሆነም አልሆነም ግን “የድረስልኝ” ጥሪውን ክብደትም ሆነ ተገቢነት አይቀይረውም።

 

እንደኢትዮጵያ መንግሥት ራሱ በዳይ ሆኖ በሚገኝበት አጋጣሚ ጥሪው መሠረታዊ ይዘቱን ሳይለውጥ የጥያቄውን ቅርጽ ይለውጥ ይሆናል። ዜጎቹን ከግፍ የመካለከል፣ ፍትሕ-ርትእን የማስፈን ሐላፊነት ያለበት መንግሥት እርሱ ራሱ ግፍ ፈጻሚ ሆኖ ሲገኝ “መንግሥት የለም ወይ?!” የሚለው ጥያቄ “የምፈልገው አይነት መንግሥት የለኝም” ብሎ እንደማወጅ ነው። ምክንያቱም ሰውየው ጩኸቱን ሲያሰማ በሕሊናው የሚያስበው ዜጎቹን የመጠበቅ ሐላፊነትና ፍላጎት ስላለበት፣ የዜጎቹን መብት ስለሚያከብርና ስለሚያስከብር፣ የዜጎቹን ድምጽ ስለሚሰማ፣ በዜጎቹ ስለሚታመንና ስለሚከበር መንግሥት ነው። ጥሪው፣ ጨኸቱ ዜጎቹን በግፍና በአምባገነንነት ለሚገዛው መንግሥት የቀረበ አይደለም።

 

ኢትዮጵያን የሚገዛት ሐፍረቱን እንኳን መሸፈን የማይችል አምባገነን መንግሥትና መሪዎቹ “መንግሥት የለም ወይ?!” የሚለውን ጩኸት ሲሰሙ ምን ይሰማቸው ይሆን? በየደረጃው የሚገኙት የመንግሥት ሐላፊዎች በየአደባባዩ፣ በየመስጊዱ፣ በየአብያተ ክርስቲያኑ፣ በየጋዜጣው፣ በየስብሰባው፣ በየሰልፉ፣ በየቀበሌው፣ በየፍርድ ቤቱ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የሚሰማውን “መንግሥት የለም ወይ?!” የሚል የብሶት ጥሪ የሚተረጉሙት ምን እያሉ ይሆን? እፍረትም እውቀትም የሌላቸው “መንግሥት አለ፣ እርሱም እኔ/እኛ ነን” ብለው በልባቸው ስለመንግሥትነታቸው ፍትሐዊነት ይመጻደቁ ይሆናል። የለየላቸው ወሮበሎቹ ደግሞ “መንግሥት እኛው ነን፤ ይህንንም ያሳየናችሁ እኛው ነን፤ ግፍ ረስታችኋል ማለት ነው” በማለት መሳለቃቸው አይቀርም (ስሕተታቸው በተነገራቸው ቁጥር ስለደርግና ስለነገሥታቱ መተረክ የሚቀናቸው ለዚህ አይደል?)። ጥቂት የቀረች የሕሊና እንጥፍጣፊ ያለቻቸው ምናልባት ደውሉ የተደወለው ለእነርሱ እንደሆነ ይረዱት ይሆናል።

 

“መንግሥት የለም ወይ?!” ስንል በብሔርና በቤተሰብ ተደራጅቶ የመንግሥትን ሥልጣንና ሀብት የሚዘርፍ ወሮበላ ድምጻችንን እንዲሰማ፣ መብታችንን እንዲያ(ስ)ከብርልን እየተጣራን አይደለም። “መንግሥት የለም ወይ?!” ስንል ሀገርንና ዜጎችን ለመጠበቅ በአገር ሀብት የተቋቋሙ የመንግሥት ተቋማትን የጭቆና፣ የሥልጣን ማቆያና የዘረፋ መሣሪያ ያደረጉ ወገኖች እነርሱው ራሳቸው ከጫኑብን ቀንበር እንዲታደጉን እየተጣራን አይደለም።

 

“መንግሥት የለም ወይ?!” ስንል ጭቆናን፣ ግፍን እና ዘረፋን ግቡ ያደረገው መንግሥት ተለውጦ ወይም ተወግዶ የዜጎቹን መሠረታዊ መብቶች የሚያከብርና የሚያስከብር፣ ከነልዩነቶቻችን የእኛ የምንለው መንግሥት ይናፍቀናል ማለታችን ነው። “መንግሥት የለም ወይ?!” ስንል የምናከብረውና የሚያከብረን፣ የምናምነውና የሚያምነን፣ ድምጻችንን የሚሰማ ድምጹን የምነሰማው መንግሥት ይገባናል፣ ይኖረናለም ማለታችን ነው። በዚህ አነጋገራችን ዘይቤው የሌለውን እየጠሩ፣ ያለውን ማነወር ነው፤ መንግሥታቸው መንግሥታችን አይደለምና!

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on March 20, 2013
  • By:
  • Last Modified: March 20, 2013 @ 9:57 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar