www.maledatimes.com መጭው ደመና ጥቁረቱ - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

መጭው ደመና ጥቁረቱ

By   /   May 2, 2013  /   Comments Off on መጭው ደመና ጥቁረቱ

    Print       Email
0 0
Read Time:6 Minute, 14 Second

በእውቀቱ ስዩም
ማለዳ መነሣት አልወድም፡፡ዛሬ ግን አቡነ ጴጥሮስ ከመታሰቢያቸው ዙፋን ሲወርዱ ለመታዘብ በማለዳው ካልጋየ ጨክኘ ወረድሁ፡፡ለአቡነ ጴጥሮስ ፍቅር ስል የማለዳ እንቅልፌን ብሰዋ አይቆጨኝም፡፡በቅርቡ በሚከፈተው ጦማሬ ላይ ስለ ጀግናው ጴጥሮስ በሰፊው የመጻፍ ሐሳብ አለኝ፡፡
በቦታው ስደርስ፣የጴጥሮስ ሀውልት በጣውላ ተገንዞ ቆሟል፡፡ድብርት ተጫጫነኝ፡፡ምናልባት አያቶቼ አቡኑ ሲረሸኑ በተመለከቱበት ሰአት የተሰማቸው ስሜት እንዲህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የራስ ቁር የደፉ የቀን ሠራተኞች በአቡኑ ትክሻ ላይ እንደ ወፍ ሰፍረዋል፡፡ ወደ መርካቶ በሚሄዱ ተሳፋሪዎች የተሞሉ ሚኒባሶች አደባባዩን ታክከው ሽው ይላሉ፡፡ ተሳፋሪዎቹ፣ በመስታውት አሻ…ግረው የሚመለከቱት ትእይንት ብዙ የመሰጣቸው አይመሰልም፡፡በፋሲካ አስፈሪ የዶሮ ዋጋ ለተጠመደ አእምሮ ታሪክ ምኑ ነው??
ከተመልካቹ በላይ የፖሊሱ ቁጥር የሚበልጥ መሰለኝ፡፡አንድ ፒካፕ መኪና ስትበር መጣችና ቁና ሙሉ ፌደራል ፖሊስ አራገፈች፡፡ሰብሰብ ብለን በቆምንበት አንዱ ፖሊስ ጠጋ አለና‹‹ እናንተን አይመለከታችሁም ከዚህ ሂዱ›› አለ፡፡ካጠገቤ የቆመ ጎበዝ ‹‹ማየት መብታችን ነው›› ብሎ መልሶ ጮከበት፡፡አሀ! የጴጥሮስ መንፈስ አልከሰመም ማለት ነው፡፡ፖሊሱ ምንም ሳይመልስ ከሬድዮ መገናኛው ጋር እየተመካከረ ካካባቢው ራቀ፡፡923102_10200568936140160_941735044_n
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጋዜጠኛ ጓደኞቼ ካሜራቸውን ታጥቀው ደረሱና ተቀላቀሉኝ፡፡ ሀውልቱን ማስቀረት ስላልቻሉ ምስሉን ቀርጸው ለማስቀረት ተሯሯጡ፡፡
ድንገት ቀና ብየ ሳይ ከሀውልቱ ፊትለፊት ጅማ በር የሚባል ፣ጣልያን የሠራው አሮጌ ሕንጻ ይታየኛል፡፡ባቡሩ የአቡነ ጴጥሮስን መታሰቢያ ደቅድቆ ሲያልፍ፣ጣልያን ሠራሹን ግንብ ንክች አያደርገውም፡፡ጉደኛ ባቡር!!!
በጣውላ የተገነዘውን የአቡኑን ሀውልት ለመሸከም አንድ አዳፋ ረጅም ተጎታች መኪና ብቅ አለ፡፡ዳይኖሰር የመሰለ ክሬን ሀውልቱን ነቅሎ ሲያንጠለጥለው፣ሀውልቱ የነበረበት ቦታ ጥርስ የወለቀበት አፍ መሠለ፡፡ቀሪውን የማየት ፍላጎት ስላልነበረኝ ከጓደኛየ ጋር ወደ ፒያሳ አቀናሁ፡፡ብዙ ነገር እዬተለወጠ መሆኑን አየሁ፡፡የጥንቱ መሀሙድ መዚቃ ቤት ወደ ቡቲክ መቀየሩን አስተዋልሁ፡፡የጥንቱ አያሌው ሙዚቃ ቤት ፍራፍሬ መሸጫ ሱቅ ሆኗል፡፡ከጥቂት ወራት በፊት ብርቱካኔ የሚለው ሙዚቃ ይንቆረቆርበት የነበረው ቦታ ፣አሁን ብርቱካን በኪሎ ይሸጥበታል፡፡
አዲስአበባ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያለጥርጥር፣ባቡር ይኖራታል፡፡ቀለበት መንገዶች ይኖሯታል፡፡አሪፍ ህንጻዎች ይኖሯታል፡፡ነገር ግን፣ ትናንት የሚባለው ነገር አይኖራትም፡፡ A city without past ላዲስ አበባ የተገባ ቅጽል ነው፡፡
ወደ ሰፈሬ የሚሄድ ታክሲ ስፈናጠጥ፣ የሚከተሉት የጸጋየ ገብረመድህን ግጥሞች ሽው አሉብኝ፡፡
….መጭው ደመና ጥቁረቱ፣
ጮቁ ፣ማጡ፣የክረምቱ፣አቤት ዝቅጠቱ ማስፈራቱ
የኛስ ትውልድ አከተመ፣አገራችንን አምክነን
የነገስ ዘር ምን ይበለን፣ስንተወው ሲኦል አውርሰን

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on May 2, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 2, 2013 @ 3:05 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar