www.maledatimes.com የእነ አንዱአለም እና እስክንድር ነጋ ነገር በጠቅላይ ፍ/ቤት ውሎ በወሰን ገብረ ኪዳን “እስክንድር ወንጀለኛ ነው ከተባለ፣ ወንጀሉ ሃገሩን መውደዱ ነው” ሰርካለም ፋሲል - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የእነ አንዱአለም እና እስክንድር ነጋ ነገር በጠቅላይ ፍ/ቤት ውሎ በወሰን ገብረ ኪዳን “እስክንድር ወንጀለኛ ነው ከተባለ፣ ወንጀሉ ሃገሩን መውደዱ ነው” ሰርካለም ፋሲል

By   /   May 2, 2013  /   Comments Off on የእነ አንዱአለም እና እስክንድር ነጋ ነገር በጠቅላይ ፍ/ቤት ውሎ በወሰን ገብረ ኪዳን “እስክንድር ወንጀለኛ ነው ከተባለ፣ ወንጀሉ ሃገሩን መውደዱ ነው” ሰርካለም ፋሲል

    Print       Email
0 0
Read Time:17 Minute, 44 Second

“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላ፣ ታሳዝነኛለች” – አዝማሪ
ለሊት ለሊት እንደ “ዳዊት ደጋሚ” ስለማመሽ ጠዋት ጠዋት ተጋድሜ ማርፈድ ልማዴ ነበር፡፡ ዛሬሬ ዕለተ ሐሙስ ሚያዝያ 26 ቀን 2005 ዓም ካለወትሮዬ በጠዋት ከዕንቅልፌ ተነሳሁ፡፡ እናም ወደ ጠቅላይፍ/ ቤት አመራሁ፡- ዕለቱን እያሰብኩ፡፡ የዛሬው ሐሙስ በክርስትና አማኞች ዘንድ በተለየ መልኩ የሚታሰብ ቀን ነው፡፡ ክርስቶስ ትህትናን በተግባር ያስተማረበት ቀን ነው፡፡ የሐዋርያዎቹን እግር ዝቅ ብሎ ያጠበበት ቀን፡፡ በልማድም ቢሆን ሐሙስ የቀን ቅዱስ ነው ይባላል፡፡ ስለዚህም ከእነ አንዱአለም አራጌ እና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የይግባኝ ማመልከቻ “የተቀደሰ” ዜና እሰማለሁ የሚል ሃሳብ ተሞልቼ ነበር 6 ኪሎ ወደሚገኘው ጠ/ፍ ቤት በእግሬ ያቀናሁት፡፡ በእግሬ ያመራሁት ተከሳሾቹ ከማረሚያ ቤት የሚመጡት አርፍደው ነወ በሢል እሳቤ ነበር፡፡

ሰርካለም ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ

ሰርካለም ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ

ነገር ግን ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ እስረኞቹ ችሎት ገብተው ተቀምጠዉ ነበር፡፡ ወዲያው ከእስረኞቹ ውጪ ችሎቱን ለመከታተል የመጡ ሁሉ ከክፍሉ እንዲወጡ ተደረገ፡፡ ችሎቱ ውስጥ አንዱአለም አራጌ እና እስክንድር ነጋ እንዲሁም በሌላ መዝገብ የተከሰሱ ሌሎች 3 እስረኞች ከአጃቢዎች ቀሩ፡፡ በእነ አንዱአለም መዝገብ ተከሰው ይግባኝ የጠየቁት ሌሎች እስረኞች በስፍራው አልታዩም፡፡ እኛ ኮሪደር ላይ ተሰባስበን ለምን ሌሎቹ እስረኞች እንዳልመጡ እየተወያየን ደቂቃዎች በደቂቃዎች ላይ ነጎዱ፡፡

“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላ፣ ታሳዝነኛለች”
3 ሰዓት ከ50 ደቂያ ሲል ናትናኤለ መኮንን እና ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) አንድ አንድ እጃቸውን በካቴና ታስረው ከውጪ ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ ኮሪደር ላይ ችምችም ብሎ በሚጠብቃቸው ሰው መሃል እያለፉ አንዱ በግራ እንዱ በቀኝ እጁ እየጨበጡኝ አልፈው ወደ ችሎት ገቡ፡- በፖሊስ ታጃበው፡፡፡
3 ሰዓት ከ55 ደቂቃ፤ ዳኞች ወደ ችሎት ገብተው ቦታቸውን ያዙ፡፡ ወዲያው ታዳሚ እንዲገባ ፈቀዱ፡፡ ጥቂት ለችሎቱ በር በቅርበት የቆሙ ታዳሚዎች ገቡ፡፡ የደሃ ሳሎን የምታክለው (ደሃ ሳሎን አለው እንዴ?) ችሎት ወዲያው ጢም አለች፡፡ 4 ሰዓት የግራ ዳኛው አንድ እስረኛ ጠሩ፡፡ እናም ውሳኔያቸውን በቃል ቅልብጭ አርገው ተናገሩ፡፡ በነፃ፡፡ በሌላ ክስ የታሰረውን ሁለተኛ ተከሳሽ ጠሩ፡- በነፃ፡፡ እኔ ከጠቀመጥኩበት ወንበር ጀርባ ያሉ ሁለት ሴቶች ወደመሬት ተደፍተው በደስታ አለቀሱ፡፡ መደሰት እንጂ ማዘን አይገባም ብለን ገፋፍተን “አስወጣናቸው፡፡” የቀጣዩን የእነ እስክንድርን መዝገብ ውሳኔ ለመስማት እየቋመጥን፡፡Photo

“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላ፣ ታሳዝነኛለች”
የመጀመሪያዎቹ መዝገቦች ፍርድ ሲነበብ እኔ በዚያች ጠባብ አዳራሽ ውስጥ ተደራርቦ የተቀመጠውን ሰው ሆን ብዬ ቆጠርኩ፡፡ የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ቦታ አጥታ ከእኔ ጋር አንድ ወንበር ተዳብላ ተቀምጣለች፡፡ ሌሎችም ሰዎች እንደዛው፡፡ ብቻ በዚያች ጠባብ ችሎት ውስጥ ከተሳሾች፣ ከጠበቆች፣ ከእስረኞችና ከችሎት አስከባሪዎች ውጭ 48 ሰው ታፍጓል፡፡ ሌላው ሰው በቦታ ጥበት ኮሪደር ላይ ተኮልኩሏል፡፡ የመሃል ዳኛው ከፊት ለፊታቸው ተደጉሶ የተቀመጠውን ፋይል እየነካኩ በለሠለሰ አንደበት “እንግዲህ እናንተ ፍ/ቤቱን ውሳኔ መቀበል አለባችሁ” አሉ፡፡ በአንድ ወንበር ላይ ተፋፍገን የተቀመጥነው እኔና ሰርካለም እርስ በርስ ተያየን፡፡ ዳኛው ቀጠሉ “በዚህ መዝገብ የቀረበው ክስ በባህሪው ከሌሎች መዝገቦች የሚለይና ውስብስብነት ያለው ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 652/2001 በመሆኑ፣ ሕጉ የተቃኘበትን መረህ መቃኘትን” እንደሚጠይቅ አብራሩ፡፡ በዚህ መሰረት በአምስት የይግባኝ ፋይሎች የቀረቡትን አቤቱታዎች ተያያዥነት ያላቸው በመሆናቸው ፍ/ቤቱ በአንድ ላይ በጥልቀት መርምሮ ዉሳኔ መስጠቱንና ገለፁ፡፡ በቅድሚያ የአቃቤ ሕግን ክስ፣ ቀጥሎም የይግባኝ ባዮችን አቤቱታ፣ ከዚያም በከሳሽና በተከሳሽ ወገኖች የቀረቡትን ምስክሮችና ማስረጃዎችን ይዘት በመመርመር ፍ/ቤቱ የሰጠውን ትንታኔና ውሳኔ በንባብ እንደሚያሙ አሳውቁ፡፡

“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላኝ፣ ታሳዝነኛለች”
ከእኔ በስተቀኝ የተቀመቡት ዕድሜአቸው ወደ ሰባዎቹ የሚጠጋ ጎስቋላ እናት ዳኛው የሚያነቡትን ነገር በቅጡ የተረዱት አይመስሉም፡፡ አንዴ ወደ እኛ፣ መንዴ ወደተከሳሶቹ እየተንጠራራሩ ያያሉ፡፡ እንደዘበት ሸብ ያደረጉት ሻሻቸውን አልሮ የወጣውን ሽበታቸው እየደባበሱ ቁና ቁና ይተነፍሳሉ፡፡ ገፅታቸው ላይ አንዳች ድካምና የሕመም ስሜት የሚነበብባቸው እኚህ እናት ምቾት አልተሰማቸውም፡፡ ዳኛው ንባባቸውን ከጀመሩ ድፍን አንድ ሰዓት አልፏል፡፡ ድንገት ወደቀኝ ዞር ስል ሴትዮዋ የሆነ ስሜት ስልም ሲያደርጋቸው አየሁ፡፡ ሰርካለምን በክርኔ ጎሽመ አድርጌ ወደሴትየዋ ጠቆምኳት፡፡ እጆቺን በእኔ ላይ አሸጋግራ “አይዞዎት” እያለች ጎናቸውን ጨመቅ ጨምቅ፣ አሸት አሸት አደረገቻቸው፡፡ ወዲያው የእፎይታ ትንፋሽ በረዥሙ ተንፍሰው “ነቃ” አሉ፡፡ የክንፈሚካኤል እናት መሆናቸውን ነገረችኝ እየደባበሰቻቸው፡፡ የእስረኛ ቤተሰቦች ከመላመድ ብዛት እርስ በርስ የሚበረታታበት ሕክምና መሆኑ ነው፡- አልኩ ለራሴ፡፡

“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላኝ፣ ታሳዝነኛለች”

ዳኛው ንባባቸውን አላቋረጡም፡፡ “ አንዱአለም አራጌን በሚመለከት፡- ሕገመንግስታዊ መብትን ሽፋን አድርጎ በመጠቀም፣ ከግቦት 7ጋር ለሽብር ተግባር በመመሳጠር፣ ወጣቶችን ለሽብር ተግባር በማደራጀት፣ ለሽብር ዓላማ በመምራት …ወዘተ ናትናኤል መኮንን፡- እንዲሁ ወጣቶችን ወኪል አስተባባሪ በመሆን…. ክንፈሚካኤል ደበበ በህኑዕ የግንቦት 7 አባለ በመሆን፣ በማሴር….እስክንድር ነጋ በሕገመንግስቱ ለዜጎች የተሰጠውን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ሽፋን በማድረግ የግንቦት ሰባትን ዓለማ ለማስፈፀም፣ በስብሰባና በፅሁፍ ሕዝብን ለአመፅ በመቀስቀስ፣ ለኢሳት መረጃ በማቀበል፣ ከጋዜጠኛ ፋሲል የኔ አለም ጋር በመመሳጠር … ወዘተ” መከሰሳቸውን መረጃና ምስክር የቀረበባቸው መሆኑን አተቱ፡፡ ሁሉም ተከሳሾች በተራ ቁጥር 1 በቀረበባቸው ክስ የሥር ፍ/ቤት ያሳለፈውን ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሚነቀፍ ሆኖ እንዳላገኘው ገለፁ፡፡ ሁለተኛው ክስ በአንደኛው ክስ ስር የሚጠቃለል በመሆኑ መሻሩንም አክለው አሳወቁ፡፡ በአጠቃላይ ሁሉም ተከሳሾች በ1ኛ እና በእራተኛ ክስ ጥፋተኛ ተብለው የተወሰነባቸው ውሳኔ የሕግ ስህተት እንደሌለበት አሳወቁ፡፡
ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው የተገኙበት አንቀፅ 17 እና 18 ዓመት እስራት በአጠቃላይ ድምር ወደ34 ዓመት እስራት የሚደነግጉ ቢሆንም፣ በሃገሪቱ ከ25 ዓመት በላይ እስር ስለማይፈቀድ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ እንዲፀና መወሰኑን ገለፁ፡፡ይሁን እንጂ የሥር ፍ/ቤት ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ፍ/ቤት በመድፈር በተጨማሪነት የተላለፈበት የ5 ዓመት እስር እንዲሻር ሲሉ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡

“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላኝ፣ ታሳዝነኛለች”

የፍርዱ ውሳኔ ምንም ለውጥ እንዳላመጣ ቀድማ የተረዳችው ሰርካለም ፋሲል “እስክንድር ወንጀለኛ ነው ከተባለ፣ ወንጀሉ ሃገሩን መውደዱ ነው” ብለህ ፅፍ አለችኝ – በንዴት፡- “ግንቦት 7 ይአስክነድርን እጅ የመጠምዘዝ ኃይል የለውም” አለችኝ በቁጭት፡፡ ችሎቱ ውሳኔውን አሳውቆ ዳኞች እንደተነሱ፣ ተከሳሾች ከፍርድ ሳጥን እየወረዱ ባለ እስክንድር እልሀ በተናነነቀው ስሜት ጮክ “አትጠራጠሩ እውነት ተደብቃ አትቀርም” አለ፡፡ ናትናኤል “የተከራከርነው ፍትህ እናገኛለን ብለን አይደለም፤ ፍትህ ወዳድ ስለሆንን ነው” አለ፡፡ አበበ ቀስቶ “ ለማንኛውም እዚህ መጥታችሁ በእናንተ ኮርተናል” ሲል በችሎት የሰገኘውን ሰው አመሰገነ፡፡
“አንተ የኔ ጀግና ነህ፡፡ ብትሞትም ሙት፣ በእውነትህ ኮርተህ ሙት!” አለች ሰርካለም እንባ እየተናነቃት፡፡ ወዲያው ፖሊሶች ታዳሚውን እየገፋፉ ከችሉት አስወጡ፡፡ በሌላኛው በር አንዱአለምና እስክንድርን አንድ ላይ፣ ክንፈሚካኤል እና ናትናኤልን በአንድ ላይ በካቴና አስረው፡- ወደ ቃሊቲ፡፡

“ አይዞዎት እማማ፤ ወደፊት የሚመጣው አይታወቅም አልኳቸው” የክንፈሚካኤልን እናት፡፡ በእኔ ቤት ማፅናናቴ ነው፡፡
“አዎ የሚመጣው አይታወቅም፣ ይኼስ ይመጣል ብሎ ማን አሰበ፡፡ እናንተ ወጣቶች ራሳችሁ አይዞአችሁ፡፡ ታሰሩ፡፡ አይዞአችሁ፡፡ ግን አትሙቱ” አሉኝ የክንፈ እናት፡፡
“አይዞአችሁ ታሰሩ! ግን አትሙቱብን!” የእኚያን እናት አባባል እያላመጥኩ ከዳኝ፡፡ እንባዬ መጣ፡፡ ዓዓይኔን እንዳያዩ ፊቴን አዞርኩ፡፡
“ሀገሬን ሀገሬን – የምትል ወፍ አለች
እኔን እኔን መስላኝ፣ ታሳዝነኛለች”

አበቃ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on May 2, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 2, 2013 @ 4:49 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar