www.maledatimes.com ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የተነገሩ ያልተሳኩ ትንቢቶችና ራእዮች፡- የኢትዮጵያ ትንሣኤ የተባለው የፍካሬ ኢየሱሱ ‹‹ቴዎድሮስ›› አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ ወይስ …?! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የተነገሩ ያልተሳኩ ትንቢቶችና ራእዮች፡- የኢትዮጵያ ትንሣኤ የተባለው የፍካሬ ኢየሱሱ ‹‹ቴዎድሮስ›› አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ ወይስ …?!

By   /   February 21, 2014  /   Comments Off on ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የተነገሩ ያልተሳኩ ትንቢቶችና ራእዮች፡- የኢትዮጵያ ትንሣኤ የተባለው የፍካሬ ኢየሱሱ ‹‹ቴዎድሮስ›› አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ ወይስ …?!

    Print       Email
0 0
Read Time:27 Minute, 13 Second

በዲ/ን ኒቆዲሞስ ዕርቅ ይሁን ~ nikodimos.wise7@gmail.com

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ከሞይ ኢብራሂም ፋውንዴሽንና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች ትብብርና ድጋፍ በተደረገ አንድ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይ ለሻይ እረፍት በወጣንበት አጋጣሚ ከአፍሪካ ሀገራት ከመጡ እንግዶች ጋር ውይይት ሳደርግ ‹‹ስለ ኢትዮጵያ የበረከት ዘመን›› ከዓመታት በፊት ትንቢት የተናገሩ አንድ የአገራችሁ ቄስ አሉ ታውቀቸዋለህን፣ እስቲ ትንሽ ስለ እርሳቸው ንገረን አሉኝ፡፡

ወይ ጉድ፣ ደግሞ ማን ይሆን የታደለ ዝናው እንዲህ እስከ አፍሪካ ጫፍ የዘለቀ ትንቢት ተናጋሪ ኢትዮጵያዊ ቄስ አልኩኝ በልቤ፡፡ ግና በወቅቱ እኚህ ዝናቸው እስከ አፍሪካ ጫፍ ድረስ የተሰማ የአገራችን ቄስ ማን ሊሆን እንደሚችሉ ባስብም ወደ አእምሮዬ ግን ሊመጡ አልቻሉም፡፡

እንግዶቹ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በተጫነው እንግሊዝኛቸው ስማቸውን ሊጠሩልኝ ቢሞክሩም እኔ ግን ማን እንደሆኑ ላውቃቸው አልቻልኩም፡፡ በኋላ ቁጭ አልንና እኚያን ባለ ራእይ ቄስ ስም በጎግል የመረጃ መረብ አስገብተን ልንፈልጋቸው ሞከርን፡፡ ግና አልተሳካልንም፡፡ ድንገት ‹‹ኦ ማይ ጋድ ጋድ!›› አለችን አንዷ አብራን ከነበረች ደቡብ አፍሪካዊት ሴት የቪዲዮ መልዕክት ስለሆነ በዩ ቲዩብ እንሞክረው አለችና ፍለጋችንን ቀጠልን፡፡ ግና የእኚህን ባለ ራእይና ትንቢት ተናጋሪ ኢትዮጵያዊ ቄስ ስማቸውን አስተካክለው ሊጠሩት ባለመቻላቸውና እኔም ስማቸውን በትክክል መረዳት ስላልቻልኩ ከስንት ሙከራ በኋላ እኚህ ባለ ራእይ ቄስ ማን መሆናቸውን ታወቀ፡፡

አዎን እኚህ ቄስ የመካነ ኢየሱሱ ቄስ በሊና ሳርካ ናቸው፡፡ እኚህ ሰው ኢትዮጵያ ወደፊት ወይም በቅርቡ የአፍሪካ ተሰፋና የመጪው ዘመን የዕድገትና የብልፅግና ማማ ስለመሆኗ ስለተናገሩት ትንቢት ምን ያህል አውቅ እንደሆነ ጠየቁኝ፡፡ ብዙም ባይሆን በጥቂቱ እንደሰማሁ ነገርኳቸው፡፡ እንዲሁም ስለ ትንቢቱ እያዳናቁና እየተገረሙ ለመላው ዓለም ይዳረስ ዘንድ ለምን ግን በእንግሊዝኛና በሌሎች ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አትተረጉሙትም በማለት ጥያቄና አስተያየታቸውን አቀረቡልኝ፡፡

በጊዜው መልስ አልሰጠኋቸውም፡፡ ግና በእኚሁ በቄስ በሊና ትንቢት ምክንያት የተጀመረው ውይይት ሌሎች ሁለት እንግዶችን አካቶ ትንሽዬ ስብሰባን ፈጠረ፡፡ በዕለቱም በዚሁ በኢትዮጵያ ላይ ስለተነገሩ መልካም ስለሆኑ ትንቢቶችና ራእዮች ውይይት የተነሳ ከሻይ እረፍት በኋላ የነበረውን ስብሰባ ሰርዘን ኢትዮጵያና መጪው ብሩህ ዘመኗ አጀንዳንችን ሆኖ ሰፋ ያለ ውይይት አደረግን፡፡ አፍሪካም ሆነ የተቀረው ዓለም ዓይኑን ወደ ኢትዮጵያ የማንሳቱ ነገር በመጠኑም ቢሆን ግርምትን አጫረብኝ፡፡

ምክንያቱ ደግሞ እንዲህ ዓይነቱን የተስፋ ትንቢትና ራእዮችን በሌላ አጋጣሚም ከአውሮጳውያን፣ ከአሜሪካውያንና ከሌሎች አገራት ጭምር ሳይቀር መስማቴ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞንም ‹‹አውሮጳና የተቀረው ዓለም እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ለጥፋት የተቀጠረ የርኩሰት ዓለም ነው፡፡›› እናም ከዚህ ለመጥፋት ከተዘጋጀ የክፋትና የርኩሰት ዓለም ለማምለጥ፣ ብቸኛው መሸሻ አፍሪካ ወይም የእግዚአብሔር ምድር የሆነችው ቅድስት ኢትዮጵያ በመሆኗ ቅሌን ጓዜን ሳልል ወደ ኢትዮጵያ መጥቻለሁ ያለ አንድ የ47 ዓመት ጀርመናዊ ጎልማሳን ታሪክ በሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ራዲዮ አደመጥኩ፡፡ እናም በዚህ ስለ ኢትዮጵያ በተነገሩ ትንቢቶችና ራእዮች ዙሪያ ጥቂት አሳቦችን ለማንሳት ወደድኹ፡፡

የአፍሪካ ኅብረቱ ስብሰባ ገጠመኜ ስለ ኢትዮጵያ ስለሚባሉት ወይም ስለተነገሩትና አሁንም እየተነገሩት ስላሉት መልካም ራእዮችና ትንቢቶች፣ እንዲሁም ይህን ለኢትዮጵያ የተነገሩ መልካም የሆኑ ትንቢቶችን ይፈጽማል ስለተባለውና ለዘመናት በጉጉት ስለሚጠበቀው ስለ ፍካሬ ኢየሱሱ ቴዎድሮስ፣ በአንዳንዶች ዘንድ ደግሞ ይሄ ቴዎድሮስማ ከሁለት ዓመት በፊት በሞት የተለዩን ‹‹ታላቁና ባለ ራእዩ መሪ›› መለስ ዜናዊ ናቸው በሚሉት ተዛማጅ አሳቦች ላይ የራሴን ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድሁ፡፡

በተለይ በቀደመው ዘመን በነበረችው ኢትዮጵያችን ትንቢት፣ ራእይ፣ ንግርት ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከምሁር እስከ አፈ ነቢብ፣ ከአለቃ እስከ ምንዝር፣ ከንጉሥ እስከ ሠራዊት ልዩና ከፍተኛ የሆነ ግምትየሚሰጡት ነገር እንደሆነ ለማወቅ በጥቂቱ የታሪክ ድርሳኖቻችንን ማገላበጥ ብቻ ይበቃናል፡፡ ከእነዚህ በታሪካችን ውስጥ ጉልህ ድርሻ ኖሮአቸው ለዘመናት ሲነገሩ ከነበሩት ትንቢቶች/ንግርቶች መካከል በእጅጉ የገዘፈው ደግሞ፣ ‹‹ቴዎድሮስ የተባለ፣ ፍርድን የሚያደላድል፣ ፍትሕን የሚያሰፍን፣ ጻድቅና ቅዱስ ንጉሥ በኢትዮጵያ ይነግሣል፡፡›› የሚለው የፍካሬ ኢየሱስ ትንቢት/ንግርት ነው፡፡

የፍካሬ ኢየሱስ መጽሐፍ፡- ‹‹ በንጉሥ ቴዎድሮስ ዘመን ኢትዮጵያ ማርና ወተት የምታፈስ የከነዓን ምድር ትሆናለች፡፡›› ይለናል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ደሳስ የሚሉና ለእማማ ኢትዮጵያችን ብሩህ ተስፋን፣ ብርሃንን፣ ፍቅርን፣ ልማትን፣ ብልጽግናን፣ ሰላምን … ወዘተ የሚሰብኩና የሚያውጁ ራእዮችን ትንቢቶችን ከልጅነታችን ጀምሮ ስንሰማ ነው ያደግነው፡፡ መቼም በተግባርም እንዲያ ቢሆንልን ሁላችንም እንዴት በወደድን፣ ምንኛም አብዝተን በታደልን ነበር፡፡

ግና ለኢትዮጵያችን የተነገረው፣ የተተነበዩት ትንቢቶች፣ መልካም ነገሮች ሁሉ የተስፋ ዳቦና በተቃራኒው እየሆኑብን እነዚህ ሁሉ መልካም ነገሮች የተነገሩላት ሌላ ኢትዮጵያ ትኖር እንዴ እስክንል ድረስ የሀገራችን ነገር ግራ የሚያጋባና እንቆቅልሽ ሆኖብን በርካታ ዓመታትን አስቆጥረናል፡፡ በቅርቡ በእኛ ዘመን እንኳን ምርጫ 97 ላይ የነበረውን መነቃቃትና ሕዝባዊ ተሳትፎ የታዘቡ በርካታዎች፡- ‹‹ለኢትዮጵያ የብሩህ ተስፋ ዘመን እየመጣ ነው፣ አይዞአችሁ የኢትዮጵያ የጉብኝት ዘመን በደጅ ነውና›› ንቁ ያሉን ህልም አላሚዎች፣ ራእይ ተናጋሪዎች፣ ትንቢት ተንባዮችን ነበሩን፡፡

በተለይም ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎችን፣ ከታናናሾች እስከ ታላላቆቹ፣ አሉ የሚባሉ የሀገሪቱን ምሁራንን ጭምር ሳይቀር በጥላው ያሰባሰበው ቅንጅት የተባለው ፓርቲ ኢትዮጵያችንን የሚታደግ፣ ሀገራችን ለዘመናት ስትመኘው የነበረውን ሰላም፣ ዕድገትና ብልጽግና የሚያሰፍን፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለምስኪኗ ኢትዮጵያችን የተላከ መልዕክተኛ ነው የተባለለት ቅንጅት በአገራችን ስሙ ገኖና ነግሦ ነበር፡፡ በአንዳንዶች ዘንድም ይህ ፓርቲ የሰዎች ስብስብ ብቻ የኾነ ፓርቲ አይደለም መንፈስም ጭምር እንጂ እስኪባል የብዙዎችን ልብና ቀልብ ለመግዛት ችሎ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡

ብዙዎችም የነገይቱ ኢትዮጵያ ተስፋና ብሩህ ዘመን ከዚህ ፓርቲ ሕልውና ጋር የተሳሰረ ነው አሉን፣ እኛም በጄ፣ እሺ ብለን አምነን ተቀብለናቸው ነበር፡፡ የፓርቲው አመራሮችም ኢትዮጵያን ከውርደት ዘመን ለመታደግ የተላኩ የዘመናችን ሙሴዎች ናቸው እስኪባሉና ቅንጅት ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያን ሕዝብ ነፍስ የሚገዛ፣ የሚነዳ ከፈጣሪ ዘንድ የተላከ ‹‹መንፈስም ጭምር ነው›› እስኪባልለት የደረሰበትን ያን አስገራሚ ግን ደግሞ ክፉና አሰቃቂ ትዝታ በአእምሮአችን ትቶ የሔደውን ምርጫ 97 እና ገድለ ቅንጅትን ሁላችንም አንረሳውም ብዬ አስባለሁ፡፡

በወቅቱ ቅንጅት የኢትዮጵያ ተስፋ የመሆኑ ትንቢት ደግሞ በተለይ በፕሮቴስታንቱ ዓለም በእጅጉ የታመነበትና የተመሰከረለት ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ በዚሁ ትንቢትና ራእይ አቅላቸውን የሳቱ አንዳንድ የፕሮቴስታንት አማኞችና አገልጋዮችም ይህንኑ እውነት በቤተ አምልኮቻቸው ለአማኞቻቸው የምስራቹን ከመስበክና ከማረጋገጥ አልፈው የቅንጅት ፓርቲ አባል በመሆንና በ97ቱ ምርጫ በመወዳደር ለኢትዮጵያ የተባሉትን ትንቢቶች ሁሉ ከፍፃሜ ለማድረስና የትንቢቱ ፈጻሚ ለመሆን ሲተጉ ታዝበናቸዋል፡፡

ግና የሆነው ከታየው ራእይ ከተነገረው ትንቢት ሁሉ በተቃራኒው ነበር፡፡ እነዛ ብዙ የተባለላቸውና ብዙዎችን ያማለሉት መልካም ትንቢቶችና ራእዮች እንደ ግንቦት ዳመና በነው ነበር የጠፉት፡፡ ለኢትዮጵያ ይመጣል የተባለው መልካም ዘመን እንደተተነበየው ሳይሆን 1997 ሀገሪቱን የኀዘን ከል አልብሷት ዐለፈ፡፡ በወቅቱ ተማሪ በነበርኩበት በአዲስ አበባው ዩኒቨርስቲ የነበረውን ቀውጢ፣ ተቃውሞ፣ የአጋዚዎቹን ምሕረት የለሽ የጭካኔ ዕርምጃ፣ የበርካታ ምስኪን ኢትዮጵያውያን እናቶችን ዋይታና ሰቆቃ አሁንም ድረስ በአእምሮዬ ሕያው ሆኖ አለ፡፡

እናም ያን የሰቆቃ ዘመንና እናት ኢትዮጵያ ዳግመኛ ወገቧን በገመድ ታጥቃ የማኅፀኗ የአብራክ ክፋይ ለሆኑት ለሟችም ለገዳይም ልጆቿ መሪር ሙሾን አወረደች፣ እ…ዬ…ዬ…ዬ…፣ ዋይ…ዋይ….ዋይ… እያለች እንባዋን ወደ ሰማይ ረጨችው፡፡ የጥፋት ሠራዊቶች፣ የሞት አበጋዞች በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ

ዳግመኛ የጥፋት ሰይፋቸውን መዘው ምድሪቱን አኬልዳማ፣ የድም ምድር አደረጓት፡፡ ምንም የማያውቁ፣ ሮጠው ያልጠገቡ ሕጻናት እንኳን ሳይቀሩ በጠራራ ፀሐይ የአልሞ ተኳሾች ጥይት ራት ሆኑ፡፡እማማ ኢትዮጵያ ዳግመኛ የኀዘን ሰይፍ ነፍሷን ሸቀሸቀው፡፡ የወላድ እናቶች ጩኸት የኢትዮጵያን ሰማይ አደፈረሰው፣ ጩኸት፣ ዋይታና እሪታ በኢትዮጵያ ምድር ከፍ ብሎ ተሰማ፡፡ ሰላም፣ ብርሃን፣ ተስፋ እየመጣ ነው ተብሎ በተተነበየባት ምድር ይህን እልቂትና ሰቆቃ፣ ይህን ያልተጠበቀ መዓትና ጉድ ያዩና የሰሙ ሁሉ ‹‹እግዚኦ የአንተ ያለህ!›› ሲሉ የኢትዮጵያን አምላክ ሁሉም በየቤተ እምነቱ ተገኝቶ በጾምና በጸሎት፣ በእንባ ተማጸኑ፣ ተለማመኑ፡፡

ይህን የወገኖቻቸውን ሞትና እልቂት፣ ይህን የአምባገነኖችን ወደር የለሽ ጭካኔና ክፋት በመገናኛ ብዙኃንና በኢንተርኔት ሲከታተሉ የነበሩ በአውሮጳና በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵውያን በእንባ እየታጠቡ ይህን እብደት፣ ይህን እልቂትና ፍጅት ኃያላኑ መንግሥታት ጣልቃ ገብተው ያስቆሙ ዘንድ በጥይት የተበሳሱ፣ አንጎላቸው የተፈረከሰና በደም የተነከሩ አሰቃቂ የሆኑ የወገኖቻቸውን ምስል በመያዝ በአሜሪካና በአውሮጳ ኤምባሲዎች ደጃፍ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አሰሙ፡፡

የኢትዮጵያ ተስፋ ተብሎ ትንቢት የተነገረለት፣ ራእይ የታየለት ‹‹መንፈስ›› እንጂ ፓርቲ ብቻ አይደለም የተባለውም ቅንጅት፣ ራሱንም ኢትዮጵያንም መታደግ ሳይችል ቀርቶ ፍጻሜው ግዞትና ወኅኒ ሆነ፡፡ የነገይቱ ኢትዮጵያ ሙሴዎች ናቸው ተብሎ የተነገረላቸው የፓርቲው አመራሮችም ከመለያየት አልፈው፣ በነገር አርጩሜ እርስ በርሳቸው መዠላለጡን ተያያዙት፡፡ እርስ በርሳቸው እስኪከፋፉና እስኪጠላሉ የጓዳ ምስጢራቸውን ሁሉ ሳይቀር ለአደባባይ በማብቃት መወነጃጀልን ፋሽን አደረጉት፡፡

በፍቅርና በይቅርታ ልብ መሸካከም አቅቷቸው፣ እንደ ገዢው ፓርቲ እንደ ኢህአዴግ ያለ ብልህነት፣ ምሥጢር ጠባቂነትና የፓርቲ ዲስፕሊን ጎድሎአቸው ዛሬም ድረስ ጥፋቱ የአንተ እንጂ የእኔ አይደለም በመባባል ከቂም በቀል አዙሪት መውጣት እንደተሳናቸው በተለያዩ መድረኮች በሚያሰሟቸው ንግግሮቻቸውና በሚያወጧቸው መጻሕፍቶቻቸው እየታዘብናቸው፣ እየበገንን ነው፡፡ለእማማ ኢትዮጵያ ብሩህ ዘመን ያመጣሉ ተብሎ ትልቅ ተስፋ የጣለባቸውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የሆነስ ሆነና ለመሆኑ ኢሕአዴግ መንበሩን ለቆላቸው ቢሆን ኖሮ ይመሩን የነበሩት እንዲህ ዓይነቶቹ እርስ በርሳቸው የማይተማመኑ፣ ምስጢራቸውን የማይጠብቁ፣ የሕዝብ ፍቅር ሳይሆን የሥልጣን ፍቅር ያሰከራቸው ሰዎች ነበሩ እንዴ ሲል ክፉኛ ታዘባቸው፣ አዘነባቸውም፡፡

እናም ‹‹ከማያውቁት ምንትስ የሚያውቁት ምን ይሻላል›› በሚል እስከ ጎዶሎውና ክፋቱም ቢሆን ኢህአዴግ ይግደለኝ ሲል ሕዝቡ በቅንጅት ፓርቲና በአመራሮቹ አመኔታም ተስፋም አጣባቸው፡፡ ያ ሁሉ ትንቢት የጎረፈለት፣ ራእይ የታየለት ድርጅትም አይሆኑ ሆኖ በታሪክ ማኅፀን ሸማ ውስጥ ተጠቅልሎ በነበር ብቻ እንድናስታውሰው የግድ ሆነ፡፡

ብዙዎችም ያ ብዙ ልብንና መንፈስን የሚያማልሉ ለኢትዮጵያ የተነገሩ ትንቢቶችና ታየ የተባለ ራእይስ ፍጻሜው ወዴት ነው፣ ‹‹የሰው ሳይሆን ይህ የእግዚአብሔር ጣት ነው፡፡›› ተብሎ የተነገረለት፣ ያ በሀገሪቷ አሉ የተባሉ ዝነኛ ምሁራንኖችንና ታላላቆችን ያቀፈ ፓርቲ-ቅንጅት ፍጻሜው እንዴት እንደ ልጆች ጨዋታ ባለ መልኩ ‹‹ዕቃው ፈረሰ፣ ዳቦው ተቆረሰ፡፡›› ሊሆን ቻለ በማለት አብዝተው ጠየቁ፡፡

እስካሁንም ለዚህ ጥያቄ ከልብ የሚደርስ አጥጋቢ ምላሽ የሰጠ ከቅንጅቶቹም ወገን ይሁን ትንቢቱን ከተናገሩለት መንፈሳውያኑ ጎራ ወይም መንፈሳዊ ነን ከሚሉት ባለ ራእዮችና ትንቢት ተናጋሪዎች ዘንድ እንዳሉ በግሌ አላጋጠመኝም፡፡ የሆነ ሆኖ ግን አሁንም ድረስ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የተነገሩ ትንቢቶች፣ የታዩ ራእዮች ከምድራችን አልፎ አፍሪካ፣ አሜሪካና አውሮጳ ድረስ ሳይቀሩ ተሻግረው ብዙዎች የኢትዮጵያ መጎብኘት፣ ለኢትዮጵያ ሊመጣ ያለው የበረከት ዘመን፣ የአፍሪካና የሌላው ዓለም ሁሉ ተስፋ እንደሆነ በተለያዩ መድረኮች አብዝተው እየነገሩን ነው፡፡

በቀጣይ ጽሑፌ የኢትዮጵያ ትንሣኤ፣ ለሕዝቦቿም ፍቅርን፣ ሰላምንና ብልጽግናን ያሰፍናል ተብሎ ለብዙ ዓመታት ትንቢት የተነገረለትና በአንዳንዶች ዘንድም ይህ የፍካሬ ኢየሱሱ ቴድሮዎስማ አቶ መለስ ነበሩ ወይስ …?! በሚለው ጉዳይ ላይ በቀጣይ ሳምንት ጥቂት አሳቦችን ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 10 years ago on February 21, 2014
  • By:
  • Last Modified: February 21, 2014 @ 9:45 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar