www.maledatimes.com በአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ስም የተጀመረው ቲጂ ቲቪ ውግዘት ቀረበበት ! - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

በአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ስም የተጀመረው ቲጂ ቲቪ ውግዘት ቀረበበት !

By   /   May 28, 2013  /   Comments Off on በአርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ስም የተጀመረው ቲጂ ቲቪ ውግዘት ቀረበበት !

    Print       Email
0 0
Read Time:23 Minute, 32 Second

በሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ (የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ባለቤት ወንድም ነኝ የሚል) በሙዚቃው ንጉስ ስም አንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ መክፈቱን ከሰማሁ ቆየሁ። ለጥልዬ አይደለም አንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ ሌላም ሌላም ይገባዋል።

 

የሚያሳዝነውና የሚያሳፍረው ግን የተከፈተው ቴሌቭዥን ጣቢያ የፕሮግራም ጥንጥኑና ቅንብሩ የሙዚቃውን ንጉስ ገድለ-ጥበብ ከመዘከር ይልቅ ዘረኛውን የወያኔ መንግስት ከተቃዋሚ ወገን ጥቃት ለመከላከል ሲተጋ መገኘቱ ነው።

 

የጥላሁን ገሠሠ ባለቤት የወ/ሮ ሮማን ወንድም ነው የሚባለው ሰው የሚመራው ይህ ቴሌቭዥን ጣቢያ፤ በብርቅዬው አርቲስት ስም ይህን ርካሽ ተግባር ሲፈጽም፤ ተው ባይ ማጣቱ ሌላው በግርምት ያስደመመኝ ጉዳይ ነው።

 

ለመሆኑ የጥላሁን የአብራኩ ክፋይ የሆኑት ልጆቹ ይህ ሰው የገዘፈ ህዝባዊ ፍቅር ባለው በአባታቸው ስም በከፈተው ቴሌቭዥን ጣቢያ ህዝባዊነት የሌለውን መንግስት ሲያገለግልበት ትንሽም የመቆርቆር ስሜት ያላሳዩት ለምን ይሆን? ይህም ከግለሰብ መብት ተቆጥሮ ይሆን?

 

የምጣደ ሳለ የእንቅቡ ተንጣጣ እንዲሉ፤ ልጆች እያሉ አማችየው ዝክር አውጭና ነጠላ አሸራጭ፤ ፊታውራሪና አጋፋሪ የሆነበትስ ሚስጥር ምንድነው?

የጥላሁን ባለቤት ወ/ሮ ሮማንስ የወንድማቸውን ፈር የለቀቀና ዓላማውን የሳተ እንቅስቃሴ በዝምታ ማየታቸው ለምን ይሆን?

 

እንደኔ እምነት ጥላሁን ከልጆቹም ከባለቤቱም በላይ የህዝብ ልጅ ነው። ጥላሁን ተከታታይ ሶስትና አራት ትውልድን መተኪያ በሌለው ችሎታው ሲያስደስት የኖረ ድንቅና ውድ የሀገር ቅርስ ነው። በመሆኑም በስሙ የሚደረግ በጎ ነገር ሁሉ ኢትዮጵያዊውን እንደሚያስደስት፤ በስሙ የሚደረግ ውስልትናና ጸያፍ ተግባርም እንደዛው ሁሉንም ያስከፋል፣ ያስቆጣል።

 

በርግጥ በማህበራዊ ህይወት የግንኙነት አግባብ፤ ለማንም ግለሰብ የሚቀርበው ቤተሰቡ ነው። ለዚህም ነው በጥላሁን ስም ሲነገድ በቅርብ ያለው ቤተሰብ (ባለቤቱና ልጆቹ) ቅድሚያ ተቆርቋሪ ለምን አልሆኑም ስል የጠየቅኩት። ይሁን እንጂ ቤተሰቡ ዝም ቢልም የብርቅዬውን አርቲስት የጥበብ ትሩፋት የተቋደሱ ሁሉ፤ እኔንም ጨምሮ በስሙ ርካሽ ተግባር ሲፈጸም ዝም ብንል በጆሯችን የተንቆረቆረው መረዋ ድምጹ ይወቅሰናል። ይህን ጽሁፍ ያቀረብኩትም ከዚሁ ወቀሳ ለመዳን ነው።

 

ግለሰቡ ለቴሌቭዥን ጣቢያው የሰጠው ስም TG የሚል ነው። Tilahun Gessesse የሚለው ክቡር ስም ምህጻር መሆኑ ነው። ይህ ስም በኢትዮጵያዊ ዜጋ ልብ ውስጥ ግዙፍ የክብርና የፍቅር ቦታ ያለው ስም ነው። የአማች ተብዬውም ደፋ ቀና በጋብቻ አማካኝነት የነበረውን የመቀራረብ አጋጣሚ በመጠቀም ከከበረው ስም፤ ሽርፍራፊ ክብርን፤ ከገዘፈው እውቅናና ፍቅር፤ ቅንጥጣቢ እውቅናን አገኝ ብሎ ነው።

 

በነገራችን ላይ ስለጥላሁን ገሠሠ የአማችነት ቅርርብ ያለው ሰው ቀርቶ የጥበብ ስራውን የሚያደንቅ ማንም ግለሰብ መታሰቢያ የሚሆነውን ስራ ቢሰራ የሚያስመሰግነው እንጂ የሚያስወቅሰው አይደለም። የሚያስወቅስ የሚሆነው ስሙን ለግል ዓላማና ጥቅም፤ ለማዋል መሞከር ነው።

 

የወዳጄ ቁምነገር አዘል ቀልድ!

ከአንድ ወዳጄ ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ስንወያይ እንደ ዘበት ጣል ያደረገውንና ከልቤ ያሳቀኝን ነገር እናንተንም ፈገግ ቢያደርግ እዚህ ላይ ላንሳ፤

 

Tilahun Gessesse የሚለውን ክቡር ስም ምህጻር አድርጎ TG TV በሚል ስም በአማቹ የተከፈተ የቴሌቭዥን ጣቢያ የሚዘጋጀው ፕሮግራም ጥላሁንን የሚዘክር ሳይሆን ለወያኔ መንግስት ጥብቅና የቆመ ነው፤ ብዬ ለወዳጄ ነግሬው፤ ሰሞኑን በዚሁ ቴሌቭዥን የተላለፈውን አሰልቺ ፕሮግራም እንዲመለከት ነገርኩት። ወዳጄም ክሉፑን ለ5 ደቂቃ ያህል ተመልክቶ ሰለቸውና አቆመው። እናም ምን አለኝ መሰላችሁ …

 

TG የሚለው ምህጻረ ቃሌ Tilahun Gessesse ለሚለው ሳይሆን TPLF Government ለሚለው የቆመ ይሆናል ብሎ በጣም አስቆኛል። በጣም ያስደነቀኝ ደግሞ የወዳጄ ፈጣን ስያሜ በትክክልም የፕሮግራሙን ይዘት የሚመጥን ስም መሆኑ ነው።

 

ይህ አማች ተብዬ ግለሰብ የወያኔን መንግስት መደገፍ መብቱ ነው። መብቱ ያልሆነው ግን በህዝብ ልጅ ስም በተከፈተ ቴሌቭዥን ጣቢያ መጠቀሙ ነው። ጥላሁን የህዝብ እንጂ የመንግስት ወይም የማንም የጎሳም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። በጥላሁን ገሠሠ ስም በተከፈተ ቴሌቭዥን ጣቢያ ምንም አይነት ፖለቲካ ነክ ዘገባዎችና ቅንብሮችን ማቅረብ በስሙ መነገድ ነው።

 

የጥላሁን የቅርብ ቤተሰብ በተለይም ልጆቹ የቴሌቭዥን ጣቢያው ስያሜው እንዲለወጥ አልያም የፕሮግራም ይዘቱን እንዲያስተካከል መጠየቅ ይገባቸዋል እላለሁ። እስካሁን ለማሳየት የሞከርኩት የአማች ተብዬው እውቅና ናፋቂ ግለሰብ ቴሌቭዥን ጣቢያ የፈጸመው እንደ ተቋም “የመታሰቢያ ተቋምን” መርህ ያልተከተለ፤ እንደ ግለሰብም በሟች ስም የመነገድ እጅግ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ነው። ይህን የጽሁፌን ክፍል የምቋጨው የዚሁ ግለሰብ እህትና ለአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ባለቤት ለሆኑት ለወ/ሮ ሮማንና ለአብራኩ ክፋይ ልጆቹ በማስተላልፈው ጥያቄ አዘሌ መልዕክት ነው።

 

ይድረስ ለክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠ ባለቤት፣ ለወ/ሮ ሮማን

ወንድምዎ መሆኑ የተገለጸው ግለሰብ ለውድ ባለቤትዎ መታሰቢያ በሚል በስሙ በከፈተው የቴሌቭዥን ጣቢያ እየቀረበ ያለው ፕሮግራም ከባለቤትዎ ከአርቲስት ጥላሁን ማንነትና ብሔራዊ ስብዕና ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው፤ ጭራሹንም ተቃራኒ መሆኑን አስተውለዋልን? ከሆነስ ለምን በዝምታ ማየትን መረጡ?

 

ከማንም በበለጠ ለአርቲስት ጥላሁን የሚቀርቡና ሕጋዊ ባለመብት እንደመሆንዎ በስሙ የሚደረግን የየትኛውንም እንቅስቃሴ ይዘት መመርመርና መከታተል ኃላፊነት አለብዎት። ከዚህ አኳያ የወንድምዎን ተግባር ለማረም ምን ጥረት አድርገዋል? ካሁን በኋላስ …?

 

ይድረስ ለክቡር ዶ/ር ጥላሁን ልጆች፦

በአባታችሁ ስም በተከፈተ ቴሌቭዥን ጣቢያ የፖለቲካ ሥራ ሲሰራ እየተመለከታችሁ ዝምታው ለምንድነው? ጥላሁን ወዳጅ እንጂ ጠላት የለውም፤ በጥላሁን ስም ሊወራ፤ ሊሰራ፤ ሊሰበክ የሚገባውም ፍቅር እንጂ ጥላቻ አይደለምና እንደ ልጅነታችሁ የአባታችሁን ክቡር ስም በተገቢው ቦታ እንዲውል ታደርጉ ዘንድ ይገባችኋል እላለሁ እንደምታደርጉም ተስፋ አለኝ።

 

አሁን ደግሞ የዚሁኑ አማች ተብዬ ግለሰብ ፕሮግራም ይዘት በተመለከተ ጥቂት ላነሳሳ።

ይህ ግለሰብ ከላይ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው የቴሌቭዥን ጣቢያውን በጥላሁን ገሠሠ ስም ያደረገው ጥላሁንን ያለ ተመልካች ለመሳብ ነው። በርግጥ ስሙን መጠቀሙን ትርጉም ለመስጠት ያህል ሙት ዓመቱን ይዘክራል።

 

ከዚያ በተረፈ ግን ትልቁ ሥራው በዲያስፖራ የሚገኙ ግንባር ቀደም የወያኔ ተቃዋሚ አክቲቪስቶችን ማጥላላትና ስም ማጥፋት … ነው።

 

ቀደም ሲል የአርቲስት ታማኝን ስም ለማጥፋት ሞከረ፤ የአርቲስት ታማኝ ስም በቀላሉ ሊጠፋ የማይችል ሆኖ እራሱኑ ሊያጠፋው ሲል አቆመ። አሁን ደግሞ ጋዜጠኛ አበበ ገላውን።

 

በሚሚ ስብሃቱ እዝ ስር እንደሚገኙትና የወያኔን መንግስት ጸሃይነት ለማሳየት ተአቅምና ችሎታቸው በላይ ብልጭ ድርግም ሲሉ የሚስተዋሉት ቅጥረኞች ሁሉ ይህም ግለሰብ የወያኔን መንግስት ለማገልገል የተሰለፈ ነው። የዚህን ለየት የሚያደርገው እንደሌሎቹ በራሱ ብልጭ ድርግም ማለትም ተስኖት ከወርቅ ጸዳል የሚያበራ ስምና ገድል ባለው አማቹ ሃውልት ለመከለል መሞከሩ ነው።

 

ይህ ግለሰብ እራሱን ጋዜጠኛ አድርጎ መቁጠሩ በራሱ ድፍረቱን የሚያሳይ ነው። ጋዜጠኝነት በቴሌቭዥን መስኮት ከረባት አስተካክሎ የተጻፈ ከማንበብ እጅግ የገዘፈና የሰፋ ሙያ ስለ መሆኑ ግንዛቤ እንደሌለው የሚመሰክረው በወጉም ያልተሰለቀው የአረፍተ ነገር አዘረጋጉና እጅግ የሚያስጠላው የድምጽ አወጣጥ ዘዬው ነው።

 

የዚህን ግለሰብ ስራ ያየሁት ጋዜጠኛ አበበ ገሊው በኢሳት ቀርቦ፤ መለስ ዜናዊ ተቃውሞ በቀረበበት ወቅት አንገቱን አልደፋም ነበር። ኢሳት አቀናብሮት ነው በሚል አንድ ግለሰብ ስም ማጥፋት መጀመሩን ሲናገር ነው።

 

አቤ ትልቅ ስህተት የተሳሳተው እዚህ ላይ ነው። ግለሰቡ በአበበ ገላው ስሙ መጠቀሱ በራሱ ሎቶሪ የወጣለት ያህል እንደሚያስደስተው የተረዳሁት ደግሞ የእለት ጉርሱን ለማግኘት ዲያስፖራውን በማጥላላት ቀበዣዥሮ የሚለጥፈው ቪዲዮ በተመልካች ድርቅ የተመታ መሆኑን ስመለከት ነው። 100 ሰው ያልተመለከተው clip አበበ ገላው ስሙን ከጠራው በኋላ ጥቂት መቶዎች ተመለከቱት። ይህ ደግሞ ለሱ ሎቶሪ … ነው።

 

አቤ እንደ ሶቅራጥስ ማድረግ ነበረበት

በታዋቂ ሰዎች የሚቀና አንድ ደደብ ቢጤ ሰው፤ ሁሉም በሆነ ነገር ለመታወቅ ያልምና ይመኝ ነበር። ይሁን እንጂ ድድብናው የእውቅናውን በር ከርችሞበት ሁሉም ምኞቱ ከምኞት ሊያልፍ ባለመቻሉ ይናደድና ይቅበጠበጥ ነበር። ታዲያ አንድ ቀን ይህ ሰው፤ ፈላስፋው ሶቅራጥስን መንገድ ላይ ሲሄድ ያየውና ድንገት አንድ ሃሳብ ብልጭ ይልለታል። ከሶቅራጥስ ጋር ቢጣላ ሊታወቅ እንደሚችል ይታየዋል። ይህንኑ ሃሳቡን ወደ ተግባር ለመለወጥ ወዲያውኑ ከሶቅራጥስ ኋላ ከተል ከተል እያለ ኮቱን ይጎትተዋል። ሶቅራጥስም ትንኝ የነካው ያህል ሳይሰማው ጉዞውን ይቀጥላል። ሰውየው በሶቅራጥስ ዝምታ ይናደዳል … ቀጥሎም ኮቱን መጎተቱን ያቆምና ከኋላው እየተከተለ መቀመጫውን ደጋግሞ በእርግጫ ይመታዋል። ሶቅራጥስ አሁንም ፊቱን ሳያዞር ጉዞ ቀጠለ … በዚህ ግዜ ደደቡ ሰው በጣም ተገርሞ እርግጫውን ያቆምና ሮጥ ብሎ ከሶቅራጥስ ፊት በመቅደም፤

 

“መምህር ሆይ! ይህን ያህል ስረግጥህ ዝም ብለህ መልስም ሳትሰጥ መሄድህ ለምንድነው?” ይለዋል። ሶቅራጥስም ሲመልስ፤ “አህያ ረገጠኝ ብዬ እንዴት መልስ እሰጣለሁ” አለው ይባላል።
አበበ ገላውም የዚህን ግለሰብ ጉንተላ ልክ እንደ ሶቅራጥስ አህያ ረገጠኝ ብዬ መልስ አልሰጥም ብሎ ቢያልፈው ጥሩ ነበር። ባይሆን አበበ ገላው ከሶቅራጥስ ኮረጀ እንዳይባል ሆዳምን ጨምሮ፣ “ሆዳም አህያ ረገጠኝ ብዬ እንዴት መልስ እሰጣለሁ?” ሊለው ይችል ነበር። እናም አቤ እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ይህ ሰው ስሙን መጥራትህ በራሱ ትከሻው ላይ ማዕረግ እንደጫንክለት ይቆጥረዋልና ለወደፊቱ የሶቅራጥስ ትዕግስት ይስጥህ እላለሁ።

 

በዚህ ጽሁፌ ውስጥ የውዱን ኢትዮጵያዊ አርቲስት ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰን ስም ከ20 ግዜ በላይ ጠቅሻለሁ። ይሁንና በራሱ ስራና በራሱ ማንነት መታወቅና አንቱ መባል እንዳይችል ድድብናው ጋሬጣ ሆኖበት፤ ሶቅራጥስን በመጎንተል ለመታወቅ እንደሞከረው ከንቱ ሰው ሁለ፤ ከዚህ ክቡር የህዝብ ልጅ (ከጥልዬ) ጋር በጋብቻ የመዛመድን አጋጣሚ የ40 ቀን እድል የሰጠችው የእውቅናው በር መክፈቻ ቁሌፍ ቆጥሮ … የሚሟዘዘውን ግለሰብ ስም ግን አንዴም ቢሆን ስሙን ለመጥራት አልፈለኩም። እንደ ሶቅራጥስ እኔም …

 

ወደ ጽሁፌ መቋጫ ላይ ደርሻለሁ፤

ጽሁፌን የምቋጨው ለአንባቢያን ዋና ዋና የጽሁፌን ጭብጥ በማስያዝ ነው። ምክንያቱም ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች ስለሚኖሩ ከወዲሁ መልስ ለመስጠት ነው።

 

የዚህ ጽሁፍ ጭብት የጥላሁን አማች የተባለው ግለሰብ በቴሌቭዥን ጣቢያው ያስተላለፈው ጉዳይ ትክክል ነው አይደለም በሚል ለመገምገም አይደለም። የዚህ ጽሁፍ ጭብጥ የህዝብ ልጅነቱ የተረጋገጠው ክቡር አርቲስት መታሰቢያ ተብሎ በተከፈተ ቴሌቭዥን ጣቢያ ኪነ-ጥበብ እንጂ ስነ-ፖለቲካ መቅረቡ አግባብ አለመሆኑን ማሳየት ነው።

 

የቀረበውም የፖለቲካ አመለካከት በስልጣን ላይ ያለውን ዘረኛ መንግስት የወገነ መሆኑ ደግሞ ሌላው አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ማሳየትና የሚመለከተው የቅርብ ቤተሰብ እርማት እንዲያደርግ ለማሳሰብ ነው። በዚህ በአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ስም በተቋቋመ ጣቢያ የመንግስት ተቃዋሚምም ሆነ ደጋፊ ብቻ ምንም አይነት የፖለቲካ አመለካከት ሊንሸራሸርበት እንደማይገባ ለማሳየት ነው።

 

የሰራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
የተወዲጁን አርቲስት የክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሠሠን ነፍስ በቀኙ ያኑርልን!

ከአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ አፍቃሪዎች አንዱ!http://www.ethiopiazare.com/articles-55/opinion/2947-betelahun-gessesse-seme-eyenegede-yalew-sew

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on May 28, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 30, 2013 @ 5:08 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar