www.maledatimes.com የባሕታዊው ማስታወሻ በገ/ ክርስቶስ ዓባይ ግንቦት 10 ቀን 2005 ዓ/ም - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የባሕታዊው ማስታወሻ በገ/ ክርስቶስ ዓባይ ግንቦት 10 ቀን 2005 ዓ/ም

By   /   May 29, 2013  /   Comments Off on የባሕታዊው ማስታወሻ በገ/ ክርስቶስ ዓባይ ግንቦት 10 ቀን 2005 á‹“/ም

    Print       Email
0 0
Read Time:21 Minute, 44 Second

ከፍል ሁለት

አባ ወ/ሥላሴ እንደተለመደው አገራችንን ኢትዮጵያን ሰላም አድርግልን፡ሕዝቧን ከረሃብ፤ከበሽታ፤ ከችግር፤ ከመጥፎ አስተዳደር፡ ከስደት ጠብቅልን። ለአስተዳዳሪዎችና ለበላይ ኃላፊዎች ማስተዋልንና ጥበብን አድላቸው። ከጎረቤት ሀገራትና ከቀረው የዓለም ሕዝቦች ጋር ሰላምን አውርድልን እያሉ ሲጸልዩ ሳለ ድንገት መልአክ መጥቶ “የተከበርክ ወ/ሥላሴ ሆይ ሰላም ላንት ይሁን! የነገሩትን የማይረሳ ፤የለመኑትን የማይነሳው አምላካችን በሰጠህ ቃል ኪዳን መሠረት ለረጅም ዓመታት ስትጋደልላት የነበረችውን ነፍስ የመጨረሻ መዳረሻዋን ታይ ዘንድ ልወስድህ መጥቻለሁ “ አላቸው። አባ ወ/ሥላሴም “እነሆኝ! የፈጣሪያችን ትዕዛዝ ይፈጸም ዘንድ እንደወደድክ አድርግ” አሉት።

 

በዚህ ጊዜ መልአኩ እጁን ከራሣቸው በላይ በማድረግ ክንፎቹን እንደ አውቶማቲክ ጃንጥላ ከኋላው በዘረጋቸው ጊዜ የአባ ወ/ሥላሴ ነፍስ ከሥጋቸው ተለይታ ወጣች፤ ወዲያውም መልአኩ ይዟት ወደሰማይ ዐረገ።

ኢዮር ከተባለው የሰማይ ክፍል ሲደርሱ ዕልፍ አዕላፍ ብርሃናዊያን መላዕክት እየጨፈሩና እየተደሰቱ የአምላካችን ባለሟል፤ “ወ/ ሥላሴ እንኳን ደህና መጣህ፤ ጠላትክን በጸሎት ድል የመታህ።” እያሉ እየዘመሩና እያሸበሸቡ በከፍተኛ ድምቀት ተቀበሏቸው።

መልአኩ በታዘዘው መሠረት በቅድሚያ አባ ወ/ሥላሴ ዘመናቸው በተፈጸመ ጊዜ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ለዘለዓለም በሕያውነት የሚኖሩበትን ቦታ አስጎበኛቸው። እርሳቸውም በሚያዩት ሁኔታ ሁሉ እጅግ በጣም እየተገረሙ ይጠይቃሉ። መልአኩም ለጥያቄያቸው በትዕግሥት ሲመልስላቸው ቆየ። በመጨረሻም ያች የተባለችው ነፍስ ከምትመጣበት ቦታ ወሰዳቸው።

 

በዚያም ዕልፍ አዕላፍ ብርሃናዊያን መላእክት ያችን ነፍስ በትዝብት እየተመለከቱ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ መቆማቸውን አስተዋሉ። በአንፃሩም በባህሪያቸው ጨለማን የተላበሱ ፤ ቁጥራቸው የትዬሌሌ የሆነ እጅግ በጣም የሚያስፈሩ የዲያብሎስ ጭፍሮች እየጨፈሩ ያችን ነፍስ ሲያዋክቧት ተመልክተው፤ አባ ወ/ሥላሴ በጣም አዘኑ። ከነዚያ ጥልማሞት ከወረሳቸው ሠይጣናት መካከል አንዳንዶቹ ይህችን ነፍስ ሊማርከን ለብዙ ዓመታት ያህል ሲታገለን የነበረው መነኩሴ ነፍስ ከዚህ አለ በማለት እያጓሩ ወደ እርሳቸው ለመምጣት ቢፈልጉም መልአኩ አብሮአቸው ነበርና አልቻሉም።

ይሁን እንጂ አባ ወ/ሥላሴ እጅግ በጣም አዝነው ሁሉንም በአንክሮ እየተመለከቱ ሳለ እነዚያ ጥልመት የወረሳቸው አስፈሪ የዲያብሎስ ጭፍሮች ወደ አለቃቸው ወደ ሣጥናኤል በታላቅ ደስታና ጭፈራ አቀረቧት።

 

እስከማእዜኑ የተባለውና በሊቅነቱ ታዋቂ የሆነው ሰይጣን እየኮራና እየተጀነነ ወደ ዲያብሎስ ሄደ። ዲያብሎስም ቁጣው በፊቱ እንደ እሣተ ገሞራ ይነድ ነበር።

“ምን አድርገህ ? ምን ሠርተህ ነው እንዲህ እየተጀነንክ የመጣኸው?” ሲል በከፍታኛ ድምፅ አምባረቀ።

 

እስከማዕዜኑም እጅ ነስቶ ሲያበቃ “ ዲያብሎስ ለዘለዓለም በዙፋንህ ኑርና፤  ከልጅነት እስከ ዕውቀት በሠለጠንኩበትና በተሠማራሁበት በተለይ ጥቂት ተምረናልና አውቀናል በማለት የሚኩራሩትን በማጥመድና እነርሱን ተገን በማድረግ መጀምሪያ እነርሱን፤ በቀጣይም ተከታዮቻቸውን በማሳሳት፤ ትክክለኛውን በማጣመምና እውነት በማስመሰል፤ የተለያዩ ደካማ ጐናቸውን በማጥናት፤ለምሳሌም በዘር፤ በጐሣ፤ በንዋይና በሥልጣን በማማለል ይኸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል የጌታዬን ትዕዛዝና ኃላፊነት ስወጣ ቆይቻለሁ። ይሁን እንጂ ይህችን ነፍስ ከእኛ መዳፍ ፈልቅቆ ለማውጣት የእኛኑ ያህል ለፈጣሪው ሲጸልይና ሲማልድ የነበረ አንድ መነኩሴ አሁንም ለምን ጉዳይ እንደሆነ እንጃ ያው በዕልፍ አዕላፍ መላዕክት ታጅቦ እየተመለከተ ይገኛል።

እስከማዕዜኑ ይህንን ሲናገር የነገደ ጥልመት ሠራዊት በሙሉ ተንጫጫ።

ዲያብሎስም በከፍተኛ ድምፅ “ እኮ ቀጥል “ አለ። በዚህ ጊዜ ሁሉም በአንድነት ጸጥ ረጭ አለ።

“እንግዲህ ጌታዬ በዚህ ውጥረት መካከል እያለሁ ነው ሰውየው፤ ወደ ምርጧ ሀገራችን አሜሪካ የሔደው፤ በዚያም አለቃችን ዲያብሎስ እንደሚያውቀው በርካታ የእኛ ሠራዊት የሚገኙበት በመሆኑ ምንም ጉዳይ እንደማይገጥመን እርግጠኞች ሆነን ተዝናንተን ሳለ፤ ድንገት ከእኛ ቁጥጥር ውጭ በሆነ መልኩ ያልጠበቅነው ጉዳይ ተከሰተ። ይኸውም የዚህን የእኛን ባለሟል የሚያስደነግጥና ቅስም የሚሰብር፤ እንዲያውም እስካሁን ድረስ ሲሠራ የቆየውን ሁሉ እንዲያሰላስልና እንዲጸጸት፤ አልፎ ተርፎም እኛን ከድቶ ወደ ጠላቶቻችን ሠፈር ማኅበረ ቅዱሳን የሚቀላቀልበትን ሁኔታ የሚያመለክት አስደንጋጭ ጉዳይ ተፈጠረ።

በዚህ ሰዓት፤ ሰውዬው የምንፈልገውንና የምንሻውን ሲሠራ የቆየና ጥሩ መሠረትም የተከለልን ስለሆነ ከዚህ ጊዜ በላይ ቢቆይ ያው ፈጣሪ አምላኩ መሐሪ ስለሆነና የዚህ መነኩሴም ጸሎት ተጨምሮ ለንሥሐ ሊበቃ ይችላል በሚል፤  ለልዩ ልዩ ተልዕኮ ተሠማርተው በቦታው ከነበሩ እኔን መሰል ሊቃውንት ሰይጣናት ጋር አስቸኳይ ምክክር በማድረግ ይበቃዋል ስላሉ፤ ለሞት የሚያበቃ ጨረር ከየአቅጣጫው ላክንበት። የተሰጠው የጨረር መጠን በአስቸኳይ ለሞት የሚዳርግ ሲሆን በየትኛውም ሀገር ይሁን ሐኪም ታክሞ ሊድን እንደማይችል በማረጋገጥ ነበር።”

 

“ለመሆኑ ከመጀመሪያው እንዴት ያዝከው? “ በማለት ዲያብሎስ እስከማዕዜኑን ጠየቀው።

“ይህንን ሰው የያዝኩት በወጣትነት ዕድሜው ነበር። ፈሪ ቢሆንም በራሥ መተማመን ነበረውና የአካባቢው ሰዎች ይፈሩት ከነበረው ወንዝ ውስጥ ያለ ወቅቱ ገብቶ ብቻውን ሲዋኝ ያዝኩት። ከዚያም በትምህርቱ እያገዝኩት ቀስ በቀስ ታዋቂ እንዲሆን አደረግሁት። በመጨረሻም ወደ ትግል ብሎ ጫካ ሲግባ የሰዎችን ልብ እንዲደፈን እያደረግሁ፤ ማስተዋል ከእነርሱ እንዲጠፋ በመስለብ፤ እሱን ብቻ ገናና እና ንቁ ሰው እያስመሰልኩ ለከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ አደረግሁት። ከዚያም በእርሱ እማካይነት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ነፍስ እንዲጠፋና የሰዎች ደም እንደ ጎርፍ እንዲፈስ  ሳደርግ ቆየሁ። ለዚህም ተግባራዊነት የተጠቀምኩባቸው ስልቶች፤ አድሎ፤ ዘረኝነት፤ ትዕቢት፤ ሲሆኑ በተለይ ሥልጣንና ፍቅረ ነዋይን ሰፍ ብሎ እንዲሰግድላቸው አደረግሁት። ፈጣሪውንም የለም እስኪል ድረስ እስካድኩት።  በተለይ በዚያች ምድር ፍርድና ፍትሕ እንዳይኖር፤ ሰዎች በሰላም ተዝናንተው እንዳይኖሩ፤ በጭንቀትና በመሸማቀቅ ተሸብበው እንዲሠቃዩ ፤ መፈናቀል፤ ዘረፋና ድብደባ የዘወትር ተግባር እንዲሆን አደረግን።”

 

“ለመሆኑ ይህንን ሁሉ ያደረግኸው በየትኛው የዓለም ክፍል ነው?”

“በኢትዮጵያ ጌታዬ! እጅግ በጣም ከባድ በሆነበት ሀገር፤ ሕዝቡ ከርስቲያኑም እስላሙም ፈጣሪውን ይፈራል ያከብራል። እንግዲህ በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ እንዲህ ያለውን ተግባር ለመፈጸም ቀላል አልነበረም። ሌላው ቀርቶ ቡና ሲያፈሉ ከርስቲያኑ እስላሙን፤ እስላሙም ከርስቲያኑን እየጠራ የሚገባበዝባት ሀገር ነበረች። አሁን ግን በዘርና በኑሮ ውድነት ሰበብ አድርገን ይህን የመሰለውን ሰላም በማጥፋት የጎሪጥ እንዲታያይ አድርገነዋል።” ሲል እስከማዕዜኑ መለሰ።

 

“በኢትዮጵያ! ይህች ሀገር እኮ ለእኛ የመጨረሻ ጠላታችን ለሆነችው፤ አዳምን ለማረከን እናት፤ በእርስትነት የተሰጠችው ሀገር እኰ ናት፤ ታዲያ ይህን ሁሉ የሠራኸው በዚች በተነጠቅናት ሀገር፤ በኢትዮጵያ ነውን?”በማለት ዲያብሎስ እስከማዕዜኑን ጥየቀ።

 

አዎ ጌታዬ! በዚያ ቦታ ለእኛ ጭፍሮች አንዳች ድርጊት ለመፈጸም እጅግ በጣም ከባድ ነበር። ሲል መለሰ።

ከዚያም “በዚህች ነፍስ አማካይነት የእኛ ጭፍሮች የተማሩና የተራቀቁ፤ ያሠማራናቸው ሠይጣናት ሊሠሩና ሊያደርጉ ያልቻሉትን ስትፈጽም መቆየቷን ባረጋገጥክልኝ መሠረት ከእኔ በታች የጠቅላይ ሚኒስተርነት ቦታ ይገባታል” አለ ዲያብሎስ እየተቁነጠነጠ።

“ይህች ነፍስ እኰ፤ በዓለም በነበርችበትም ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ነበረች” አለ እስከማዕዜኑ የተባለው ዋነኛው አሳቹ ሠይጣን።

እኔም በዚህ በሲዖል ይህንኑ ማዕረግ አጽድቄዋለሁ! አለ ዲያብሎስ።

በዙሪያው ከበው የነበሩ ምሁራን ሠይጣናት ሁሉ በአንድ ደምፅ “ይገባዋል!  ከእኛ በላይ ተንኰለኛ ስለነበር ይገባዋል! የዲያብሎስ ፍርድ ፍርዳችን ነው!” በማለት ጭብጨባና ሁካታ አሰሙ።

 

“ሌላስ የምትለው አለህ?” በማለት ዲያብሎስ ሪፖርት አቅራቢውን እስከማዕዜኑን ጠየቀ።

“አዎ ጌታዬ! አዳምን የማረከን ጠላታችን በምድር በነበረበት ጊዜ ለደቀመዛሙርቱ በምድር ያሰራችሁት በስማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድር የፈታችሁት በሰማይ የፈተፈታ ይሆናል የሚል ቃልኪዳን እንደሰጣቸው ይታወቃል። ታዲያ ለዚች ነፍስ ልዩ ፍትሃት ለማድረግ ወደኋላ የማይል የእምነቱ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ፓትርያርክ የእርሱ የቅርብ ሰው ስለነበር፤ ይህንኑ ፍትሃት እንዳይፈጽም በማሰብ አስቀድመን የዚህን ሰው ነፍስም በድንገትኛነት እንድትቀሠፍ አድረገናል። በዚህ ሰው ነፍስ ምክንያት በአለፈው ወቅት በእኛና በመላዕክት ዘንድ ከፍተኛ ከርክር ተደርጎ እኛ የረታንበትና  ነፍሲቱ በመካከላችን የምትገኝ መሆኑ ይታወሳል” ሲል ተናገረ።

የአባ ወ/ሥላሴን ነፍስ ይዞ የሄደውም መልአክ “ይኸው እንዳየኸው ነው። ሰዓታችን ደርሷልና እመልስሃለሁ” አለ።

አባ ወ/ሥላሴም ልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው! እኔ ምንም የማልረባ ኢምንት ሰው ስሆን አክብሮኛልና ስሙ ለዘለዓለም የተመሰገነ ይሁን። እናንተም አምላካችንን እንድታገለግሉ የተመረጥጣችሁ መላዕክት እንዲሁ የተመሰገናችሁ ናችሁ! እያሉ ሲጸልዩ መልአኩ ነፍሳቸውን ወደ ሥጋቸው አዋህዶአት ወደ ሰማይ ዐረገ።

አባ ወ/ሥላሴም ዓይናቸውን ገለጥ ሲያደርጉ አባ ከሰተ ብርሃን ጸሎት እያደረሱ መሆኑን አስተዋሉ። ጉሮሮአቸውን እንደማጽዳት አድርገው፤ አንደምን ዋሉ አባ ከሰተ ብርሃን? አሉ በደከመ ድምፅ።

እግዚአብሔር ይመስገን! ይባርኩኝ አባቴ!

“ከመጡ ቆይተዋል?”

“አዎ! ምን ተፈጠረ? እኔማ የእርስዎን ሁኔታ ሳላይ አልሄድም ብዬ ነው አስካሁን ድረስ የቆየሁት” አሉ አባ ከሰተ ብርሃን በአርምሞ።

“የአምላካችን ሥራ ዕፁብ ድንቅ ነው! የነገሩትን የማይረሳ፤ የለመኑትን የማይነሳ አምላክ ባለፈው ያጫወትኩዎትን ፤ለብዙ ዓመታት የተጋደልኩላትን ነፍስ መጨረሻዋን ሊያሳየኝ ፈቃዱ በመሆኑ ነበር ያላገኙኝ” አሉ አባ ወ/ሥላሴ።

አባ ከሰተ ብርሃንም ለቸርነቱ ወሰን የሌለውን የአምላካችንን ተዓምር እስኪ ከመጀመሪያው ጀምረው ይተርኩልኝ በማልለት ለመኗቸው። በዚህም  መሠረት ይህንኑ በዝርዝር ነገሯቸው።

ተፈጸመ

እግዚአብሔር አምላክ አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

 

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on May 29, 2013
  • By:
  • Last Modified: May 29, 2013 @ 8:42 pm
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar