www.maledatimes.com ኢትዮጵያ እየወጣች ወይስ እየሰጠመች? - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

ኢትዮጵያ እየወጣች ወይስ እየሰጠመች?

By   /   July 28, 2012  /   Comments Off on ኢትዮጵያ እየወጣች ወይስ እየሰጠመች?

    Print       Email
0 0
Read Time:17 Minute, 5 Second

የቄስ በሊና ሳርካ “የከፍታ ዘመን ለኢትዮጵያ” ራዕየ መጽሐፍ ከወቅቱ ሁኔታ አንጻር ሲፈተሽ

ኢኮኖሚ ተንታኞች በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን መሠረተ ልማት በመጥቀስ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ11 ፐርሰንት እንዳደገና ቻይናን ተከትሎም በዓለም ሶስተኛ ፈጣን አዳጊ አገር እንደሆነች ሌተቀን እየለፈፉ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ መኖር ያቃተው የሕብረተሰብሰ ክፍል፣ የኢኮኖሚ ተንታኞች የሚያቀርቡት ዘገባ፣ “ጉንጭ አልፋ ነገር ነው፣ ምክንያቱም ዕድገት ማለት በመጀመርያ በቅጡ ስንበላና በገንዘባችን የወደድነውን ነገር ስናደርግ ነው ይላል፡፡ ሰው ተርቦ እድገት፣ ሰው በስራ እጦት እየተንከራተተ ዕድገት፣ ሰው ቀዬውን ጥሎ እየተሰደደ ዕድገት ይባላል ወይ?” ይላል፡፡
በቅርቡ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ ዝናብ ልጠለል አንድ ካፌ ገብቼ ያጋጠመኝ ወጣት ለዚህ ዋቢ ምሥክር ነው፡፡ ከወጣቱጋ በአጋጣሚ ጠረጴዛውን ተጋርቼ ስለነበረ፣ ሕይወቱን ቆርሶ አካፍሎኛል፡፡ የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ምሩቅና የመንግሥት ሠራተኛ የሆነው ይህ ወጣት፣ ደሞዙ ሁለት ሺ ብር ነው፤ ነገር ግን “ይርበኛል” ነው ያለኝ በሙሉ አፉ፡፡ “እንኳንስ የፈለኩትን ምግብ አማርጬ ልበላ ይቅርና፣ እንዲያውም ይርበኛል፡፡ በደሞዜ ከወር ወር መድረስ አቅቶኛል፣ ከደሞዜ ላይ የጡረታና የዓባይ ከአንድ ሺ ብራ ያላነሰ ይቆረጥብኛል፤ በዚያ ላይ የቤት ኪራይ ላንዲት ደሳሳ ክፍል፣ ስምንት መቶ ብር ከፍዬ ቀሪዋን ብር እንዴት ብዬ ነው ለትራንስፖርት፣ ለምግብ፣ ለንጽህና መጣበቂያና ለመሳሰሉት የማውለው?” ይላል እንባ ባጋቱት ዓይኖቹ እያየኝና ከንፈሩን እየነከሰ፡፡ በወቅቱ የወጣቱ ስሜት ተጋብቶብኝ ሰውነቴን ከላይ እስከታች ወሮኛል፣ እውነት ነው ማንም ሊክደው የማይችለው ሀቅ፡፡ በዚህ ሰዓት በአዲስአበባ ውስጥ እየኖረ ያለው ፊት ለፊት የሚሮጠው ሠራተኛ ሳይሆን በአቋራጭ የሚሮጠው ነው፡፡ ነጋዴው ነው፡፡ ሞሳኙ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢው ነው፡፡ ኦ! ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የሚያስጠላበት ሁነኛ ጊዜ ቢኖር ይህ ጊዜ ነው፡፡
በደርግ ሥርዓተ መንግሥት ወጣቱ ብሔራዊ ውትድርናና ጦርነትን ሽሽት ተሠደደ፡፡ አሁን ደግሞ ርሃብን ሽሽት፡፡ ሁኔታው የሚያስፈራና ተስፋ የሌለው ዓይነት ቢመስልም እንደ መንግሥትና የኃይማኖት መሪዎች፣ በተለይም የክርስትና ፣ ከፊታችን ትልቅ ተስፋ አለ እየተባለ ነው፡፡ ችግሩ እንዳለ ሆኖ መንግሥት ባሁኑ ሰዓት ሰፊ መሠረተ ልማት ባገሪቱ እያስፋፋ ነው፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ስራዎች ወጣቶችንና ሥራ ፈቶችን ለማሰማራት እየሞከረ ነው፡፡ ነገር ግን ሁኔታው በመንግሥት ብቻ የሚዘለቅ ነው ወይ? አነጋጋሪ ነው፡፡ ብዙዎቻችን የቤት ሥራችንን በመንግሥት ጫንቃ ላይ ብቻ ስለጣልን፣ የመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ መንግሥት እንዲመልሰው እየጠበቅን ነው፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ጥላቸው ከራሳቸው አልፎ የተረፈ ግዙፍ ዋርካዎች ብዙ ናቸው፡፡ ባለሐብቶች ከመንግሥትጋ እጅና ጓንት በመሆን ለተደቀነው ድኅነትና ችግር ትልቅ ሚና መጫወት የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ ሁልግዜ የበለጸጉ አገራትን እርዳታ መጠበቁ አያዋጣም፡፡ ደግሞም የበለጸጉ አገራት የሚባሉቱ እነርሱ የሚፈልጉትን አዠንዳ ካላስፈጸምን የእርዳታ እጃቸውን እየሰበሰቡብን የሚገኙ ናቸው፡፡ ለአብነት በአሁኑ ሰዓት አገራችን እንድትቀበልና ተግባራዊ እንድታደርገው ከሚጫኗት አዠንዳዎቻቸው አንዱ ግብረሰዶምና ግብረሰዶማዊነት በአገሪቱ ተንሰራፍቶ ሕጋዊ ሆኖ እንዲቀጥል ነው፡፡ ወጣም ወረደ አገሪቱ በዚሁ ከቀጠለች ምናልባት ለሚመጣው ትውልድ ከምጣድ ላይ የወረደ ትኩስ እንጀራ ታዘጋጅለታለች፡፡ ዕድለኛ ትውልድ፡፡ የኔ ትውልድ ግን እንደ ሻማ ሆኖ ማለፉ አይቀሬ ነው፡፡ ቢሆንም የተረገመ ትውልድ ሆኖ ሳይሆን ያለፈው ትውልድ አያሌ ያልተሠሩ የቤት ሥራዎችና ዕዳዎችን ሳይሰራና ሳይከፍል ኖሮ ስላለፈ ነው፡፡ ስለዚህ የኔ ትውልድ ባንድ እጁ ሁለት ሥራዎችን እየሰራ የሚገኝ ትውልድ ነው ማለት ነው፤ አንድም ለራሱ ትውልድ  ያኛው ትውልድ ያልሰራውን ሥራና ዕዳ ሲሰራና ሲከፍል፣ ደግሞም በመንገድ ላይ ላለው ትውልድ እንጀራ ሲያሰፋ፡፡
የከፍታ ዘመን ለኢትዮጵያ
የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ አንድ መጽሐፍ አግኝቼ ሳነብ፣ ብዙም ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር፡፡ በቄስ በሊና ሳርካ ራዕይ ተመስርቶ የተጻፈውና “የከፍታ ዘመን ለኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ የተሰጠው፡፡ ለዛሬ ብዕሬን የመዘዝኩት መጽሐፉ ላይ የተጻፉትንና ራዕዮችና እየሆኑና እየተሰሙ ያሉትን ነገሮች አንድ መሆን አለመሆናቸውን በጨረፍታ ለማየት ነው፡፡ በጥልቀት ማወቅ የፈለገ ግን መጽሐፉን አግኝቶ ቢያነበው የበለጠ ግንዛቤ ሊያገኝ ይችላል፡፡
እንደ ቄስ በሊና ሳርካ ራዕይ
ቄስ በሊና በጾምና ጸሎት በአምላካቸው ፊት ባሉበት ሰዓት ነው የወደፊቷ ኢትዮጵያ ፍንትው ብላ በራዕይ የተገለጸልቻቸው እንደመጽሐፉ፡፡ ባጭር ቃል ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ ያድግና፣ ታሪኳ ተለውጦ የምትታወቅበትን ረኃብና ችግር እንደ ማቅ ከላይዋ ላይ አውልቃ ትጥላለች፡፡ በአገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ከምስራቁ አካባቢ ነዳጅ፣ ከሰሜኑ ማዕድናት፣ ከደቡብ ደግሞ ፍራፍሬና አትክልት ብሎም የቁም ከብት በብዛት እንደሚገኝ መጽሐፋቸው ይናገራል፡፡ በምሥራቅ የአገሪቱ አካባቢ እያንዳንዱ ገበሬ የነዳጅ ጉድጓድ ባለቤት ይሆናል ይላሉ፡፡
በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስራ መንፈስ ይገባና ሁሉም ለሥራ ታጥቆ ይነሳል፡፡ አዲስ አበባ ጽዱና ያማረች ለምለም ትሆናለች፡፡ ሕንጻዎቿም ሳይታሰብ ወደ ሰማይ ይመጥቃሉ፣ መንገዶቿም ያማሩና ንጹህ ይሆናሉ፡፡ ሁሉም ሲፈጸምም ጃፓን በ1994 ዓ.ም. እንደፈረንጆች አቆጣጠር የነበራትን ይዘት አዲስ አበባችን ትይዛለች፡፡ ያኔም አፍ ተሞልቶ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካ ርዕሰ መዲና ልትባል ትበቃለች ይላሉ በራዕየ መጽሐፋቸው፡፡
ቱሪስቶች ከወትሮው በተለየ መልኩ ወደኢትዮጵያ መጉረፍ ይጀምራሉ፡፡ አየር ንብረቷንና መልክዓ ምድሯን፣ ሕዝቦቿንና ባሕሏን ወደውም በወራት ለሚቆጠሩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር ይገደዳሉ፡፡ ከኢትዮጵያውያንም ይጋባሉ ደግሞም ይዋለዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር የነበራት የጦርነት ቁርሾ ይሻርና በአካባቢው ሰላም ይሰፍናል፡፡
ይህ ነገር እስከሚሆን ግን አገሪቱ በጸና ችግር ውስጥ ማለፍ ግድ ይሆንባታል፡፡ ሥር የሰደደ የጨለማ ጊዜያት፡፡ ይህ ችግር ምን ያህል ጊዜ ይቆያል ከተባለም ከአሥር ዓመት አይበልጥም፡፡
የቄሱ ራዕይ ከወቅቱ ያገሪቱ ሁኔታጋ ይዛመዳል ወይ
አሁን እየታየ ካለው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር ራዕዩ ከመቶ አብዛኛው እጁ እየተፈጸመ ነው፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች የምናያቸው የልማት ሥራዎች፣ አዲስ አበባ ላይ እየተሰሩ ያሉት ሕንጻዎችና መንገዶች፣  ከልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተገኙ ያሉት ማዕድናት፣ በምሥራቁ የአገሪቱ አካባቢ የሚታሰሰውና የሚቆፈረው ነዳጅ የራዕዩን እውነታነት ያረጋግጣሉ፡፡
ሕዝቡም በጸና ችግር ውስጥ እያለፈ ነው፡፡ በልቶ በሚያድረውና በማያድረው መካከል የገደል ያህል የሰፋ ልዩነት እያየን ነው፡፡ ለማኙ በዛ፡፡ ድሮ ድሮ አይነሥውራንና አካል ጉዳተኞች ነበሩ ሲለምኑ የሚታዩት፣ አሁን ግን ጤነኞች ሰዎች አንዳንዶቹ በነጠላና ኩታ ማንነታቸውን ደብቀው፣ ሌሎቹ የመጣው ይምጣ ብለው ስለምንተማርያም ሲሉ እየተስተዋሉ ነው፡፡ በተለይ አረጋዊያን እናቶችና አባቶች፡፡
ኢትዮጵያ በሞት ሽረት ላይ ያለች ትመስላለች፡፡ ሁኔታው በጣም የከፋ ነው፡፡ የሸቀጥ፣ የትራንስፖርት፣ የልብስና የቤት ኪራዩ መናር የከፋ ጉዳት ላይኖረው ይችላል፣ የምግብ መናር ግን ከሁሉም ያስፈራል፡፡
ቄስ በሊና በመጽሐፋቸው ጽኑ ጨለማ ያሉት ይሄ ነው፡፡
ሰው ለሰው መተዛዘን የጠፋበት ጊዜ ነው በኢትዮጵያ፡፡ ድሮ ድሮ አንድ ሰው መንገድ ወድቆ ቢታይ ጠጋ ብለው “ምን ሆነክ ወንድሜ፣ ምንሆንሽ እህቴ” ይባል ነበር፣ አሁን ግን ይኼ የለም፣ ለምን አይንፈራፈርም፣ ዝም ብሎ ማለፍ ሆኗል፡፡
ይሁንና በአንጻሩ ሕዝባችን ሊመሰገን ይገባዋል እላለሁ፡፡ እንዲህም እስከ ጥግ ተቸግሮ ወደ ዝርፊያ ወንጀል አልተሰማራም፡፡  ቢሆንም ብዙዎች እየተራብን ጥቂቶች በራችንን ከርችመን ቁንጣን እየወጠረን ነውና መታሰብ አለበት፡፡ ለሚያልፍ ቀን፣ የማያልፍ ታሪክ መጻፍ ተገቢ አይደለም፡፡
እናንተስ አንባቢዎቼ ምን አላችሁ?
የግርጌ ማስታወሻ
የከፍታ ዘመን ለኢትዮጵያ፣ በቄስ በሊና ሳርካ www.kiduskal.com
Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar