www.maledatimes.com የአሲምባ ፍቅር ደራሲ- ካህሳይ አብርሀ (አማኑኤል) ትችት-(ሐተታ)- ሽፈራው ክፍል ሁለት - MALEDA TIMES
Loading...
You are here:  Home  >  Ethiopia  >  Current Article

የአሲምባ ፍቅር ደራሲ- ካህሳይ አብርሀ (አማኑኤል) ትችት-(ሐተታ)- ሽፈራው ክፍል ሁለት

By   /   October 24, 2013  /   Comments Off on የአሲምባ ፍቅር ደራሲ- ካህሳይ አብርሀ (አማኑኤል) ትችት-(ሐተታ)- ሽፈራው ክፍል ሁለት

    Print       Email
0 0
Read Time:50 Minute, 45 Second

አንባቢ ሆይ : በክፍል አንድ ባጭሩ አንደገለፀሁት ጓድ “አማኑኤል” ጋር በሕብረ ብሔራዊዉ የኢትዮጵያ 
ህዝባዊዉ አቢዮታዊዉ ሠራዊት (ኢሕአሠ) በወሎ፣ በቤጌምድር እና በትግራይ በብዙ ፈተናና ችግር አብረን
ተካፍለናል። ከ30 አመት በኋላም ተገናኝተን ስለ ኢሕአሠ መጽሃፍ ለመጻፍ እንዳሰበ ሲነግረኝ እንደምረዳዉ
ቃሌን ሰጥቸ በሰፊው አስተዋጽዖ አድርጌአለሁ ።መጽሐፉ እስኪወጣ ብዙ ጓጉቻለሁ ጠብቄአለሁ።
እንደወጣም በተቻለኝ አቅም በብዙ መንገድ ለአንባቢያን እንዲደርስ አድርጌአለሁ። በፌስ ቡኩ(Face
book) እና በጉግል(Google) እውነተኛ ታሪክ ሁሉም ሊያነበው የሚገባ በማለት አስተዋውቄአለሁ።
ይህን ሁሉ ሳደርግ ግን መጽሃፉን አንብቤ ሳይሆን ታሪኩ አማኑኤል ጋር በስልክ ለብዙ ጊዜ ያወራነዉን ነዉ
ከማለት ግምት በመነሳት ነው። ሌላው ቀርቶ መጽሐፉ ከመታተሙ በፊት አማኑኤል ተመልከተው ብሎ
ባለመስጠቱ እንኳን ጥርጣሬም አላደረብኝም። በአጠቃላይ በመጽሀፉ መውጣት የተደሰትኩ መሆኔን ስገልጽ፤
በታሪኩ ዉስጥ ሆን ብሎ ወይም ታሪኩን ለአንባብያን ለማጣፈጥ የተጻፉትን አንዳንድ ብረዛና የፈጠራ
ተረቶች ስመለከት “የአሲምባ ፍቅር” በበረሃና በከተማ፤ተንገላተዉ መስዋትነት ለከፈሉት መታሰቢያ
መሆኑ ቀርቶ ፤ ሌላም ተልእኮ ያለው ሆኖ ነው ያገኘሁት ። በኢሕአሠ ውስጥ በነበረበት ጊዜ በትግሉ
የነበረውን መማረር ለትግላችን እንቅፋት ለሆነው ለዘር ክፍፍል ችግር ማወደሻና መኩሪያ መሆኑ በጣም
አሳዝኖኛል። ኢህአፓ እና ኢሕአሠ ውስጥ በነበሩበት ወቅት የትግሉ መራራነት ከሚችሉት አቅም በላይ
ሆኖባቸው ድርጅቱን በመክዳት፤ንብረቱን ይዘው ከኮበለሉ በኋላ በድርጅቱ ላይ ወቀሳ፤ዘለፋ የሚያቀርቡትን
በጣም አጥብቄ እቃወማቸዋለሁ። የኢሕአፓ/ኢሕአሠ ታሪክ በኢትዮጵያዊነታቸዉ ሳያወላዱ ከተለያዩ
ህብረ-ብሄር በኢትዮጵያዊነታቸው ብቻ ተሰባስበው በመካከላቸው መጠራጠር ሳይኖር ውድ ህይዎታቸውን
ለመላዉ ሕዝብ እኩልነት አሳልፈው የሰጡ ትዉልድ ታሪክ ነዉ። የራሳቸውን ድክመት ለመሸፈን ከጠላት
ጋር በማበር ኢህአፓ/ኢሕአሠን ሲዘልፉና ሲያንቋሽሹ ስሰማ ወይም የጻፉትን ሳነብ ፤ በከተማዉ፤ በሸለቆዉ፤
በወንዙ ዳር፤ በበረሀዉ ፤በአሸዋዉና በድንጋዩ ስር የወደቁትን ጓዶች ታሪክ ማናናቅ በመሆኑ ያናድደኛል።
“የአሲምባ ፍቅርም “ በአንድ አካሉ ሌሎችን ለማስደሰት በኢሕአፓ/ኢሕአሠ አሰራር ላይ የሰነዘረው በጣም
አሳዝኖኛል። ይህንንም ስል ስህተቶች አልነበሩም ለማለት አይደለም። የአማኑኤልን ” የአሲምባ
ፍቅር”መጽሀፍ በሚመለከት የኔን የግሌን ትችት በስምንት ነጥቦች በማተኮር አቀርባለሁ።
1ኛ- የወሎ ኦፕሬሽን፤-
የወሎ ኦፕሬሽን በኢህአሠ የትግል ታሪክ ትልቅ ስፍራ የያዘ ነው። ለምን ቢባል መልሱ የኢህአፓ ዓባላት
ለትግሉ ያላቸውን ፍቅር በቆራጥነት ውድ ሕይዎታቸውን መስዋት በመክፈል በተግባር የተረጎሙበት በመሆኑ
ነው። የኢህአፓ ሰራዊት በጊዜው ከነበረው ከግማሽ በላይ በጠላት እጅ ወድቆ በሰራዊቱ ላይ ትልቅ ጉዳት
ደርሶበት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። አበው እንደሚሉት “ሰው ያለ ቀኑ አይሞትም” ሆነና ከወሎ
ከዘመተው መካከል በተአምር ወይም በእድለኝነት በህይወት ተርፈን፤ ከአርሶ አደሩ ምርኮኝነት ወጥተን
በተለያየ መከራና ጥረት በቡድንና በግል ወደ አሲምባ ተጉዘን ኢህአሠን የተቀላቀልነዉ ጓዶች (መገርሳ ፣
ፍሱሕ ገብራይ ፤ ነጻነት ማንጁስ ፣ ጀማል ፣ እቁባይ ፣ ገብረመስቀል፣ ወርቁ፣ አማኑኤል(ደራሲዉ)እና እኔ 2

(ሽፈራዉ) ነበርን። ስለወሎ ኦፕሬሽን አማኑኤልና እኔ ቀደም ብሎ በታተመ መጽሐፍ አጠቃላይ የዐይን
ምስክር ቃል ብንሰጥም(ኢሕአሠ ፀሐፊ አስማማው ወይንም አያ ቫረው ገጽ 89-100) አሁን በህይዎት
የቀረነዉ ከ5 በላይ ያልሆን ጓዶች ራሱን የቻለ የግል ታሪክ ስላለን ሀቁን ለወደፊት ትዉልድ በጽሁፍ
የማስቀመጥ ሃላፊነት እንዳለብን እገነዘባለሁ ። ይህ አማኑኤል በወቅቱ የከፈለዉን መከራና ስቃይ ለማሳነስ
ሳይሆን ፣በአገር ዉስጥም ይሁን በስደት ተበታትኖ የሚኖረዉ “ያትዉልድ” ቢችል በራሱ ፤ ካልሆነም
እዉነትን ለጥቅም ሳይለውጡ፤ ሀቅን ሳይበርዙ ለትዉልድ ለማቅረብ ከሚሹ ደራሲያንና መጽሐፍ
አቀነባባሪዎች ጋር በመተባበር የሚጻፍ ማስታወሻዎች እንዲቀርቡ ማድረግ ለታሪክ ይጠቅማል ብየ
ስለማምን የቀረነው እንድናስብበት እግር መንገዴን አሳስባለሁ። አማኑኤል ”አሲምባ ፍቅር” ስለወሎዉ
ኦፐሬሽን አብዛኛዉን ዋና ዋና ሁኔታወች በትክክል ቢአቀርባቸዉም ፣ያ የሰኔ 27, 1968 በወሎ ጉራ ወርቄ
በተባለዉ ቦታ ፤ አንተ ለኔ እኔ ለአንተ እያሉ ጉዶች መከራና ፍዳን የከፈሉበት ፤ ንጹህ ደም የፈሰሰበትና
ህይዎት የጠፋበት ነዉና አንዳንድ ቅንባሬወችን ለማረም እሞክራለሁ።
ሀ፤- በጉራ ወርቄ በተደረገው የመጨረሻ ፍልሚያ፤አማኑኤል,(አሲምባ ፍቅር ገጽ 127)አሊጋዝ ሲሞት እንዳየ
እና አንደነበረ ገልጿል፤ የአሊጋዝ አሟሟት ግን በመጽሃፉ እንደቀረበዉ እንዳልነበር ጓድ አማኑኤል
ይዘነጋዋል ብየ አልጠራጠርም። ሰኔ 26 ቃሊም ላይ ከደርግ ሰራዊትና አርሶ አደሮች ተከበን ሙሉ ቀን
ባደረግነዉ ጦርነት ተዳክመን፤አብዛኛዉ ጥይት ስለጨረሰ አማራጩ ማፈግፈግ በመሆኑ ወደ አፋር በረሃ
ለመጓዝ የአስመራን መንገድ አቋርጠን ዞብል ገባን። ፤ብዙ ድካምና ረሃብ ስለነበረ አንድ መንደር አደረን ፤
በጧት ወደ ምስራቅ ወሎ ጉዞ ስንጀምር የጥሪ ጡርምባ ሰማን፣የአርሶ አደሩ ጦር(ሚሊሺያ) ከኃላ ሲከተሉን
አየን፤አኛም ጥሩ ወታደራዊ ቦታ ለመያዝ በፍጥነት መንቀሳቀስ ጀመርን። በወቅቱ ሰራዊቱ በሦስት ተከፍሎ
ነበር፤ አሊጋዝ እኔ የነበርኩት ቡድን ዉስጥ ነበር ። አማኑኤል ግን ከእኛ ጋር አልነበረም። አርሶ አደሮቹን
የሶሪያ ጦር፤የአረብ ጦር፤መጣብህ አያሉ ሲያስተባብሩት ሰምተን ከአርሶ አደሩ ጋር በተለይ ከሽማግሌዎች
ጋር ለመደራደር ተስማምተን እኛ ከነበርንበት ጋንታ ውስጥ ሦስታችን የወሎ ልጆች (አሊጋዝ፣ወርቁና
እኔ)ወደ አንዲት ኮረብታ ላይ አመራን።በዚህ ጊዜ ጃንሆይ (ጀማል)መማረኩንና በአርሶ አደሮቹ እጅ
መውደቁን ሰማን፤ ከአራት የአርሶ አደር ሽማግሌዎች ጋር ለውይይት ቁጭ አልን።በአቅሪአባችን ግን ተኩሱ
ተፋፍሟል ። እኛ የናንተው ልጆች ነን፣ እገሌን እናውቀዋለን እገሌ ጋር ዝምድና አለን፤በማለት አንዳንድ
የታወቁ የወሎ ሰዎችን ስም መወርወር ጀመርን። እነርሱም በጣም ተገርመው እያዳመጡን እየተወያየን
እንዳለን ጠመንጃ የያዙ ሦስት አርሶ አደሮች በድንገት መጥተዉ ተኩስ ከፈቱብን።አሊጋዝ ተመታ የእርሱን
ብረት ለመንጠቅ የቀረበው አርሶ አደር ጋር ተናንቀው መሬት ላይ ይንከባለሉ ጀመር። እኔና ወርቁ ተኩስ
ከፍተን ሁለት አርሶ አደሮች ተመተው ወደቁ።ወርቁም እግሩ ላይ ተመታ ፣ አሊጋዝ ወዲያው ህይወቱ
አለፈች ፣ አርሶ አደሮቹ ጠመንጃዉን ዘርፈዉ ተበታትነው ከኛ አካባቢ ለጊዜዉ ጠፉ ።
የወርቁ መመታት በጣም አሳሰቦን ደሙን ለማቆም ወደ አንድ ሸለቆ ውስጥ ገባን።በዚህ ጊዜ ተከበናል፤ወርቁ
የተመታውን እግሩን በኩሽክ(ከምንታጠቀው አቡጀዲ ቁራጭ በመቅደድ) ደሙን ለማቆም አሰርነው።
በአካባቢዉ ተኩስ ቁሟል፤ አብዛኛወቹ ጓዶች መያዛቸዉን በመግለጽ እጅ ስጡ እያሉ የከበቡን አርሶ አደሮች
ይለፈልፋሉ፤ እኔና ወርቁ ብቻ እንደቀረን ያስታውቃል። እኛም እጅ ሰጥተን የደርግ መጫወቻ ከምንሆን
እራሳችንን እንግደል ብለን ወሰን።የወርቁ ክላሽን ኮፍ በጥይት ተመቶ ስለነበር አልከፈትም አለን።
ለማንኛውም ለሁለታችን በቂ ጥይት እንዳለ ለማረጋገጥ ጠመንጃየን ስከፍተው የቀረኝ አንድ ጥይት ብቻ 3

ነበር። አንተን ገድየ እኔ በምን ልሞት ነው በማለት ወርቁን ጥያቄ አቀረብኩለት፤ ሌላ አማራጭ እንደሌለ
በማወቅ በል እጃችን እንስጥ ተባብለን ተስማማንተ እጅ ሰጠን። አማኑኤል (አሲምባ ፍቅር በገጽ 127 እና
142) አሊጋዝ ሲሞት አየሁ የሚለው የመጽሀፉ አቀነባባሪዎች በስህተት ወይም ለቅመም የጨመሩት
ካልሆነ በስተቀር የ”አሲንባ ፍቅር”ን ላነበበና የጓድ አማኑኤልን የማስታወስ አእምሮ ችሎታ ላደነቅነዉ
በወቅቱ በነበረዉ ሁኔታ አንድ ጓድ ሁለት ቦታ ሊሆን እንደማይችል ያዉቃልና፣ የታሪኩን ስህተት ማረም
ይገባል ።
ለ፤- ኢህአፓ የወሎውን ዘመቻ ውድቀት ደብቆ ከስህተቱ ለመማር ወይም ሀላፊነት ለመውሰድ
አልፈለገም(አሲንባ ፍቅር ገጽ 169)። ይህ ኢህአፓን ለመወንጀል ታስቦ በመጽሃፉ አዘጋጂወች የተወረወረ
ካልሆነ በስተቀር ፣ ጒድ አማኑኤል ያምንበታል ብየ የማልቀበለዉ ስህተት ነዉ። ከአርሶ አደሮቹ እጅ
ወጥተን ወልድያ ከተማ በአንድ የድርጅት አባል ቤት ወርቁ ህክምና በሚያገኝበት ጊዜ ተገናኝተን የወሎ
የፓርቲው አመራር እኛን አነጋግሮን ስለ ኦፕሬሽኑ አጠቃላይ ድክመት፤ያለመሳካቱን ዋና ዋና ምክንያቶች
አስመልክቶ ሀሳባችንን አቅርበናል።፣ የሰጠነዉ አስራ አራት ገጽ የሚሆን ዝርዝር ዘገባም የኢህአፓ
የመጀመሪያ ኮንግረስ ላይ እንደቀረበና እንደተወያዩበት ከነበሩት (በደብተራው) ተገልጾልናል። የወሎዉን
እንቅስቃሴና አጠቃላይ ጉዳትና ድክመት በፓርቲዉ አራተኛዉ ፐሌኔም የተጻፈዉን የትግል የግምገማ ሪፖርት
አላየዉም??
ጓድ አማኑኤል አሲምባ እንደተመለስንም እኔና ወርቁ ከከተማ አዲስ ለሚመጡት በሰንገደ ማሰልጠኛ ጣቢያ
ለሚሰለጥኑ ጓዶች በአጠቃላይ የወሎን ኦፕሬሽን ጥንካሬ፤ውድቀት፤እያነሳን እንድንወያይ አመራሩ አድርጎ
እንደነበረ ያዉቃል። እኔና ወርቁም እኛ የመሰለንን ስህተቶች በመጠቆም ለወደቀቱና ለተሰዉት ጓዶች
አመራሩ ተጠያቂ እንደሆነ በመግለጽ ያለምንም ተጽእኖ መናገር መወያየት ችለናል።
2ኛ፤- ስለ ውቅሮ ኦፕሬሽን።
የውቅሮ ኦፕሬሽን ወጣቱ(ማንጁስ) አማኑኤል “በአሲምባ ፍቅር” እራሱን ለአንባብያን እንዳቀረበው ፍጹም
የተጋነነ የግል ጀብዱነት ሚና ሳነብ በመገረም ብቻ ሳይሆን ፤ ፀሃፊዉ ወይም የታሪኩ አቀነባባሪዎቹ ያደረጉት
ሀቁን የሳተ ብረዛ አሳዝኖኛል ። ከከተማ የወጣው ጥናት የኛን መምጣት ጠላት አውቆ ተጠናክሮ
እንደሚጠብቀን እያወቅን ሚስጥር ነው ስለተባለ ሳንናገር ዝም ብለን ገባን የሚለን(የአሲምባ ፍቅር ገጽ
338)ፍጹም ሀሰት እውነት ከሆነም እሱም እያወቀ ዝም ብሎ መግባቱ በጣም አጠያያቂ ነው። በዉቅሮዉ
ጦርነት ፤ ራሳቸዉን ከጓዶች አስቀድመዉ ከጠላት መሀል ገብተዉ በጨበጣ ዉጊያ አያሌ የሀይልና የጋንታ
መሪዎች በአርአያነት ህይወታቸዉን አስቀድመዉ የሰጡበት፤ የብዙ ህብረ-ብሄረሰብ ጀግና ጓዶች ህይወት
የተከፈለበት ዋናዉ ምክንያት ጓድ አማኑኤል እንደሚወነጅለው አደጋዉ ታዉቆ “ሚስጥር” ስለተሸሸገ
ሳይሆን ፣ለኦፐሬሽኑ የተደረገዉ ጥናት የተምታታና ትክክለኛ አለመሆኑን ጓዶች የተገነዘቡት ግንቡን ጥሰዉ
ከጠላት ጋር ሲቀላቀሉ ነበር።
በውቅሮ ኦፕሬሽን ከባድ መሳሪያ (RPG)ለመተኮስ ከተመደቡት አንዱ እኔ ነበርኩ፣በምድቤም በህብስቱ
ከሚመራው አጥቂ ምድብ ነበርኩ። አማኑኤል ከየት እንዳመጣው እንጃ (የአሲምባ ፍቅር ገጽ 343) ሁለት
ባዙቃ ብቻ እንዲተኮስ ነው የተፈቀደላቸው ብሏል። እኛ ግን አራት እንደተኮስን አስታውሳለሁ።4

የመጀመሪያው ባዙቃ ካምፑ ላይ ወደቀ። ። ሁለተኛው የዘቡን ግንብ አፍርሶት ስለነበረ ሦስትና አራት
አከታትለን ተኮስን። ተኩሱም የተከፈተው በከባድ መሳሪያ ነበር፣ በኃላ በህብስቱና በወርቁ ትእዛዝ ከባድ
መሳሪያ አቁሙ እኛ ልንገባ ነው ተብሎ መተኮሱን አቁመናል። አማኑኤል ከኛ ጋር አልነበረም። አማኑኤል
ተከለልኩበት የሚለው ቤት በቦታዉ ያልነበረ፣ በሳት ተቃጠለ የሚለው መከላከያ በአእምሮ የተፈጠረ ሲሆን፥
በዛ የተኩስ ማእበል የጠይት ሩምታ ውስጥ ጓዲት ድላይ መጥታ “አማኑኤል” “አማኑኤል” እያለች
ፈለገችኝ የሚለው የድርሰት ማጣፈጫ ድራማ፥እንኩዋንስ በቦታዉ ለነበረ ፤ የጦርነትን ትርጉምን ባፈ ታሪክ
ለሰማም ሳያስገርም አይቀርም ።
የጓድ ያእብዮን መሰዋት እንዳወቅን ሬሳዉን አውጥተን ለማሸሽት ሞከርን፤የጠላት ኀይል ተጠናክሮ ጊዜውም
ሊነጋጋ ስለሆነ ምን እናድርገው አንገቱን ቆርጠን እንሂድ መልኩን እንቀይረው በመባባል እያለን፤ጠላት
ደርግ) ከካምፑ ወጥቶ በእግሩ ወደእኛ መምጣት ስለጀመረ ያእብዮን ከአንድ እርሸ ቆፍር ቆፍር አድርገን
አፈር አልብስነው ወደ አዶቢ ተራራ አፈገፈግን። ኣማኑኤል እንደሚለው ለእያብዮ አልተለቀሰለትም
መዝሙርም አልተዘመረለትም። የውቅሮ ጦርነት እንደነ ህብስቱ ያሉት ጀግኖች በጠላት ካምፕ ዘሎ
በመግባት የጠላትን መሳሪያ ቀምተዉ አፈሙዙን በጠላት ላይ እንዳዞሩ የተፋለሙበት፤ ብዙ ጓዶች ከጠላት
ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀዉ እጅ በእጅ እየተዋጉ በኢትዮጵያዊነታቸዉ ኮርተዉ በጀግንነት የተሰዉበት
ጦርነት እንጅ ፤ አማኑኤል እንደሚለው የእሱና የጥቂቶች ጀብዱ ሥራ የታየበት ጦርነት አልነበረም።
የውቅሮን ጦርነት በበላይ የመሩት ሁለት አመራሮች በህይወት እዚህ አሜሪካ አገር አሉ። በ”አሲምባ ፍቅር”
የተጻፈዉን እንደሰሙና ፥ በተለይም የወቅቱን ሁኔታና የተከፈለዉን ታላቅ የጓዶች መስዋእትነት በአይኑ ከአየ
ጓድ የተነገረ መሆኑን ሲሰሙ በጣም እንዳሳዘናቸው ገልጸውልኛል። የራሳቸውን መልስም ያቀርባሉ ብየ
እምናለሁ።
3ኛ፤-በአጠቃላይ የኢሀሰን አመራር በሚመለከት፤
አማኑኤል (“ማንጁስ”) በወጣት እድሜዉ ኢሕአሠን መቀላቀሉና ፤ ከጠባብ ከልሉ ይልቅ ህይወታቸዉን
ለመላ ኢትዮጵያዉያን ጭቁን ሕዝብ መስዋእት ለመክፈል ቆርጠዉ ከወጡት ጒዶች ጋር ጎን ቀደም ብሎ
ተሰልፎ ፤ የተከፈለዉን አብይ መስዋእትነት ያየ፤ የትግሉን ዉጣ ዉረድና አያሌ መከራ አብሮ የተካፈለ ፤
በጓዶች መካከል በነበረዉ እኔ ለአንተ ፤ እኛ ለኛ የህይወት ፏፏቴ፤ የትግሉን ስርአት፤ የሠራዊቱን ስነምግባር
እየቀሰመ ያደገ ሲሆን፤ አብይ መስዋእትነትን የከፈለበትን የትዉልድ ታሪክ ለማሳነስ የኢሕአሠን ሰራዊት
ዲስፕሊን የሌለዉ የነጭ ሰራዊት አስመስሎ ለማቅረብ በመጽሐፉ ዉስጥ የተጠቀሱት አንዳንድ ተግባራት
በወቅቱ የነበረዉን የኢሕአሠን የአሰራር መላ ሁኔታ የማያንፀባርቅ መሆኑን ለመጠቆም ጥቂት መጥቀስ
አስፈላጊ ይመስለኛል ። የመፅሐፉ አዘጋጆች ለቅመም የጨመሩት ቢሆንም አያስገርምም። ለምሳሌ
1-አማኑኤል በተደጋጋሚ ለኢሕአሠ አመራሮች በወታደራዊ ስነስርአት አነጋገርኳቸው የሚለው ፍጹም
ከኢሐአሠ አሰራር፤ባህልና ልምድ ያልነበረ ነው። ትግራይን ለቀን ከወጣን በኃላ በኤርትራ በረሀ በሸምሸሚያ
ቁጭ ብለን ስራ በፈታንበት ጊዜ የሠራዊቱ ሞራል እንዳይወድቅ ለማዝናናትና ግዜን ለማሳለፍ በግልና በቡድን
በዙ ነገሮች ተሰርተዋል። ቲያትሮች ተቀናጅተዋል ፤ ስነፅሁፎች ተደርሰዋል፤ አረንጒዴ ቅጠሎችም የጒዶችን
ስም እየተጎናጸፉ እየተቀቀሉ ተበልተዋል። የአየር ወለድ ጓዶች ኢሕአሠን በፈቃዳቸዉ የተቀላቀሉና 5

የኢሓፓንና የሠራዊቱን መላ አላማ ተቀብለዉ በዉጊያ ስልት በአርአያነት ጀግንነታቸዉን ያስመሰከሩ፤ ታላቅ
መስዋእትነትን የከፈሉ ታሪክ ወደፊት የማይረሳቸዉ ጓዶች ናቸዉ። የአየር ወለድ ጓዶች ሰራዊቱን
ለማዝናናትም በተደረገዉ ጥረት የተጫወቱትን ታላቅ ሚና በቦታዉ ለነበረ ማንም ጓድ በግልጽ የታየ ነበር።
ለምሳሌም ለመጥቀስ አየርወለዱ ጓድ ተኮላ ከጓድ ከሰተ ጋር ቲያትሩን ሲጀመሩ ፤ ለሰራዊቱ ቲያትር
እንዲያዘጋጁም ያበረታታቸዉ ጓድ አበጀ (ኮለኔል አለመየሁ) ነበር (ኢሕአሠ ፀሐፊ አስማማው ወይንም አያ
ቫረው ገጽ 266)። የአየር ወለድ ጓዶችም በፈቃደኛነት ስለ ሰልፉ ስንስርአት፤ስለሰላምታ አሰጣጥ ያሰለጥኑን
ነበር። ስልጠናዉ የጊዜ ማሳለፊያ እንጅ ለአመራሩ ሰላምታ ለመጠቅሞ አልነበረም። አማኑኤል አብዛኛዉን
አስተዋጽኦ “የሰላምታ ስልጠና” በየጊዜው የጠቀሰው፤ ለመጽሐፉ ማጣፈጫ ይሆን ተብሎ ይሆን ወይስ
በቀዩ ሰራዊት የነጭ ሰራዊት ተግባር ያከናውናሉ በማለት ሰራዊቱን ለማራከስ?
2-አማኑኤል ከሰራዊቱ በመገንጠል ከጓዲት ድላይ ጋር ብዙ ጊዜ ብቻውን እንዳሳለፈ ይጠቅሳል። በተለይም
ከውቅሮ ኦፕሬሽን በኃላ፤ሰራዊቱ በማፈግፈግ በነበረበት ጊዜ እሱና ጓዲት ድላይ ልብስ ለማጠብ ተብሎ ቀኑን
ሁሉ እንዲያውም እስከሚጨልም ጊዜ ድረስ ብቻቸውን መሆናቸው፤በአሰራር ላይ በፍጹም የማይደረግ
የመጽሐፉ ማጣፈጫ ተረት ነው። በሐይል አመራርና በተለያዩ የሰራዊቱ አመራር ውስጥ ሰርቻለሁ።እንደ
አማኑኤል አባባል ሁለት ጓድና ጓዲቶች ለብቻ ቀኑን ሙሉ የሚጠፉበት ተልእኮ ተደርጎም ተሰምቶም
አያውቅም።ጓዶች ወደዋና ሰፈር ለተልእኮ ይላካሉ እንጂ ከሀይል እንቅስቃሴ በመለየት የሙሉ ቀን ራንዴቡ
(rendezvous) እንዲያውም አድሮ መምጣት የፈጠራ ሀተታ ብቻ አይደለም፤ የልጅነት ቀልድ ነዉ ።
4ኛ- ጓዲት ድላይን በሚመለከት፤-
ከጓዲት ድላይ ጋር ነበረኝ የሚለው የፍቅር ግንኙነት በፍጹም ያልነበረና ለመጽሀፉ ማጣፈጫ የተፈጠረ
ታሪክ ነው።ይህንንም ለማለት የበቃሁት በመጀመሪያ ስለ ጓዲት ድላይ የተወያየነዉ አማኑኤል የጉዲቶችን
የትግል ታሪክ በመጽሀፉ ዉስጥ ለመጨመር በነበረዉ ፍላጎት ነበር። እኔም ለጓዲቶች ብቻ ሳይሆን
ለሁላችንም የምታኮራ የምታስመሰግን የትግል አርአያ ከጓዲት ድላይ በላይ የለምና ጥሩ መርጠሀል
እፈልጋለሁ ነው ያልኩት። ከዚያም ጓዲት ማሽረሻ ጋር አገናኝቼው ስለ ጓዲት ድላይ አሟሟትና ስለ
መጨረሻ ጊዜዋ የነገረችውን፤ስለ ድላይ በዝርዝር የአጫወተችውን ትቶ፤ በመጵሓፉ ዉስጥ ለአንባብያን
ያቀረበዉ፤ አብዛኛዉ ታሪክ ግን ልብ ወለድነት የሞላበት ፥ በወቅቱ የነበረዉን የሰራዊቱ የግኑኝነት መመሪያ
ያልተከተለ የፈጠራ ወሬ ሆኖ ስላገኘሁት፤ አንድም መጽሀፉን አማኑኤል አልጻፈዉ ወይም ሆነ ብሎ ታሪክን
ለመበረዝ ሙሉ በሙሉ ተባባሪ ሆኖአል በማለት ተጠራጠርሁ። የጓዲት ድላይን የትግል ታሪክ፤ ለጓዶች
የነበራትን ፍቅር ፤ የጦር ቆራጥነቷና የከፈለችዉን መስዋእትነት በደምብ ለሚአዉቋት ጓዶች አማኑኤል
በመጽሓፉ ዉስጥ “ድላይ በፍቅር ተመስጣ እግሮቿ መሀከል የተተኮሰውን (የባረቀውን) ጠበንጃ (ሦስት
ጥይት) ከየት እንደተተኮሰ ማወቅ አቅቶአቸው፤ባለቤቱ እርሶ አደር ከነሱ መተኮሱን ነገሩን ብሎ ማቅረቡ
የድላይን የወታደራዊ ችሎታ ለማንቋሸሽ ወይም እኛን ደንቆሮ ለማለት ተብሎ ወይም አሁን ለማጣፈጫ
የተፈጠረ ትእይንት እንጂ ፤ ጓዲት ድላይ እንኳን የባረቀን ጠብመንጃ ያውም በሁለት እግሮቿ መሀል ማወቅ
አይደለም በሩቅ በተተኮሰ ጥይት እርቀቱን መገመት ትችላለች። ድምጹስ ይቅር ፤ የባሩዱ ሽታስ ምን
አጠፋዉ ? ከዋሹ አይቀር ለአንባቢያን እሱንም ምስጥ አድርጎ ጠበንጃ እጆሮዉ ላይ መባረቁንና እንዳሸት
አፍንጫውን ያዘጋውን ድላይ በወቅቱ የተቀባችዉን የሽቶ አይነት ቢጠቁም ታሪኩን ለማመን ይረደል። ምን 6

ይደረግ ጠብመንጃ ላልያዙ እውነት ይመስላልና፤ ይህን መጽሀፍ ያቀነባበሩት ደራሲያን ልብ ወለድ
በመጨመር የአማኑኤልን የትግል ታሪክ አሳንሰዉታል፤፤ አማኑኤልም ስለ ጓዲት ድላይ የተነገረዉን ለምን
በሙሉ እንዳላሳተመዉና ይህን መጽሀፍ የጻፉት ሌሎች ናቸው፤ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ መልሱ “አይ ከናንተ
በቀር ህዝቡ ወዶታል፤ሁሉ እያመሰገነኝ ነው፤”ነበር። እንግዲህ እናንተ ፍረዱ። በETHIOMEDIA ድላይን
በሚመለከት ሐይሉ በለሳ በዝርዝር የገለጸው ትችትና ፤ አራቱም የቀድሞ የኢህአሰ ጓዲቶች በጋራ የጻፉትን
አንብቤዋለሁ ፤በአጻጻፋቸው ሙሉ በሙሉ የምስማማበት ነው። የጓዲቶች መስዋትነትና የትግል አጋርነት
የመጽሀፍ ማጣፈጫ ሊሆን አይገባውምና አማኑኤል እዉነቱን አንድ ቀን ገልጦ ይነግረናል ብየ ተስፋ
አደርጋለሁ ።
5ኛ፤-ደብተራው (ፀጋየ ገብረመድህን በሚመለከት)
አማኑኤል “በአሲምባ ፍቅር “ ላይ አበበ(ደብተራው ፀጋየ ገብረመድህን) በአንድ በኩል አንባገነን ፤ ጨቋኝ
የማይከሰስ ፍጹም አለቃ አድርጎ ያቀርበዋል። በሌላ በኩል በጣም የሚቀርበው የሚያከብረው መሪ
እንደነበረ ይነግረናል። ወደ ጎንደር በተመደበበት ጊዜም ከፍቅሩ ብዛት የተነሳ ለማስታወሻ የሚሆን አንድ ነገር
እንዲሰጠው ጠይቆ መሳሪያ እንደተለዋወጡ አትቷል። መሳሪያ መለዋጥ አይደለም የወጭ ብሎ መሰነባበት
በኢሕአሠ ሆኖ የማይታውቅ የፈጠራ ትችት ወይም ለማጣፈጥ የቀረበ ነው እላለሁ። አበበ(ደብተራው)
ሽጉጡን ጣለ ተብሎ በመጽሀፉ የጠቀሰው ሀሰት ሲሆን በዛ ጊዜ ሽጉጡ ለከተማ ስራ እንደተላከ አሁንም
በድርጅቱ ውስጥ ያሉ ጓዶች ይናገራሉ። በወቅቱ ሽጉጡ ጠፍቶበታል የተባለውም ጓድ አማኑኤል እስከዛሬ
ካላወቀዉ ወደ ከተማ ሲላኩ የነበሩ ጓዶችን ለመሸፈን ነበር ይላሉ።
6ኛ፤-ስለ ነበለት ጦርነት (የሓይል-74)
ሀቁ በነበለት የነበረችው ኀይል ከአንዱ መንደር እንዳረፈች በተለይም በአንዷ ጋንታ ላይ እንደተኙ ተከበው
ብዙ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ነገር ግን ሁለቱ ጋንታወች በደንብ አድርገው የወያኔን 3 ባታሊወን ቀኑን ሙሉ
ሲዋጉ ውለው ከፍተኛ ጉዳት በወያኔ ላይ ማድረሳቸውን የኢሕአሠ የሓይል 74 የጀግንነት ታሪክ እስከአሁን
በወያኔወች ዘንድ የሚታወስ ነው ። አማኑኤል ኢህአሰ ከወያኔ ጋር ባደረገው ውጊያ እንዳልተካፈለ እያወቀ
ለምን የነበለትን ጦርነት አጣጥሎ ለመጻፍ እንደፈለገ (አሲምባ ፍቅር ገጽ 380)ፍርዱን ለአንባቢያን
እተወዋለሁ። ከአንድ ጋንታ አራት ብቻ እስኪቀሩ ተደመሰሱ የሚለን ለምን ይሆን? በመጽሀፉ የከተተው
የትግራይ ልጆች ጀግንነት፤የወያኔን ጥንካሬ ሊያወሳልን ብሎ ወይም አስቦ ይሆን ? ስለ ነበለቱ ጦርነት በቦታዉ
የነበሩ ቢያወሩ ሀቁ እንዴት በወጣ ነበር።
7ኛ፤-የአማኑኤል ኢሕአሠን ክህደት
አማኑኤል ከሰራዊቱ ሲወጣ ከሌሎች ሁለት የትግራይ ጓዶች ጋር በመሆን በጦርነቱ መሀል ጓዶችንና ጓዲቶችን
አስተኝቶ መሳሪያ በመስረቅ ከድቶ ወደ ኤርትራ በመኮብለሉ ብዙ ባያስገርመኝም፤የራሱን ክህደት እንደ
ትክክለኛ አመለካከት ሊያስረዳን መሞከሩ የበለጠ አሳዝኖኛል። ነገሩ የወያኔና የኢሀሰ ጦርነት ተፋፍሞ ወደ
ቤዝ በቀረበበት((አሲምባ ፍቅር ገጽ 383-397)ጊዜ ስለነበር ብዙም ለኛ ለነበርነው አይደንቀንም። ብዙ
የትግራይ ተወላጆች ((አሲምባ ፍቅር ገጽ 383) እንደዚሁ ዘብ በሚመደቡበት እየጠፉ መክዳት የየእለት 7

ተግባር ሆኖ ነበር። አማኑኤል በመጽሀፉ እንዳቀረበው የትግሬ ልጆች በየጊዜው በመመካከር እንደዚህ ያለ
የክህደት ተግባር መፈጸማቸው በህብረ ብሄረሰብነቱ የሚያምነዉን ቆራጥ ትግራይ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ
ጀግኖች የመስዋትነት ታሪክ ላይ ጥላሸት መቀባት ነው እላለሁ። እነዚያ ወሎ ተይዘው ኢህአፓን አንኮንንም
ብለው የተረሸኑት ጓዶች ፤እጅ አልሰጥም ብሎ ከፎቅ ተወርውሮ የተሰዋውን ተስፋዪ ደበሳይ፤በውቅሮ
የወደቁት እነ ያእብዮ፤ እነ ተስፋዪ ደሳለኝ(ጴጥሮስ) ደበሳይ፤በዛ በኤርትራው መሬት ገና ትግሉን ሲጀምሩ
በሳህል በረሓ ህይወታቸው ያረፈችው የእነ መሃፉዝ ታሪክ ማበላሸት ባልተገባው ነበር።የወታደራዊ ይዘትና
(MILITRY STRATEGY) የመራራውን ትግል እስትራቴጂ መርምሮ ድርጅቱ መፈራረሱን ስላረጋገጥኩ
ከጓደኞቼ ጋር ወደ ኤርትራ ሄድኩ ይለናል። በወቅቱ በነበረዉ ሁኔታ ግን ከህደት ይመስላል ። በጦርነት ሜዳ
ያመኑህን ጓዶችን አስተኝተህ ከዘርና ጎሳ ጋር ተመካክሮ ትጥቅ ይዞ መጥፋት አጸያፊ ተግባር መሆኑን
ብዙም መከራከር አይገባም።
8ኛ፤- መጽሀፉ በዘር ላይ ያተኮረ በተለይም የትግራይ ልጆችን ጀብደኝነት ለማውራት የተጻፈ ነው ብል
ብዙም አልተሳሳትኩም።ለነገሩማ አማኑኤል ለምን መጻፍ እንደፈለገ ስጠይቀው “አይ የኛ ትግራይ ልጆች
ታሪክ በተለይ በኢህአሰ ውስጥ የነበረውን ታሪክ መጻፍ እፈልጋለሁ “ ብሎኝ ነበር። ለምን የተለየ ረሀብ
አላጋጠማችሁ፤የተለየ ተራራ አልወጣችሁ፤የተለየ ጥይት አልተኮሳችሁ ብየ ስጠይቀው “አይ እኛ ነን
ያሳለፍነውን የምናውቀው በወያኔ እና በኢህአፓ ውስጥ ብዙ ተሰቃይተናል ተመክሮአችንን መጻፍ
እፈልጋለሁ“ ነው ያለኝ። እውነቱን ነው በመጽሀፉ ውስጥ የጠቀሳቸው አብዛኛወቹ የትግራይ ልጆችን ጀግንነት
ነው። ይባስ ብሎ ደግሞ ለአንድ ቀን ያየውን (መለስ ዝናዊ) ስለማግኘቱና ስለማየቱ ጥርጣሬ ቢኖረኝም ፤
አገኘሁት ብሎ ሊስለው ሊቀባው፤ አሁን የሚፈልገው (አሲምባ ፍቅር በገጽ 161-162) አሁን ከመለስ
ራዕይ ጋር መግጠሙን በግልጽ ያሳያል።ገና በነሐረጋዊ ዘመን፤ገና ወያኔ እንጭጭ በነበረበት ጊዜ መለስ ዜናዊ
አዋቂ፤አስተዋይ፤መጽሀፍ የሚያነብ ረጋ ያለ ብስል ነበር ይለናል።
በአጠቃላይ የአማኑኤል “የአሲንባ ፍቅር “ በመውጣቱ ብዙወቻችንን እውነተኛ የኢሕአሠን ታሪክ
እንድንጽፍ ማበረታታት ብቻ ሳይሆን በታሪክ ተጠያቂነታችንን እንድናስብ ይመረምራል። ከብዙ ጓዲቶችና
ጓዶች ጋር እንድንወያይበትም ምክንያት ስለሆነ በዚህ አማኑኤልን አመሰግነዋለሁ። እኔም ሆነ ሌሎች
በትግሉ ያለፍን እውነተኛውን ታሪክ በመጻፍ ለትውልድ ማስተላለፍ ሀላፊነት አለብን።ሁላችንም
የምናውቀውን ሀቁን ለመናገር፤ለመጻፍ ለማቅረብ፤በውይይት መካፈል ይገባናል እላለሁ። ከሰላሳ አመት
በፊት የነበረውን የትግል ጉዞ በአሁኑ አመለካከት በርዞ፤ሰርዞ አጨማልቆ ማቅረብ ግን በታሪክ አስጠያቂ
ያደርገናል። የአሁኑን የፖለቲካ አመለካከት በድሮ ታሪክ ላይ ለማንፀባረቅ መሞከር ግን ተገቢ አይደለም።
ያስጠይቀናል የታሪክ ተወቃሽ ያደርገናል።

ሽፈራው(ሀይሌ)
ከሂውስተን, ቴክሳስ
ኦክቶበር 23/2013

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
    Print       Email
  • Published: 11 years ago on October 24, 2013
  • By:
  • Last Modified: October 24, 2013 @ 10:15 am
  • Filed Under: Ethiopia
  • Tagged With:

Average Rating

5 Star
0%
4 Star
0%
3 Star
0%
2 Star
0%
1 Star
0%
<"Without the support of our readers, the Maleda Times website would not exist in its present form">

You might also like...

በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ መከላከያ ከአማራው ማህበረሰብ እና ከፋኖ ጋር ጦርነት ገጥሟል

Read More →

This site is protected by wp-copyrightpro.com

%d bloggers like this:
Skip to toolbar